ዋና መሥሪያ ቤቱን በሌጎስ ናይጄሪያ ያደረገውና በአፍሪካ ግንባር ቀደም ከሆኑ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ የሆነው ዜኒት ባንክ፣ በኢትዮጵያ አዲስ በተከፈተው የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዝናቡ ይርጋ ከባንኩ ተወካዮች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ኢትዮጵያ ግዙፍና ታማኝ የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በኢኮኖሚ ጥንካሬዋ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ እና እየተገነቡ ያሉ ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለፋይናንስ ዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም ምክትል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
የዜኒት ባንክ የዓለም አቀፍ ገበያ መስፋፋት የቡድን ኃላፊ ኦሉካዮዴ አኪንቢኑ በበኩላቸው፣ ባንካቸው በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ባለው ኢኮኖሚ እና በተደረጉት የዘርፍ ማሻሻያዎች መሳቡን ገልጸዋል።
ባንኩ በተለይም በዲጂታል የፋይናንስ መፍትሄዎች እና በመንግስት የሚመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፍ ረገድ ያለውን ዕድል እያጠና መሆኑን ተናግረዋል።
ዜኒት ባንክ በአሁኑ ወቅት በኮርፖሬት፣ በችርቻሮ እና በዲጂታል ባንክ አገልግሎቶች የሚታወቅ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱም የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ለማጠናከርና የካፒታል አቅምን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ባንኩ በኢትዮጵያ ሥራ እንዲጀምር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በውይይቱ ወቅት አረጋግጧል።
