ይህ ጥያቄ የቀረበው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቡድኑን ደህንነት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት እና በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ውጥረት በመጨመሩ ምክንያት የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎቹ ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወሩ በመጠየቁ ነው።
ፊፋ ባወጣው መግለጫ ሁሉም ተሳታፊ ሃገራት አስቀድሞ በወጣው የጨዋታ መርሃ ግብር መሰረት በተመደቡባቸው ከተሞች ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ በማሳወቅ ኢራን በአሜሪካ የምታደርጋቸው ጨዋታዎች እንደማይቀየሩ አረጋግጧል።
ኢራን በምድብ ጨዋታዎቿ ሰኔ 9 ቀን (June 15, 2026) ከኒውዚላንድ እንዲሁም ሰኔ 15 ቀን (June 21, 2026) ከቤልጂየም ጋር በሎስ አንጀለስ የምትጫወት ሲሆን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋን ሰኔ 20 ቀን (June 26, 2026) በሴያትል ከግብፅ ጋር ለማድረግ ተመድባለች።
ምንም እንኳን የኢራን ስፖርት ሚኒስቴር ከውድድሩ የመውጣት ፍንጭ ቢሰጡም የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የእስያ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ግን ቡድኑ አሁንም በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል። ኢራን ከውድድሩ የምትወጣ ከሆነ በእርሷ ምትክ ለመሳተፍ እንደ ኢራቅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያሉ ሃገራት ከፍተኛ እድል እንዳላቸው ተጠቁሟል።
