በክልሉ “አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ወደ ሥራ ለማስገባት የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ያስፈልጋል” ተብሏል
በትግራይ ክልል ለ2 ዓመታት የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶርያው ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ክልሉን እና አካባቢውን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ጥረት ቢደረግም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ተተኳሾች ሙሉ ለሙሉ አለመጽዳታቸውን ነዋሪዎች ለአሐዱ ተናግረዋል።
እነዚህም በተለይም ወደ መማር ማስተማር ሥራው በተመለሱ ትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ የሚገኙ መሳሪያዎች ተማሪዎች እና መምህራን ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ ጉዕሽ ትምህርት ቤቶቹን ወደ ስራ ከማስገባታችን በፊት ተተኳሾቹን ከቅጥር ጊቢዎቹ ውስጥ የማፅዳት ሥራ ቢሰራም፤ ሙሉ ለሙሉ ጸድተዋል ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።
በአሁን ሰዓት በክልሉ 416 ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዳልጀመሩም ኃላፊው አንስታውሰዋል።
“ተተኳሾቹ አለመፅዳታቸው የታየው ሥራ የጀመሩት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው” ያሉት ኃላፊው፤ ሥራ ያልጀመሩት ትምህርት ቤቶች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2015 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ወደ ሥራ እስካሁን በትግራይ ክልል ተግባራዊ አለመድረጉ ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም አሐዱ “አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ለማስጀመር ምን እየተሰራ ነው? መቼስ ይጀመራል?” ሲል የክልሉን ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ ጠይቋል፡፡
ኃላፊው በሠጡት ምላሽም፤ አሁን ላይ ዝግጅቶችን ጨርሶ በ2018 አዲሱን ስርዓተ ትምህርት በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረው የመጽሐፍ ህትመት ሥራ በበጀት እጥረት ምክንያት መቋረጡን ገልጸዋል፡፡
“ክልሉ ካለበት ችግር አኳያ መፅሐፉን አሳትሞ ወደ ሥራ ማስገባት እና አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ማስጀመር ባለመቻሉ የትምህርት ሚኒስቴርን እርዳታን ጠይቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው” ብለዋል።
በዚህም መቼ ይጀመራል የሚለውን ጉዳይ ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጠው ምላሽ የሚወሰን መሆኑንም ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
አሐዱ በጉዳዩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴርን ምላሽ ለማካተት ወደ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ደውሎ ጥያቄውን ያቀረበ ሲሆን፤ በዘርፉ ላይ ምላሽ ለመስጠት የተመደቡ አካላት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለማወቅ ችሏል፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
