ስኬት ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት ከታክስ በፊት ከ1.54 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉን አስታወቀ።
ባንኩ ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው የበጀት ዓመቱን አፈፃፀም ግምገማና የትኩረት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ የሥራ አመራር ጉባኤው ላይ ይህንኑ አረጋግጧል።
በጉባኤው ላይ በቀረበው አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደተገለጸው፣ ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የካፒታል መጠኑን 10.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉንም ወደ 7.9 ቢሊዮን ብር ከፍ አድርጓል።
በተጨማሪም በተከናወነው የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ 14.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገልጿል።
በእነዚህ ጠንካራ የንግድ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ በ51 በመቶ ዕድገት በማሳየት 29 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመላክቷል።
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳምጠው አለማየሁ የበጀት ዓመቱ በላቀ ስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል። አያይዘውም የባንኩን ተወዳዳሪነት የበለጠ ለማጠናከር፣ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እና ለደንበኞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት ለማሻሻል የሚያስችሉ አዳዲስ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የባንኩ ዲስትሪክቶች፣ ቅርንጫፎች እና ሠራተኞች የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው ለመረዳት ተችሏል።
