የቀድሞ አመራሮችና ባለሙያዎች ተከሰሱ

Date:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ለሕዝብ መዝናኛነት እና ለልዩ ፕሮጀክት የተከለለ ሰፊ ይዞታን፣ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀምና ከጥቅም ጋር በመመሳጠር ለግል ማህበር አሳልፈው ሰጥተዋል የተባሉ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በ30 ተጠርጣሪዎች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረበው ይህ የክስ መዝገብ፤ የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ሕጉንና የሙስና አዋጁን በመጥቀስ ያቀረበው ነው።

በክስ መዝገቡ ላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቀድሞ ምክትል ኃላፊ ሞሊቶ አባይነህ፣ የቢሮው የመልሶ መልማት ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉጌታ፣ የከተማዋ ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ አብዮት ጁፋራ እና የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር ኃላፊ የነበሩት ቸርነት አበበ ይገኙበታል።

ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ዝርዝር ክስ መሠረት፣ ተከሳሾቹ እርስ በርሳቸው በመናበብና በጥቅም በመመሳጠር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ክልል ውስጥ የሚገኝና በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሳይቀር “በመሬት ባንክ ቋት” ውስጥ እንዲጠበቅ የጸደቀን ይዞታ ለግል ጥቅም አውለዋል።

ይህ ይዞታ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በ”ዓድዋ ፓርክነት” የሚታወቅ፣ በ10ኛው መዋቅራዊ ፕላን መሠረትም ከመጋቢት 2010 ዓ.ም በኋላ በ”ዊንዶስ ኦፍ አፍሪካ” (Windows of Africa) ልዩ ፕሮጀክት ክልል ውስጥ እንዲካተት የተደረገ ነው።

ቦታው ለጎልፍ ክለብ፣ ለከተማ ደረጃ መናፈሻና ለተለያዩ የሕዝብ መዝናኛ አገልግሎቶች ተብሎ የተከለለ የመንግስት ይዞታ መሆኑን እያወቁ፣ ተከሳሾቹ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊሰጣቸው የማይገባውን “ዮርዳኖስ ዘውዲቱ እና ጓደኞቻቸው ሲሚንቶ አከፋፋይ ሕብረት ሽርክና ማህበር” ለተባለ አካል 2 ሺህ 905 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል።

በዚህ ሕገ-ወጥ አሰራር ምክንያት መንግስት በወቅታዊ የሊዝ ጨረታ ዋጋ ሊያገኝ ይችል የነበረውን 168 ሚሊዮን 724 ሺህ 405 ብር ጉዳት እንዲደርስበት ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ሦስት ተከሳሾች ድርጊቱን ለመፈጸም 7 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር “የእጅ መንሻ” ወይም ጉቦ መቀበላቸው በክሱ ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ የተቀበሉትን የጉቦ ገንዘብ ምንጩ እንዳይታወቅና ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ፣ በተለያዩ የባንክ ሂሳቦች በማዘዋወር “በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ” ወንጀልም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከሰዋል።

ፍርድ ቤቱ ክስ ከቀረበባቸው 30 ተከሳሾች መካከል ለ13ቱ ክሱ እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን፣ የክስ መቃወሚያ ያላቸውን ለመስማትና ያልቀረቡ ተከሳሾችን ለመጠባበቅ ለመጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። መረጃው የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...