• መጽሐፉን ያሳተሙት ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ሚቸል ኮሎን ናቸው
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ትርክቶች የያዘ፣ “የእኔ ተጋድሎ ለኤርትራ እና ለአፍሪካ” የሚል ርዕስ ያለው አዲስ መጽሃፍ በእንግሊዝኛ ታትሟል።
ከኢሳያስ ጋር በአገራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረጓቸውን ተከታታይ ቃለ ምልልሶች ቃል በቃል በማሰባሰብ በፕሬዚዳንቱ ፍቃድ ያሳተሙት፣ ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ሚቸል ኮሎን ናቸው።
መጽሃፉ የኤርትራን “ራስን የመቻል” መርህና ኢሳያስ ስለ ዓለማቀፉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት ያላቸውን አመለካከት ለአፍሪካዊያን ወጣቶች ለማስተዋወቅ የታለመ ሲኾን፣ በአማርኛና ሌሎች ቋንቋዎችም ይታተማል ተብሏል።
መጽሃፉ ካካተታቸው ምዕራፎች መካከል፣ “ኤርትራና ቅኝ ግዛት”፣ “የሱዳንና አፍሪካ መከፋፈል”፣ “ኤርትራ ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም የገጠማት ጣልቃ ገብነት”፣ “የአሁኗ ኤርትራ ተግዳሮቶች” እና “ፕሮፓጋንዳን እንዴት መቋቋም ይቻላል?” የሚሉ ይገኙበታል። ኢትዮጵያዊው የታሪክ ተመራማሪ፣ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን የመጽሐፉን ማጠቃለያ ጽፏል፡፡
(ዋዜማ)
