አንዳንድ የፓርቲው አመራርና አባላት ውሳኔውን ተቃውመውታል
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፣ ራሱን አክስሞ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሀድ የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ፡፡
ቦዴፓ ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም መተከል ቡለን ውስጥ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፣ ራሱን አክስሞ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አመንቲ ገሺ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአስቸኳይ ጉባኤው “የውህደት ውሳኔ ነው ያሳለፍነው” በማለት የአስቸኳይ ጉባኤው ዓላማ ፓርቲውን ማክሰም እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር፣ ቦዴፓ ህልውናውን አክስሞ “ያለውን ኃይል፣ አጀንዳና ንብረት ይዞ፣ ብልጽግናን ይቀላቀላል” ብለዋል፡፡ ህልናውን ለማክሰም ውሳኔ ያሳለፈው ፓርቲው የሚቀላቀለው የክልሉን ብልጽግና ቅንጫፍ ሳይሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራውን ዋናውን ብልጽግና ፓርቲ መሆኑን አቶ አመንቴ ለዋዜማ ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡
አቶ አመንቴ ወደ ብልጽግና ለመግባት በምን እንደተስማሙ ከዋዜማ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች “ተግባብተናል” ከማለት የዘለለ ዝርዝር የስምምነት ይዘቶችን ከመግለጥ ተቆጥበዋል፡፡ የውህደቱ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ዝርዝር የስምምነቱን ይዘቶች ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
