የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ስር ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የዕዳ ሽግሽግ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ከስምምነት መድረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
ስምምነቱ እ.አ.አ ማርች 2025 በመርሕ ደረጃ የተደረሰውን የብድር ሽግሽግ በይፋ ተግባራዊ የሚያደርግ እና ለሀገሪቱ የ3.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ዕዳ የክፍያ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህም ለዓመታት ሲደረግ ለነበረው ድርድር ስኬታማ መቋጫ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የመንግሥት ዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ ስምምነቱ ከእያንዳንዱ የኮሚቴው አባላት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት ተግባራዊ ይሆናል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ስምምነቱን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፤ “በእስካሁኑ ሂደት የተንፀባረቀው የትብብር መንፈስ በሁለትዮሽ ስምምነቶች ሂደት ወቅትም እንደሚቀጥል እና ሂደቱን ለማፋጠን እንደሚረዳ የጸና እምነት አለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች ጋር በቅን ልቦና መሥራቷን እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።
