(ይትባረክ ዋለልኝ)
ዐዲስ ቸኮል፤ የቪኦኤ የአፍሪቃ ቀንድ አገልግሎት የኢትዮጵያ ዘጋቢ ኾኖ ከስድስት ዓመት በላይ ሠርቷል፡፡ በዋናነት የድሬዳዋ እና አካባቢዋ ዘጋቢ ነው፤ ነዋሪነቱም በዚያው በድሬዳዋ ከተማ ነው።
በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ(ፌስቡክ ገጽ) ላይ በሚያደርገው ጠቃሚ ተሳትፎም ብዙ ወዳጆችን ማፍራት የቻለ ትጉህ እና ጠንካራ ጸሓፊ ነው። በጠባዕዩ ተግባቢ እና ትሑት የኾነው ዐዲስ፣ ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።
ታታሪው ጋዜጠኛ ዐዲስ፣ ከአራት ዓመት በፊት በመሠረተው ትዳር ያፈራው፣ የአንድ ዓመት ከአምስት ወር ዕድሜ ያለው ልጅ አባት ነው፡፡ ይኹንና ለቤተሰቡ የአባወራነት ሓላፊነቱን ሳይወጣና የአባትነት ፍቅሩን ሳያጣጥም፣ በግል ዐቅሙ የማይቋቋመው የጤና እክል ገጥሞታል፡፡
ዐዲስ በጭንቅላቱ ውስጥ የአንጎል ዕጢ ተገኝቶበታል። ዕጢው መኖሩ በሐኪሞች ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባለው ገንዘብ በሀገር ውስጥ ሕክምናውን እየተከታተለ ቆይቷል። አኹን ግን ጥሪቱን ጨርሶ፣ ሕመሙም ተባብሶ፣ ለሕይወቱ በሚያሰጋው ደረጃ ላይ ደርሷል።
ይህን ዐይነቱን የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና ለዐዲስ ቸኮል መስጠት የሚችል ሆስፒታል በጣሊያን ሀገር የተገኘ ሲኾን፣ ራሱ ዐዲስም የሕክምና ማስረጃዎቹን ልኮ ከባለሞያዎቹ ጋራ ሰፊ የቪዲዮ ውይይቶችን አድርጓል፡፡
ዕጢው በቀዶ ሕክምናው ሳይወገድ ከዚኽ በላይ ከዘገየ፣ በማንኛውም ጊዜ ሕይወቱን እስከማሳጣት የሚያደርስ ጉዳት እንደሚያስከትልበት የሕክምና ባለሞያዎቹ ለዐዲስ ነግረውታል፡፡
ሆስፒታሉ፣ ለዐዲስ ቸኮል የሚያስፈልገውን የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና (ዌክ ሰርጀሪ) ለመሥራት 42ሺሕ ዩሮ(48ሺሕ ዶላር) ክፍያ ጠይቋል፡፡ ለመሰል የአንጎል ቀዶ ሕክምና ሥራዎች በዓለም አቀፍ ሆስፒታሎች ከሚጠየቀው ክፍያ አንጻር ለዐዲስ የሚፈለገው ተመጣጣኝ መኾኑን ለመረዳት ቢቻልም፣ አኹን ዐዲስ እና የቤተሰቡ አባላት ባሉበት ኹኔታ የሚቻል አይደለም።
ዐዲስ ቸኮል ሞያዊ ተግባሩን በትጋት የሚያከናውን ጠንካራ ሠራተኛ ቢኾንም፣ የአንጎል ዕጢው ባስከተለበት ከፍተኛ ተጽእኖ ምክንያት የሥራ እንቅስቃሴው የተገደበ በመኾኑ የሚያገኘው ክፍያም ዝቅተኛ ነበር፡፡ የተጠየቀው የሕክምና ወጪም ከፍተኛ በመኾኑ፣ የጤና እክሉን በይፋ አሳውቆ በአደባባይ ድጋፍ ማሰባሰብ አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል።
ይህ ተማጥኗችን የደረሳችኹ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እና በጎ አድራጊዎች ኹሉ፣ ዐቅማችኹ የፈቀደውን ድጋፍ በጋዜጠኛ ዐዲስ ቸኮል ስም በተከፈተው የጎፈንድ ሚ እና ከዚኽ በታች በስሙ በተከፈቱት ሌሎች አካውንቶች አማካይነት በመለገስ፣ የወንድማችንን የዐዲስ ቸኮልን ሕይወት በመታደግ እንድትተባበሩን በታላቅ አክብሮት እና በፈጣሪ ስም እንማጠናለን፡፡
GoFundme (ጎ ፈንድ ሚ)፡- https://shorturl.at/YHOSA
ዐዲስ ቸኮል አለነ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፡- 1000061095989
ዳሽን ባንክ:- 5009778150021
አቢሲኒያ:- 225994951
አዋሽ:- 013200542570900
በተጨማሪም ይህን የድረሱልኝ የነፍስ አድን መልእክት #SHARE በማድረግ ለሌሎች በማድረስ እንድትተባበሩን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ለትብብራችኹ ኹሉ በእጅጉ እናመሰግናለን።
ጓደኞቹ እና የሞያ አጋሮቹ!
