የትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኢፈርት) እና ያቀፋቸው ድርጅቶች በትግራይ ክልል የተፈጠረው ልዩነት ሰለባዎች ሁነዋል ሲሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ገለጹ።
በዚህም ምክንያት የሶስተኛ ወገን ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርግ እና እየሰፋ የሄደ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት ለሁለት ቀናት ሐምሌ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀለ ከተማ በተካሄደው ትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኢፈርት) አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ተቋሙ ስላጋጠመው አደጋ እና ከተሳታፊዎቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
በኢፈርት የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ጉዳዩ በህግ እንዲታይ መቅረቡን ጠቁመው ይህም በባሰ ደረጃ ጉዳዮቹን ሊያወሳሰበው ይችላል ብለዋል፤ ተቋሙ ላጋጠመው ችግር ሁሉም መወገኖች በከፍተኛ የህዝብ ሀላፊነት በምክክር እና በትዕግስት እንዲፈቱት አሳስበዋል።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ለህዝብ ጥቅም ሲባል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለበት ሃላፊነት እጁን በማስገባት ሊፈታው እንደሚገደድ አሳታውቀዋል፤ “ለህዝቡ ጥቅም ሲባል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጣልቃ ለመግባት ይገደዳል” ብለዋል።
በኢፈርት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንድ ሶስተኛ የምክር ቤቱ አባላት ፒቲሽን በማሰባሰብ ጉባኤ መጥራት እንደሚችሉ መደንገጉን ተከትሎ የተጠራ ጉባኤ መሆኑን ከክልሉ መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ህጋዊ የትዕምርት ባላደራ ቦርድ መሆኑን በመግለጽ ላይ የሚገኘው በአቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ የሚመራው አካል በበኩሉ የትግራይ ፍትህ ቢሮ ያሳለፈውን ውሳኔ በመጥቀስ በሁለቱ ቀናት የተካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ህግን የጣሰ እና በኢፈርት ስር የሚገኙ ድርጅቶችን በቀጣይ ቀውስ ውስጥ የሚከት አካሄድ ነው ማለታቸውን ዘገባዎቹ ጠቁመዋል።
