የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) የንግዱን ዘርፍ ወደ ተሻለ ለውጥ ለማሳደግ ከውጭ ሀገራት ጋር የቢዝነስ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል የኢትዮ-ቤልጂየም የንግድ ኮንፍረንስ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ የንግዱን ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት ከቤልጂየምና በሉግዘምበርግ ንግድ ዘርፍ የተወጣጡ አካላት ጋር ተሞክሮዋቸውን ወይንም የልምድ ልውውጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና እያበረከተ የሚገኝ ተቋም መሆኑን አንስተው፤ ዘርፉን ለማሳደግና ዘርፉን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ይህ ሲሆን የህብረተሰቡን መብት ፍላጎትና ጥቅም ለማሳደግ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር፣ የውጭ ሀገር ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባና የሀገር ውስጥ ገጽታ እንዲገነባ የሚያስችል አሰራር መፍጠር ይገባል” ብለዋል።
ምክር ቤቱ ይህንን ጉባኤ ሲያዘጋጅ በቤልጂየም ኤምባሲ፣ በሉግዘምበርግ ንግድ ምክር ቤት፣ በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ትብብር ማድረጉን አስታውቀዋል።
በዚህ የቢዝነስ ተልዕኮ ላይ ከቤልጂየም የመጡ በግብርና፣ በታዳሽ ሃይል፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሕክምና እንዲሁም በፕላስቲክ መልሶ ማልማት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በኢትዮዮጵያ በመገኘት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን አስተዋውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ከሀገር ውስጥ ተመሳሳይ ኩባንያዎች ጋር የቢዝነስ የልምድ ልውውጥና ትስስር የሚፈጥር መድረክ መሆኑ ተመላክቷል።
የንግድ ኮንፈረንሱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዘለቀ ተመስገን እና የአዲስ አበባ ቻምበር ተ/ዋና ፀሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ መልዕክት አስተላልፈዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
