የኦሮሚያ ክልል ያቃረበውን ቅሬታ የተመለከተው የአሸማጋይ ቡድን አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ መሆኗ በህገ መንግስት ይጻፍ የሚል ምክረ ሃሳብ አቅርቦ፤ የ500 ቡድን አዲስ አበባ የፌደራል መንግስት አካል ናት በሚል የተስማማበት ቀርቶ “ተጠሪ” በሚል እንዲተካ ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ምክክሩ ተጠናቋል።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 38 ቀናት ሲካሄድ የቆየው የምክክር ጉባዔ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተጠናቋል።
አዲስ አበባን በተመለከተ በሁለት ጎራ ከፍሎ ሲያከራክር የቆየው ጉዳይ አሁንም በልዩነት ተመካካሪዎች ካሳለፏቸው 4 ምክረ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ ነው።
አዲስ አበባን በተመለከተ ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ለርዕሰ ቡድን ተመካካሪዎች በንባብ የቀረበው ሰነድ “አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ትሁን፤ ራሷን በራሷ ታስተዳድር” በሚለው ላይ ሁሉም ከስምምነት መድረሱን ያስረዳል።
ክልሉ ከከተማው አስተዳደር ልዩ ጥቅም ማግኘት ስላለበት የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ ክፍልም “የጋራ ጥቅም” በሚል እንዲሻሻል ከስምምነት መደረሱን ያክላል።
አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና መቀመጫ ትሁን ከሚለው ጋር በተያያዘ ግን የ500 ቡድን ሁለት ምክረ ሃሳቦችን አቅርቦ ተንቦ ነበር።
እነሱም፦ ክልሎች የራሳቸውን መቀመጫ መወሰን እንዲችሉ በሕገ መንግሥቱ ይካተት የሚለው አንደኛው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 (ወይም አግባብ ያለው አንቀጽ) ላይ የሰፈረው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ከተማዋን እና ክልሉን የሚመለከቱ ጉዳዮች በሕግ ይወሰኑ የሚል ድንጋጌ ይካተት የሚሉት ናቸው።
ይሁንና የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ይህን ጉዳይ በተመለከተ ቅሬታ አቅርበው ኮሚሽኑም ይህን ችግር የሚፈታ የክልል ጉባዔ ጠርቶ ከዚያ ውስጥ አሸማጋይ ቡድን አቋቁሞ የነበረ ሲሆን፣ የቡድኑንም ውሳኔ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ ለ4,000 ጉባዔተኞች ትናንት ምሽት በንባብ ማቅረባቸው ታውቋል።
በተነበበው መሠረት አሸማጋይ ቡድኑ በሕገ መንግሥቱ “የኦሮሚያ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ናት” የሚል ድንጋጌ ይጻፍ የሚል ምክረ ሃሳብ መስጠታቸውን እና ከተማዋ “የፌደራሉ አካል ናት” የሚለው ተስተካክሎ “ተጠሪ” በሚል እንዲተካ ምክር ማቅረቡን ውሳኔውን ያነበቡት ኮሚሽነር ዮናስ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ግን ከቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ውስጥ የየትኛውን እንደሚቀበል ለጊዜው አላስረዳም።
ነገር ግን በምን መስፈርት እንደሆነ ባልዘረዘረው ሁኔታ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበሩ ውሳኔዎችን መርምሮ “ለሀገር የሚበጅ” ያለውን ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተናግሯል።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው ምክክር ትናንት ምሽት ለ4 ሺህ ጉባዔተኞች ተነቦ ተወካዮችም በይፋ ምክረ ሃሳቦችን ለኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አስረክበዋል።
በዚህም መሠረት ለቀረቡ 8 ዋና ዋና አጀንዳዎች፣ 96 ንዑስ አጀንዳዎች እና 225 መሪ ጥያቄዎች 400 ምክረ ሃሳቦች መዘጋጀታቸው ታውቋል።
በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በአብዛኞቹ ላይ መስማማት መደረሱን ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ተናግረዋል።
ሙሉ በሙሉ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች በ4 ምክረ ሃሳቦች ላይ ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም በልዩነት ቀርበዋል።
በዚህ የኢትዮጵያ ሰንድቅ አላማ አሁን ያለው አርማ ይቀጥል የሚለው እና ህብረብሔራዊነትን ባካተተ መልኩ ተጠንቶ ይካተት የሚለው አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ የምትከተለው የመንግስት አይነት የፓርላሜንታሪ ሆኖ ርዕሰ ብሔር እና ርዕሰ መንግስት ሆኖ የሚያገለግል ፕሬዚዳንት ከፓርላማ ይመረጥ በሚበዙት የተደገፈ፤ሙሉ በሙሉ የፕሬዚዳንት ስርዓት ሆኖ ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ በህዝብ ይመረጥ የሚለው በጥቂቶች የተደገፈው ሁለተኛ የልዩነት ሀሳብ ነዉ።
የፌደሬሽን ውክልና የተመለከተው ሶስተኛ ሲሆን ፤አዲስ አበባን ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተያይዞ የክልሉ መቀመጫ ትሁን ከሚለው ጋር ተያይዞ የቀረበው አራተኛው ጉዳይ ነው።
በዚህም በፌደራል ከተሞች ጉዳይ ሥር አንድ (የአዲስ አበባ ጉዳይ)፣ በአገር ግንባታ አጀንዳ ሥር አንድ (የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ)፣ በመንግሥት አደረጃጀት አጀንዳ ሥር ሁለት ምክረ ሃሳቦች (የፌደሬሽን ምክር ቤት ውክልና እና የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ምን ይመስል የሚሉት) በልዩነት ምክረ ሃሳብ የቀረበባቸው ጉዳዮች ናቸው።
በቀሪዎቹ አጀንዳዎች ላይ ጉባዔተኞቹ በሁሉም ምክረ ሃሳቦች ተስማምተዋል ተብሏል።
ለምሳሌ በሃይማኖት አጀንዳ ሥር፦ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ ቢደረግ፣ የኢሬቻ በዓል እና የበዓለ ሃምሳ በዓል በካላንደር ተካተው እንዲከበሩ፣ የሃይማኖት ፖሊሲ እንዲወጣ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሃይማኖት ተቋማት በሕግ እንዲቋቋሙ፣ ለ7ኛው ቀን አድቬንቲስት ተከተዮች በቅዳሜ ዕለት አስገዳጅ ሥራ እና ፈተና እንዳይኖር እና ሌሎች ምክረ ሃሳቦች ያለ ልዩነት ቀርበዋል።
በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ ሥር ደግሞ፦ መሬት የመንግሥት፣ የግል እና የወል ነው የሚለው አንዱ ሲሆን ይህም አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት “መሬት የሕዝብ እና የመንግሥት ነው” የሚለው ድንጋጌ እንዲሻር ይጠይቃል።
በየአሥር ዓመቱ የሕዝብ ቆጠራ ይካሄድ የሚለው የሕገ መንግሥቱ ክፍል ቀርቶ ከዚያ በታች ባሉ ሕጎች ዝርዝር ነገሮች እንዲደነገጉ፣ ሴቶች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት የሚቀሩበትን ቀን ለመቀነስ የንጽሕና መጠበቂያዎችን በነጻ እንዲያገኙ እና መቀየሪያ ሥፍራም እንዲመቻችላቸው፣ የታክስ አወሳሰን ሂደት ላይ ነጋዴዎች እንዲሳተፉ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን የሚሉት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
ብሔራዊ መዝሙርን በተመለከተ ደግሞ አሁን ያለው እንዲቀጥል፣ የክልሎች ግን አሉታዊ መልእክት ያላቸው ስላሉ እንዲታረሙ ጉባዔተኞች ተስማምተዋል።
በማጠቃለያው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሂደቱ የተሳተፉ ተመካካሪዎችን አመስግነው፣ የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ወደፊት ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርቡ ጠቅሰዋል።
