ለሚያጋጥሙ ሰደድ እሳቶች ተገቢው ዝግጅት ይካሔድ!

Date:

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለማችን እየተከሰቱ ያሉ ሰደድ እሳቶች በኢትዮጵያም ማጋጠም ጀምረዋል፡፡ ለአብነት እንኳን፣ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ወንዶ ወረዳ እንዲሁም በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በሚገኘው ሃላይዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ የሰደድ እሳት አጋጥሟል፡፡

በዘርፉ የተካሔዱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ የሰደድ እሳት በደን ላይ ተፈጥሯዊ በሆነና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚደርስ የደን ቃጠሎ ቢኾንም፣ በአብዛኛው በአገራችን የሚከሰተው ግን ቆላና ቆላ ቀመስ በሆኑ ዘርዛራ ደኖች፤ በቁጥቋጦና በግጦሽ ስፍራዎች ነው፡፡ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ እስካሁን ያልበረደውን የካሊፎርኒያውን ጨምሮ፣ በአውስትራሊያ እና በሌሎችም በርካታ የዓለም ታዋቂ ጥብቅ ደኖች ለቀናት ሲቃጠሉ፣ ቃጠሎውን ለመቆጣጠርም ከላይ በሄሊኮፕተር፣ ከታች በመኪና ኬሚካልና ውኃ ሲረጭ ማየቱ ተለምዷል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ላለ የሠለጠነ የዱር ሰደድ እሳት ቁጥጥር የታደለች ሀገር አይደለችም፡፡ ባለፉት ዓመታት ስሜን ተራሮችን ጨምሮ በተለያዩ ጥብቅ ፓርኮች ውስጥ ተመሳሳይ አደጋ ሲያጋጥም የታየውም ይኼው ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፉት ስድስት ዓመታት በፓርኮች ውስጥ እየተከሰተ ያለው የዱር ሰደድ እሳት ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ነው፡፡ ተገቢውና በችግሩ አሳሳቢነት ልክ የመገናኛ ብዙኀን ሽፋን ሲያገኝም አልታየም፡፡ ምናልባትም ዓለም ጆሮ የሰጠው ሰሞነኛው የሎስ አንከለስ ሰደድ እሳት እነኚህን በኢትዮጵያ በስፋት ሲያጋጥሙ የሰነበቱ ሰደድ እሳቶች መለስ ብለን ለመመርመር ጥሩ ምክንያት የሚኾነውም ለዚህ ነው፡፡ ጥያቄው ታዲያ በፓርኮች ውስጥ እሳት እንዳይከሰት ቀድሞ ምን ተሠርቷል? የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደሠለጠኑት አገሮች የቱሪስት መስህብ በሆኑት ፓርኮቿ እሳት ቢከሰት ከባህላዊው አሠራር በተለየ ልትከተለው የምትችለው አማራጭ ያላት አትመስልም፡፡ ስለሆነም በዱር የሚከሰት ሰደድ እሳት የሚሸነፈው የአካባቢው ማኅበረሰብ ለቀናት ያህል ከእሳት ጋር ግብግብ ከፈጠረ በኋላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት፣ የዱር እንስሳቱንና ዕፀዋቱን ሳይነጥቅ አያልፍም፡፡ ከዚህ ቀደም በባሌ ተራሮች ፓርክ እንዲሁም በሌሎች የዱር ሰደድ እሳት ለማጥፋት ሲሉ የተሰው ግለሰቦች መኖራቸውም አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ የዱር ሰደድ እሳትን ለመከላከል ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂ የላትም፡፡ በፓርኮች ውስጥ አርብቶ አደሩም ሆነ አርሶ አደሩ እሳት የሚጠቀምና ፓርኮቹም ለእሳት ተጋላጭ መሆናቸው በመንግሥት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ስትራቴጂና ፖሊስ ነድፎ መንቀሳቀሱ ላይ ትኩረት አልተሰጠም፡፡ ይህም ለዓመታት ጥብቅ ፓርኮች እየተባሉ የሚጠሩትን የቱሪስት መስህቦች ለአደጋ አጋልጧል፡፡

የእሳት አደጋ የተጋረጠባቸውን ፓርኮች ለመታደግ የእሳት ቁጥጥርና አያያዝ ሥርዓት እየተዘጋጀ መኾኑ ከተገለጸ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሥርዓቱ እሳት ቀድሞ እንዳይከሰት፣ ከተከሰተም ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ግብዓቶችን የያዘ ሲሆን፣ የእሳት መከላከያ መስመሮችንና መሠረተ ልማት መገንባትም የሥራው አካል ይሆናል፡፡ ይህ ሥርዓትም ለመፋለም የሚያዳግተውን እሳት ለማጥፋት በየጊዜው ርብርብ የሚያደርጉ የየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ወታደሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎችንም የሚያግዝ ይሆናል፡፡ የሥርዓቱ መዘርጋት እንደ ከዚህ ቀደሙ ‹‹የእሳት አጥፉ ዘመቻና ጥሪ›› ሳይኖር ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ እሳት ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር የሚያስችል ይሆናል፡፡

ከሰሞኑን በምዕራብ አርሲ ወንዶ ወረዳ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ፣ የአካባቢዉ ማህበረሰብ እና የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ ከማድረጋቸው ጀምሮ፣ እሳት የማጥፋቱ ስራ ላይ የኮሌጁ ማህበረሰብ መሳተፉ መጠቀሱ ምን ያህል ይኽን ሥርዓት ተግባራዊ ያደረገ ነው የሚለውን ለመገምገም ግን ግልጽ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ሰፊ ትኩረት ሰጥተው ካሁኑ ዝግጅት እንዲያደርጉ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 222 የካቲት 8 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...