ከ50 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል

Date:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 7ኛ ስብሰባው ላይ የቀረቡ ምክረሃሳቦችን እና የጸደቁ ውሳኔዎችን በሚመለከት የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢው በመግለጫቸው በገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው የጸደቁት ምክረ ሃሳቦች አምስት የተለያዩ ውሳኔ ሳይሆኑ አንድ ወጥ የሆነ የፖሊሲ ፓኬጆች ናቸው ብለዋል።

ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከቀጥተኛ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች ወደ ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች እየተሸጋገረ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በማብራሪያቸው በተጨማሪ ምን አሉ ?

” ኮሚቴው በመጀመሪያ ያቀረበው የፖሊሲ ምክረሃሳብ አመታዊ የብድር እድገት ገደብ ወይም Credit Cap ሙሉ በሙሉ ማንሳት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመታዊ የብድር እድገት ገደብን እንደ ጊዜያዊ እርምጃ የተጠቀመው ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች በመጠቀም በወለድ ምጣኔ ላይ ተመስርቶ ወደሚሰራ የገንዘብ ስርዓት ሙሉ በሙሉ እስከሚሸጋገር ድረስ ነበር።

አሁን ላይ ማዕከላዊ ባንኩ ይህንን አላማ አሳክቷል።

ይህ የብድር እድገት ገደብ መነሳት ፈጽሞ የፖሊሲ ለውጥ ሳይሆን በአሰራር ዘዴ ላይ የተደረገ ለውጥ ነው።

ይህንን የብድር እድገት ገደብ ማንሳት ብቻውን ከብድር እድገት ጭማሪ ጋር ተያይዞ በዋጋ ግሽበት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና በመረዳት ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የባንኩን ጥብቅ የፖሊሲ አቋም ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ኮሚቴው ተገንዝቧል።

በመሆኑም የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን በአንድ መቶኛ ከ 15 በመቶ ወደ 16 በመቶ እንዲጨምርና አሁን ያለው የ3 በመቶኛ ክልል(interest rate Coder) በነበረበት እንዲቆይ ተወስኗል።

ስለሆነም የፖሊሲ ወለድ ተመን ጭማሪውና የብድር እድገት ገደቡ መነሳት አብረው ሊታዩ ይገባቸዋል።

አንዱ መሳሪያ ጊዜውን ሲጨርስ ሌላው ደግሞ ሲጠነክር የሚያሳይ ሲሆን ይህም ድምር ውጤቱ ከእዚህ ቀደም ከነበረው ይልቅ ባንኩ ይበልጥ ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም መያዙን ያመላክታል።

ተጨማሪ ጥበቃ ለማድረግ እና ይበልጥ ለማጠናከር ኮሚቴው የብድር እድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንኩ በእያንዳንዱ ባንክ ላይ በሚያካሄደው መደበኛ ግምገማ መሰረት ከመደበኛው የመጠባበቂያ ተቀማጭ የተለየ ተጨማሪ የመጠባበቂያ ተቀማጭ Targeted Reserve Requirement እንዲተገበር ምክረሃሳብ ቀርቦ በቦርዱ ጸድቋል።

ይህም ማዕከላዊ ባንኩ በአጠቃላይ ኢኮኖሚ የብድር መጠንን ከመገደብ ይልቅ በእያንዳንዱ ባንክ ላይ አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ ያስችለዋል።

የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ኮሚሽን መጠንም ከ 2.5 በመቶ ወደ 1.5 እንዲቀንስ የተደረገ ሲሆን ይህም ከሸቀጦች የገቢ ንግድ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመቀነስ እና በዋጋ ግሽበት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ለመገደብ ያግዛል።

በተጨማሪም የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነት ለማሻሻል ፣የውጭ ምንዛሬን ገበያን ለማሳለጥ የዋጋ ግኝትንም ለማሻሻል ላኪዎች ከሸቀጦች ወጪ ንግድ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ላይ ለባንኮች እንዲሸጡ የሚጠይቀው ከ50 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

በአጠቃላይ እነዚህ እርምጃዎች በአንድ ላይ ሲታዩ ኮሚቴው የሰጠዉን ውሳኔ ወጥነት ያንጸባርቃሉ እንዲሁም የኢትዮጵያ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ቀጥተኛ ወዳልሆኑ እና በገበያ ላይ በተመሰረቱ መሳሪያዎች ላይ የመተማመን ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያሉ።

ይህም ሂደት በቀጣይነትም ቢሆን የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ላይ ያለንን ቁርጠኝነት በማጠንከር ዲስፕሊን ባለው መልኩ የሚቀጥል ይሆናል ” ብለዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኔታንያሁ እና ትራምፕ የፊታችን ማክሰኞ በዋይት ሀውስ እንደሚወያዩ ተገለጸ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፤ ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ...

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ውይይት አካሄደች

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጄ. ማሲንጋ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን...

የካፍ ፕሬዝዳንት የ2027 አፍሪካ ዋንጫ በ24 ተሳታፊ ሀገራት እንደሚካሄድ አስታወቁ

የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሙትሰፔ የ2027...

የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ነፃ የጤና ምርመራና ሕክምና መስጠት ጀመረ

ሆስፒታሉ በቀን ከ300 በላይ ታካሚዎችን ያስተናግዳል የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ከሐምሌ...