ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሽን ባንክ እና ኢታ ሶሊሽን ጋር በመተባበርም ያዘጋጀውን ዙሪያ የተሰኘ አዲስ የቢዝነስ አውቶሜሽን ሶሉሽን ይፋ ሆኗል።
ዙሪያ ሶሊሽን (የክፍያ ማሽን) የኢ.አር.ፒ ፣ የፒ.ኦ.ኤስ እና ካሽ ሬጂስተር አገልግሎቶችን በአንድ ላይ ለመስጠት የሚያስችል የቢዝነስ አውቶሜሽ ሶሉሽን ሲሆን የንግድ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን እና የቢዝነስ እንቅስቃሴን የሚያቀላጥፍ እንደሆነ በመክፈቻው መርሀግብር ተገልጿል።
የዙሪያ ሶሉሽን ለንግድ ተቋማት በርካታ ፋይዳዎችን ይዞ የቀረበ ሲሆን ክፍያን በቀላሉ ለመፈፀም፣ ምርቶችን ለመቆጣጠር፣ ደንበኞችን በቅልጥፍና ለማስተናገድ እና የፋይናንስ አያያዝን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞን በቀዳሚነት እየመራ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም፥ ደንበኞች ከ54 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ባሉት ቴሌ ብር እና ሌሎች የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም ክፍያቸውን በዙሪያ የክፍያ ማሽን መፈፀም እንደሚችሉ የኩባንያው ቺፍ ሞባይል መኒ ኦፊሰር ብሩክ አድሀና አንስተዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመቀናጀት የዙሪያ ሶሉሽን ያቀረበው የዳሽን ባንክ፥ ቀድመው ለመጡ 200 ደንበኞች ለአንድ አመት ከክፍያን ነፃ የሂሳብ ምዝገባ እና የተቋማትን ሃብት ማስተዳዳር (Enterprise Resource Planning) እንደሚያቀርብ የባንኩ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር ኤልያስ ሁሴን በመድረኩ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ባንኩ ማሽኑን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከማመቻቸት ባለፈ ለአገልግሎት አቅራቢ ደንበኞች “አሁን ይግዙ ቀስ ብለው ይክፈሉ” የሚል የፋይናስ አቅርቦት እንደሚያመቻች አስታውቋል።
የኢታ ሶሊሽን መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ተመስገን ገ/ህይወት (ዶ/ር) በበኩላቸው ሶሉሹን ይፋ ለማድረግ ሁለት አመታትን የፈጀ መሆኑን አንስተው ውስብስብ በሆነው የግብይት ስርአትን ውስጥ የሚያጋልጡ መስተጓጉሎችን በመቅረፍ ረገድ ዙሪያ የማይተካ ሚናን እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የዙሪያ ሶሉሽን ፈጣን የቢዝነስ ግብይትን፣ ግልጽ አሰራርን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ከወረቀት ገንዘብ ንክኪ የጸዳ የቢዝነስ ግብይትን ለመፈፀም ያስችላል ተብሏል።
በአገር በቀል አቅም የበለፀገው ዙሪያ የቢዝነስ ሶሉሽን ሁሉንም የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ካርዶች መቀበል የሚችል እንዲሁም ነጋዴዎች የሚያንቀሳቅሱትን ሃብት በቀላሉ ለማስተዳደር እና ማንኛውንም የክፍያ መረጃዎች በአንድ ያካተተ ደረሰኝ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ሶስቱ ተቋማት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከ10ሺ ለሚበልጡ ነጋዴዎች ዘመናዊ የዲጂታል ሶሉሽኖችን በማቅረብ የስራ ቅልጥፍናና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም አገልግሎታቸውን ይበልጥ እንዲያጎለብቱ በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
NBC Ethiopia
