“ያለ ፕሬስ መንግሥትም ኾነ ሕዝብ ሊያድግ አይችልም”
“ሕገ መንግሥቱ ካልተቀየረ ግን ችግሮች አሁንም ይቀጥላሉ”
“መንግሥት አሁን የያዘው እሳት የማጥፋት ሥራ ነው”
ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ
የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ነው፡፡ ክንፉ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የአራት ኪሎን መንበር በተቆናጠጠ ማግሥት የነጻውን ፕሬስ በመቀላቀል ከአምባገነኑ መንግሥት ጋር በመተናነቅ ዋጋ ከከፈሉ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ለተደጋጋሚ እሥርና በኋላም ለስደት ተዳርጓል፡፡ በስደት ዓለም በቆየባቸው ከሃያ ለሚበልጡ ዓመታትም ትግሉን በመቀጠል ሀገር ቤትና ከሀገር ውጪ በሚገኙ ሚዲያዎች ላይ መጣጥፎችን እና ትንታኔዎችን በመሥጠት ሥርዓታዊና ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ በብርቱ ታግሏል፡፡ ከመጋቢት 24ቱ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ወደሥልጣን መምጣት በኋላ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ክንፉ፣ ከወራት በፊት ከህወሓት ቡድን ጋር በነበረው ጦርነት ግንባር ድረስ በመሄድ ሰራዊቱን አበረታትቷል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ “እኛ እና እነሱ” በሚል ርዕስ መጽሐፉን ያስመረቀው ክንፉን፣ የግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ሃያ ዓመታትን ወደኋላ መልሶ ስለነበረው የነጻው ፕሬስ ትግል፣ ስለአሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ስላስመረቀው መጽሐፍ ይዘት ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የመጽሔታችን እንግዳ ለመኾን ፈቃደኛ በመኾንህ እያመሰገንን ወደ ነፃው ፕሬስ ለመቀላቀል ያነሳሳህ ምንድነው? የተቀላቀልክበት ወቅትስ መቼ ነበር? ከሚለው ብንጀምር?
ክንፉ፡- ነፃው ፕሬስን የተቀላቀልኩት ከዩኒቨርሲቲ እንደወጣሁ ነበር፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ልምድ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎችን መንግሥት ራሱ ወደ ሥራ ይመድብ ነበር፡፡ በእኛ ጊዜ ግን ይህ ነገር ቆሞ “እራሳችሁ ሥራ ፈልጉ” የሚል አዲስ መመሪያ ወጣ፡፡ መመሪያው የበቀል ዓይነት መንገድን የተከተለ ነው፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎች ከዚያ በፊት ወደ ብላቴ ዘምተው ስለነበር የኢሕአዴግ መንግሥት የዩኒቨርሲቲ ተማሪና መምህራንን አይወድም ነበር፡፡ ከእኛ በፊት 42 መምህራኖች ተባረውም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ከወርቅነህ ገበየሁም ጋ አብረን ነበር የተማርነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችን የጨረስነው ሁለታችንም ሥራ አጦች ኾነን ነበር፡፡ እኔ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ አንዳንድ ጽሑፎችን አወጣ ነበር፡፡ የመመረቂያ ጹሑፎችንም አዘጋጅ ነበር፡፡ እኔ በፊትም የጽሑፍ ግንዛቤው ነበረኝ፡፡ እናም ተሰባሰብን በመነጋገር ጋዜጣ ማዘጋጀት ጀመርን፡፡ በዚያን ጊዜ ወርቅነህም አብሮን ነበር፡፡ ጋዜጣውን ስንጀምር እውቀቱም ድፍረቱም ነበረን፡፡ ያው ሥራውን እንደጀመርን መንግሥታዊ አፈናውም ወዲያው ጀመረ፡፡
በዚያን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዓባይን በተመለከተ ግብፅ ሄደው ከሆስኒሙባረክ ጋር ተነጋግረው የመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ የአቶ መለስ መሄድ እንጅ የሄዱበት ጉዳይ ሚስጥሩ አይታወቅም ነበር፡፡ እኛ ግን የሄዱበትን ምስጢር ከእነ ፊርማው አገኘነው፡፡ በዚህም አቶ መለስ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ውል እንደተፈራረሙ ደረስንበት፡፡ ይህን ለሕዝብ ስናጋልጥ ሁላችንም ታሰርን፡፡ ከዚያ በኋላ በያንዳንዱ ሥራችን መታሰር ዕጣችን ኾነ፡፡ በየጊዜው እያሠሩ ይፈቱናል፡፡ ዓላማቸው ተስፋ ቆርጠን ሥራውን እንድንተው ቢኾንም ልንተው ግን አልቻልንም፡፡ በኋላ ግን ከማዕከላዊ ወደ ከርቸሌ ወስደው ረዘም ያለ ጊዜ አሠሩን፡፡ በወቅቱ የነበረው እሥራችን የፕሬስ አዋጁን በግልጽ የሚጻረር ነበር፡፡ የሚያሥሩን አካላትም ስለፕሬስ አዋጁ የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ታስረን በነበረበት ወቅትም “ከጀርባችሁ ማን አለ? መረጃ አውጡ” እያሉ ያሰቃዩን ነበር፡፡
ግዮን፡- የጋዜጣችሁ ሥም ምን ነበር?
ክንፉ፡- የመጀመሪያው ጋዜጣችን “ሞገድ” ነበር፡፡ በጣም ብዙ ኮፒ ነበር የሚታተመው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሞገድ ታሪክ አንድ የማይረሳ ሥራ ሰርተናል፡፡ ይኸውም አንድ ወቅት የኢሕአዴግ ወታደሮች ወደሰሜን ሸዋ ጅሩ አካባቢ መኪና አስቁመው ሲዘርፉ በጥይት ተመተው ሆስፒታል የገቡበት ኹነት ተከስቶ ነበርና፣ መረጃውን ሥፍራው ድረስ ሄደን በማጣራት ለሕትመት በማብቃት ጀብዱ ሰርተናል፡፡ በዚህ ሥራችን ራሳቸው ጭምር አድንቀውናል፡፡ በዚህ ሥራችን ሳይቀር ሊከስሱን ቢፈልጉም መረጃችን የተረጋገጠ በመኾኑ ሳይኾንላቸው ቀርቷል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የነበሩ ባለሥልጣኖቻቸውን አባረዋል፡፡ ሞገድን ስንሠራ ዝም ብለን ብቻ ሳይኾን የሚደርሱንን መረጃዎች ለማጣራት እንጥራለን፡፡ ለመንግሥት ሳይቀር “ይኼ መረጃ ደርሶናል፣ ምን ትላላችሁ?” ብለን እንጠይቃለን፡፡
ለምሳሌ በአንድ ወቅት “አልቱራቢ” የተባለው የሱዳኑ የእስልምና መሪ ኦጋዴን አካባቢ የኃይል ማሠልጠኛ ከፍቷልና “ይህን በተመለከተ መንግሥት የሚያውቀው ነገር አለ ወይ” ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ስዬ አብርሃ ነበር፡፡ የመለሱልን “ይህን ነገር ታወጡና እናንተው እራሳችሁ እንደአልሸባብ ትመታላችሁ” የሚል ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ግን መረጃውን አወጣነው፡፡ ካወጣነው ከ5 ቀን በኋላም አቶ ስዬ አብርሃ ራሱ ሚዲያ ላይ ወጥቶ “የአልሽባብ ወታደሮችን መታናቸው” ብሎ ተናገረ፡፡ እርሱ ይኼን ሲናገር ግን እኛ ባወጣነው መረጃ ተወንጅለን እሥር ቤት ነበርን፡፡
ግዮን፡- ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከእናንተ ተነጥለው ኢሕአዴግን የተቀላቀሉት መቼ ነበር?
ክንፉ፡- በሥራ ላይ እያለን ነበር ኢሕአዴግን የተቀላቀለው፡፡ አገባቡም ምስጢራዊ ነው፡፡ በምን መልኩ እንደገባም አላውቅም፡፡ በፊት በጣም ወዳጄ ነበር፡፡ በችግር ጊዜ አብረን ብዙ አሳልፈናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መጀመሪያ በአካል ያገኘኋቸው ጊዜ ያነሱልኝ ሐሳብ “ስለወርቅነህ የጻፍከው ነገር እንዳለ ኾኖ እርሱ ለአንተ መልካም አመለካከት ነው ያለው፤ በክፉው ጊዜ ተረዳድታችኋልና ሁሌ ያስታውስሃል ፤ ተነጋገሩ” የሚል ነበር፡፡
ግዮን፡- ስለወርቅነህ ገበየሁ የጻፍከው ምን ነበር?
ክንፉ፡- በወቅቱ ጋዜጣ ስንሠራ አንድ መረጃ መጣልን፡፡ ያንን መረጃም ለመሥራት የሄድነው ደግሞ ሁለታችን ነበርን፡፡ ባለመረጃዎቹ ከውጭ የመጡ በሕቡዕ የተደራጁ የኢህአፓ አባላት ናቸው፡፡ አንዳንድ መረጃዎችን እንሠጣቸው ስለነበር እኔና ወርቅነህም በዚህ መሠረት ከእነርሱ ጋር ቀጠሮ ይዘን ልናገኛቸው በተቀጣጠርንበት ቀን ስንሄድ ጠፉብን፡፡ ነገሩን “ለምን” ስል፣ ከእነርሱ ጋር የሚያገናኘን አካል እኔን ወቅሶ የመለሰልኝ መልስ “ሰዎቹን ለመንግሥት አሳልፋችሁ ሰጣችሁ” በማለት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር መረጃውን ለመንግሥት የሰጠው “እርሱ ነው” የሚል ጥርጣሬ ሊያድርብኝ ቻለ፡፡ እኔም ይህን ነው ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ተንትኜ የጻፍኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ራሱ ወርቅነህ ደህንነት ውስጥ እየሠራ መኾኑን ነገረኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያገኘኝ ጊዜ እንደውም “ወዳጄ ስለኾንክ እጠብቅሃለሁ” አለኝ፡፡ ከዚያም እርሱ ሻሸመኔ ደህንነት ቢሮ ተመድቦ ሲሄድ እኔም ከእርሱ ሸሸሁ ፤ ወደ ውጭ ሀገርም ወጣሁ፡፡ እዚያ እያለሁም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደኾነ ተነገረኝ፡፡
ግዮን፡- ከለውጡ በኋላ ሀገር ቤት ስትመለስ ከዶ/ር ወርቅነህ ጋር አልተገናኛችሁም?
ክንፉ፡- ተገናኝተናል፡፡ አሁንም ድረስ እንደዋወላለን፡፡ እንዲያውም መጽሐፌ ሲመረቅ “እንኳን ደስ አለህ ፤ እዚህ ብኖር እመጣ ነበር፡፡ አሁን ያለሁት ቱርክ ነው” ብሎ መልካም ምኞቱን ገልጾልኛል፡፡ ከዚያም በኋላ እየተገናኘንም እየተደዋወልንም እናወራለን፡፡
ግዮን፡- በነጻው ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ነበሩ የምትላቸው በጎ ነገሮች ምን ምን ናቸው?
ክንፉ፡- ፕሬስ ውሰጥ በነበርኩበት ጊዜ “ፕሬሱ”ን የምናየው እንደ አርት ነው፡፡ ፕሬስ ሕብረተሰብን የመቀየር ኃይል አለው፡፡ ሕዝቡ መብቱን እንዲያውቅ ፕሬስ ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ በተለይ በ1997ቱ ምርጫ ሕብረተሰቡ ፍራቻውን ከውስጡ እንዲያወጣ ብዙ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ አንዳንድ ባለሥልጣናት ሥማቸው እንዳይጠፋ ሳይቀር ከነውራቸው እንዲቆጠቡ አስችሏል፡፡ መንግሥታዊ በደል ከነበረው እንዳይከፋም ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተዘመረለት ነገር ቢኖር ነፃው ፕሬስ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲናገሩ ያስቻላቸው ነፃው ፕሬስ ነው፡፡ እስካሁንም ነፃው ፕሬስ በብዙ ነገር እየተበደለ ነው ያለው፡፡ የመጀመሪያው የሕትመትና መሣሪያዎቹ ዋጋ መጨመር ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ በየጊዜው ጋዜጠኞቹ መታሠራቸው ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ማስታወቂያዎቻቸውን በነፃው ፕሬስ ላይ ለማውጣት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ያለ ፕሬስ መንግሥትም ኾነ ሕዝብ ሊያድግ አይችልም፡፡ ነፃ አስተሳሰብን የሚያመጣው ፕሬስ ነው፡፡ ነፃ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የባሕል አስተሳሰብን የሚያመጣው ነፃ ፕሬስ ነው፡፡ ነጻ ፕሬሶች የሕዝብን አተያይ እየቀረጹ ባሉበት ሁኔታ የትኛውም አካል ጫና ያሳድርባቸዋል፡፡ እናንተን በጣም አደንቃለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ኾናችሁም ሥራችሁን አላቆማችሁም፡፡ ትንገዳገዳላችሁ ግን አልወደቃችሁም፡፡
ግዮን፡- ከሀገር ለመውጣት ያበቃህ ምክንያት ምን ነበር? የአወጣጥህ ሂደትስ ምን ይመስላል?
ክንፉ፡- እንደ አጋጣሚ እኔ በቱርክ ወይም በሱዳን አሊያም በሊቢያ ተሰደው እንደሄዱት ጋዜጤኞች አይደለም የሄድኩት፡፡ እኔ የሄድኩት ቀጥታ ነው፡፡ አካሄዴም ለሴሚናር ነበር፡፡ ነገር ግን አጋጣሚውን ተጠቅሜ በዚያው ቀረሁ፡፡ የቀረሁበት ምክንያት ደግሞ በጣም ብዙ ክሶች ስለነበሩብኝ ነው፡፡ ከክሶቼ ብዛት የተነሳ ዋስ የሚኾነኝ ሰው እንኳን አልነበረም፡፡ ዋስ ሲጠፋ ደግሞ እዚያው እስር ቤት መበስበስ ነው ምርጫው፡፡ ሰውም ዋስ መኾን እየፈራ መጣ፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ቤተሰብንም ያስፈራራ ስለነበር ነው፡፡ እኔም ይህ ሁኔታ ሲገጥመኝ እዚያው ቀረሁ፡፡ እዚያ ያለው ነገር ደግሞ ያው እንደሚታወቀው ስደት ነው፡፡ ስደት ላይ ከቋንቋ ጀምሮ ብዙ ችግር አለ፡፡ እዚህ የተማርከው ነገር ለዚያ ሀገር መሥሪያ መኾን አይችልም፡፡
በጋዜጠኝነት መቀጠል አልቻልኩም፡፡ በዚያ ለመቀጠል የሀገሩን ባሕል፣ ቋንቋ እና ታሪክ በደንብ ማወቅ ይጠበቅብኛል፡፡ እነዚህን የመሰሉት ተግዳሮቶች በስደት ሀገር ላይ ከፍተኛ ፈተናዎቼ ነበሩ፡፡ እነዚህ ፈተናዎች ለመሻገርም ብዙ ለመሥራት ሞክሬያለሁ፡፡ የሀገሩን ቋንቋ፣ ባሕል እና ታሪክ ለማወቅ ተምሬያለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ተግዳሮት አልፌና ተምሬ ሙያየን ቀይሬ መኖር ግዴታዬ ነበር ፤ አድርጌዋለሁም፡፡ ይህ የኾነው እንግዲህ በሆላንድ ሀገር ነው፡፡ ከብዙ ትምህርት በኋላ ሙያዬን ቀይሬ አሁን ኮምፒውተር ሳይንስ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ነው የምሠራው፡፡ ነገር ግን ከምወደው ሙያ ላለመላቀቅ ስል እየጻፍኩ ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም በኢሳት ምሥረታም ውስጥ ነበርኩበት፡፡ ምንም እንኳን ኑሮዬ ሆላንድ ቢኾንም ልቤ ያለው ሀገሬ ስለኾነ ከሙያዬ አልወጣሁም፡፡
ግዮን፡- በሆላንድ ምን ያህል ዓመት ቆየህ?
ክንፉ፡- ሆላንድ ወደ 21 ዓመት አካባቢ ቆይቻለሁ፡፡ አሁንም ያለሁት እዚያው ነው፡፡ እዚህ የመጣሁት ለጉብኝት እንጂ ነዋሪነቴ እዚያው ነው፡፡
ግዮን፡- ከለውጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገርህ የገባኸው መቼ ነው? ከቤተሰብህ ስትገናኝስ የተሰማህ ስሜት ምን ይምስል ነበር?
ክንፉ፡- እዚያ እያለሁ ስልክ እንኳን ለመደወል እሳቀቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም እናቴ ታለቅሳለች፡፡ ቀጥታ ስልክ ደውለን ካነጋገርን በጥቁር ዝርዝር ውስጥ ስላለን ስልካችንን ይከታተሉት ነበር፡፡መንግሥት “መርዘኛ ዳያስፖራ” ነበር የሚለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥትን የሚቃወሙ የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎችን ስለምናዘጋጅ ነው፡፡ ባለሥልጣናት ሲመጡ ስለምንቃወማቸው መንግሥት መርዞ ይዞን ነበር፡፡ “የሰው ልጅ ለምን ይገደላል?” ብለን ስለጮህን መርዘኛ ዲያስፖራ ብለውናል፡፡ እንደዚህ ብለው ስላሉን ከቤተሰብ ጋር ደውሎ ለመነጋገር እሳቀቅ ነበር፡፡ እናቴ “በዓይኔ ሳላይህ ትሞታለህ” ብላኝ ነበር፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ለውጡ ሁለተኛውን ወር ሲይዝ ሀገሬ ስመጣ እናቴ ማመን አቃታት፡፡ ሕልም ነበር የመሰላት፡፡ እቤት ገብቼ አድሬ ጠዋት ስነሳ ግን እናቴ የለችም፡፡ “የት ሄደች?” ብዬ ስጠይቅ “ስለት ለማድረስ ሄዳለች” ተባልኩ፡፡ እናቴ እኔን በዓይኗ ለማየት ለሦስት ታቦት ነበር የተሳለችው፡፡ እነዚያ ሁሉ ቦታዎች ጋር ስለቷን አድርሳ ስትመጣ በእልልታ አቀለጠችው፡፡ ቤተሰቦቼ ያሉት ጅማ ነው፡፡ በዚህም በልጅነቴ በአካባቢው አየውና እሰማው የነበረውን ነገር በሰመመን እያጣጣምኩ ባለሁበት ሰዓት እልልታ ስሰማ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፡፡ በቃላት መግለፅ የማልችለው ዐይነት ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ በዚህ ደስታዬ ልክ ታዲያ ረጅም ዓመት ዜግነቴን ተነጥቄ የኖርኩ ያህል ቁጭትና ከፍተኛ ሐዘንም ተሰምቶኛል፡፡
ግዮን፡- ለውጡን ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ትከታተለዋለህና አሁን የደረስንበትን ሁኔታ እንዴት ትገመግመዋለህ?
ክንፉ፡- መጀመሪያ የመጣሁ ጊዜ የነበረው ስሜትና አሁን ያለው ስሜት የተለያየ ነው፡፡ እኔ ከለውጡ በኋላ አራት ጊዜ መጥቻለሁ፡፡ መጀመሪያ የመጣሁ ጊዜ ተስፋም ፈተናም ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ ሰው ውስጥ ተስፋው ያመዘነ ነበር፡፡ ችግር ኖረም አልኖረም ሰው ተስፋ ከሌለው ዋጋ የለውም፡፡ በዚያን ጊዜ በብዙ ሰው ውስጥ ተስፋ ነበር፡፡ በእርግጥም ደግሞ ብዙ ለውጦች ተከናውነዋል፡፡ የፕሬስ ሕጉ፣ የጸረ ሽብር ሕጉ፣ ሌሎች አዋጆችም ተለውጠዋል፡፡ የእነዚህ ነገሮች በጽንሠ ሐሳብ ደረጃ መለወጥ ለሕዝቡ ተስፋ ሰጥቶት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ እየተራበም ቢኾን ተስፋ ስላለው ደስተኛ ነበር፡፡
ወደየትኛውም የሀገሪቱ ቦታ ብትሄድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፎቶ ተለጥፎ ይታይ ነበር፡፡ ይሄ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ትልቅ እድል ተፈጠረ አስብሎኝ ነበር፡፡ ከመምጣቴ በፊት አብሮኝ የሚሠራው አሜሪካዊ ኃላፊዬ “የዕረፍት ጊዜዬን ስለጨረስኩ መሄድ አልችልም” ስለው “እኔ እረፍት እሰጥሃለሁ፣ አፍሪካ ውስጥ የሚደረገው ነገር አይታወቅምና ሂድ” ነበር ያለኝ፡፡ ሥራውን እነርሱ ስለሚሠሩት በየትኛውም ሰዓት ነገሩ ሊቀለበስ እንደሚችል ያውቃሉ፡፡ እኔም በነጋታው ትኬት ቆርጬ መጣሁ፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ተመልሼ ስመጣ ሰውየው ያለው ልክ ኾኖ አገኘሁት፡፡ ነገሮች ሁሉ ተለውጠው ጦርነት ውስጥ ነበርን፡፡ በነገራችን ላይ እኔ እራሴም ግንባር ሄጄ ነበር፡፡ በማይጸብሪና በጋሸና ግንባሮች ተገኝቼ ነበር፡፡ እዚያ ኾኜ “አገር አገር” እያልኩ መጮህ ግብዝነት መስሎ ስለተሰማኝ ነበር ሥራዬን ትቼ የመጣሁት፡፡
ግዮን፡- ግንባር ተገኝተህ ጦርነቱን ስታይ ምን ተሰማህ?
ክንፉ፡- ከባድ ኃላፊነት (ሪስክ) ወስደን ነበር የሄድነው፡፡ ከእነ ታማኝ ጋር ነበር የሄድነው፡፡ በተለይ ተከዜ ለመድረስ ሊማሊሞ ተራራን መውረድ ስለሚጠበቅብን በዚህ ጉዞ ውስጥ መድፍ ሁሉ ሲተኮስ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ሠራዊታችን ለሀገሬ ብሎ እንደሚሞት ሁሉ ብንሞትም መስዋዕትነት ስለኾነ ሪስኩን ወስደን ሄደናል፡፡ ሁኔታው በጣም ያሳዝን ነበር፡፡ እዚያ አካባቢ የተደረገው ነገር መወለድን የሚያስጠላ ነው፡፡ ህወሓቶች የሰሩት ግፍ “ከሰብዓዊ ፍጡር የወጡ ናቸው ወይ?” ያስብል ነበር፡፡ ቄሱን ጥምጣሙን አስወልቀው በፊቱ ላይ ሚስቱን የደፈሩበት ሁኔታ ጭምር ነበር፡፡ ይኼ ይዘገንናል፡፡ ይህን ካየሁ በኋላ በጣም ተስፋ ቆረጥሁ፡፡ የውጭ ወራሪው ጣሊያን እንኳን ያላደረገውን ነገር እነርሱ አድርገውታል፡፡ እንደዚያም ኾኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ካሉት ይቅርታ ያደርጋል፡፡ እነርሱ ግን ይቅርታ ማድረግ ቀርቶ እየባሰባቸው መጡ፡፡ በማይጸብሪና በተለይ ደግሞ በጋሸና የነበረው የአስክሬን ብዛት በወቅቱ ምግብ እስካለመብላት ነበር ያደረሰኝ፡፡ ጋሸና ማለት እነርሱ 80 ሺህ ሠራዊት ደመሰስን ያሉበት ቦታ ነው፡፡ እነርሱ የሚናገሩት ውሸት ነው፡፡ ይኼን ደግሞ በአካል አረጋግጬ ነው የመጣሁት፡፡ በዚህም እስካሁን ሲናገሩት የቆዩት ሁሉ ውሸት መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ግዮን፡- ለውጡ በተጠበቀው ልክ መሄድ ያልቻለው ለምድን ነው ትላለህ?
ክንፉ፡- መጀመሪያ ላይ በለውጡ ማናችንም ትልቅ ተስፋ ነበረን፡፡ አሁን ላይ ግን ከተስፋው ይልቅ ፈተናው እንዲያመዝን የተደረገበት ምክንያት የኦሮሞ ልኂቃን በየዕለቱ የሚያደርጉትና የሚናገሩት ነገር ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ “ሐጫሉ ሞተ” ተብሎ ሻሸመኔ የኾነውን እናስታውስ፡፡ እኔ በዚህ ዙሪያ ህወሓት ላይ እጄን አልቀስርም፡፡ ገና ለውጡ መጣ በተባለ ጊዜ ከስድስት በላይ የሚኾኑ የኦሮሞ ድርጅቶች “አዲስ አበባ የእኛ ናት” የሚል ቅስቀሳ ጀመሩ፡፡ “ልዩ ጥቅም” የሚባለው ነገርም እንዲጮህ ተደረገ፡፡ ችግሩ የጀመረው ከዚህ ነው፤ አሁንም በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ልኂቃኑ የፈጠሩት ችግር ለውጡን ለዚህ እንዳበቃው ነው፡፡ እኔ የኦሮሞን ሕዝብ አውቀዋለሁ፤ አብሬው ነው ያደግኩት፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰረ ፍቅር ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ውሃ ሲጠይቁት ወተት የሚሰጥ ሕዝብ ነው፤ ይኼ በዓይኔ ያየሁት ሀቅ ነው፡፡ አሁን የሚታየውን ነገር ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለማመሳሰል መሞከር በጣም ስሕተት ነው፡፡ ልኂቃኑ ለሥልጣን ሲሉ የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የከፈለውን ዋጋ እና መስዋዕትነት ያኮስሱበታል፡፡
ምኒልክን ሲኮንኑ እነጎበና፣ እነ ፊታውራሪ ሐብተጊዮርጊስ፣ እነ ባልቻ፣.. ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የሠሩትን ሥራ ይዘነጉታል፡፡ እነርሱ ግን አማራን ከምኒልክ ጋር በማያያዝ ጠላት አድርገው ለዚህ ችግር አብቅተውታል፡፡ ይኼ ነው ዛሬ ላይ የአማራን እልቂት ያመጣው፡፡ እያንዳንዱ የኦሮሞ ልሂቅ የሚናገረው ንግግር የአማራን ሞት የሚያውጅ ነው፡፡ በቅርቡ አቶ ሌንጮ ባቲ “ኦሮሞን ኮንስትራክት ለማድረግ ኢትዮጵያን ዲኮንስትራክት ማድረግ ነበረብን” እንዳሉት ሌላውም ልኂቅ ሂሱን እንደሳቸው ማውረድ አለበት፡፡ 27 ዓመታት ሲበርዙት የነበረውን ወጣት እንደገና ለመመለስ ግን ሂስ እንደመዋጥ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ወጣት “ኢትዮጵያ ጠላት ናት” ብሎ የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሲባል በመጀመሪያ አማራን አንስተው ጠላት ያደርጉታል፡፡ ይሄ ትልቁ የሀገሪቱን ተስፋ የገደለ ጉዳይ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ላይም በርካታ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡ ይህን ሙከራ የሚያደርጉት ደግሞ እራሳቸው ናቸው፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኖሩ ተቃዋሚውም ኦሮሞ ኾኖ መጣ፡፡ ይኼ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉት ምንድነው የሚለው ጉዳይ መታየት ይኖርበታል፡፡ ዋናው የእነርሱ መዳረሻ ሥልጣን መያዝ እንጂ ለኦሮሞ ሕዝብ መቆርቆር አይደለም፡፡ ለኦሮሞ ሕዝብ ቢቆረቆሩ ኖሮ አሳንሰው በዚህ መልኩ አይቀርጹትም ነበር፡፡ አሁን የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ጋር አብሮ እንዳይኖር ልኂቁ በርዞታል፡፡ ይኼ በልኂቁ ተኮትኩቶ ያደገ ወጣት እራሱን ወደ ማጥፋት እያመራ ነው፡፡ አንዴ ከሐዋሳ ወደ ዐዲስ አበባ ስንመጣ ሻሸመኔ ላይ ያገኘናቸው ቁጭ ብለው የሚቅሙ ቄሮዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ቄሮዎች ድሮ ይሠሩበት የነበረውን የአበባ ፋብሪካ አቃጥለውታል፡፡ ይማሩበት የነበረውን ትምህርት ቤት አንድደውታል፡፡ ይታከሙበት የነበረውን ክሊኒክ አውድመውታል፡፡ ስለዚህ አሁን ሥራ ስለሌላቸው ቁጭ ብለው ይቅማሉ፡፡ ይኼ በአጭር አማርኛ ሲገለጽ “እራስን ማጥፋት” ይባላል፡፡ ወጣቶቹ ይህን እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው ልኂቃኑ በየቀኑ የሚናገሯቸው መርዛማ ቃላት ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ለዚህ ሁሉ የፖለቲካ መበላሸት የመጀመሪያ ተጠያቂው ሥልጣን ፈላጊ የኦሮሞ ልኂቃን ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በውስጥ የመወሰን ችግር የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሄ የኔ ግምት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድረግ በሚችሉት ልክ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ከውነዋል ብዬ አላስብም፡፡
ግዮን፡- መንግሥት ማንነት ተኮር ግድያዎችን ማስቆም ያልቻለው ለምድነው? በተለይ ወለጋን በመሳሰሉ አካባቢዎች ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው በተደጋጋሚ ሲጨፈጨፉ ችግሩን መቆጣጠር ለምን ተሳነው?
ክንፉ፡- ግድያውን በደንብ ማስቆም ይቻል ነበር፡፡ እኔም ከፍ ሲል የውሳኔ ችግር ብዬ ያነሳሁት ይኼን የመሰለው ነገር ነው፡፡ ዩጎዝላቪያም ኾነች ሶቭየት ሕብረት ቋንቋን መሠረት ያደረገ አወቃቀር ይዘው መጨረሻቸው መበታተን ነው የኾነው፡፡ እኛም ሀገር የዘር ፖለቲካን ምርጫው ያደረገ መንግሥት አምባገነን መኾን ይኖርበታል፡፡ አምባገነን ማለት ሕግን በኃይል ማስከበር ማለት ነው፡፡ በዘር ፖለቲካ ሀገር ማስተዳደር ካስፈለገ ዴሞክራሲን ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲና የዘር ፖለቲካ ፈጽሞ አብረው መሄድ የማይችሉ በመኾናቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዴሞክራሲና በአንባገነን መሐል ላይ ኾነው የሚያጠፉትንም ሊያጠፉ የተዘጋጁትንም ዝም በማለታቸው የምናየው ችግር ሊከሠት ችሏል፡፡ መንግሥት አሁን የያዘው እሳት የማጥፋት ሥራ ነው፡፡ እሳት ማጥፋት ጊዜያዊ ሥራ ነው፡፡ መፍትሔ የሚኾነው ግን ወይ የዘር ፖለቲካን ማጥፋት አሊያም መራር ሕግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ ሕጋዊ ሰውነት እስካለው ድረስ ችግሩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡ ለምሳሌ የቤንሻንጉል ክልል ሕገ መንግሥት አብዛኛውን “መጤ” ብሎ መምረጥ መመረጥ እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡
ይኼ ሕገ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ለሕዳጣኑ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥርዓት ይዞ ዴሞክሲያዊ ሥርዓት ማስቀጠል አይቻልም፡፡ በወለጋ በዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ በደርግ ጊዜ ሠፍረው ጫካ መንጥረው ከተማ መሥርተው የሚኖሩ አማሮችን ሀብት ለመውረስ ነው፡፡ ለምሳሌ ከፋ የሚገኙ የትግራይ ሰዎች ላይ እንደዚህ ሲደረግ አይታይም፡፡ “ለምን ወለጋ?” ከተባለ የኦሮሞ ልኂቃን “አማራ ጠላት ነው” ብለው ዒላማ ስላደረጉት ነው፡፡ እኔ ባለፈው የወለጋ ተፈናቃዮችን ሄጄ ስጠይቃቸው “መጀመሪያ መሣሪያችንን የኦሮሚያ ፖሊስ ቀማን፤ እነዚህ ሰዎች ቀን ፖሊስ ማታ ደግሞ ሸኔ ናቸው፡፡ ማታ መጥተው ቤታችን አቃጥለው እኛን ይገድሉናል” ነው ያሉኝ፡፡ ስለዚህ ሸኔ ያለው መንግሥት ውስጥ ነው፡፡ እነርሱ እንደሚነግሩን ከኾነ ሸኔ ያለው የመንግሥት አወቃቀር ውስጥ ነው፡፡ አርሲ ላይ “ሸኔ የኾናችሁ ወጣቶች ኑና መሬት እንስጣችሁ” ሲባል በይፋ ሰምተናል፡፡ መሣሪያና መሬትም ሰጥተዋቸዋል፡፡ ይኽን ጥቅም ለማግኘት 30 ሺህ ወጣት ሸኔን ተቀላቀለ፡፡ ይኼ የሚያሳየው የአስተሳሰብ ክፍተትና አርቆ ያለማየት ችግር እንዳለ ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ አመራሮች መፍትሔ ሳይኾን ችግርን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ተፈናቃዮች እንደሚሉት መሣሪያ ቢሰጣቸው ሸኔን በሁለትና ሦስት ቀን ውስጥ ያለማንም እርዳታ እንደሚያጠፉት ነው፡፡ ችግሩ ግን ሸኔ የኾነው መንግሥት ነው፡፡ መፍትሔውን ስጠይቃቸው ወደዚያ መመለስ እንደማይቻል፣ ነገር ግን እዚያ ያለውን ቀሪ ሕዝብ ወይ መጠበቅ አልያም ወደ አማራ ክልል ማፍለስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ይኼን ያሉት ከዛሬ ስድስት ወር በፊት ነው፡፡ ይኼንን በሚዲያ አስተላልፈናል፡፡ እዚያ የቀረውን ሰው ወይ አልጠበቁት ወይ መሣሪያ አልሰጡት ወይ ከአካባቢው አላወጡት ዝም ብለው አስፈጁት፡፡ ይህ የሚያሳየው የመንግሥትን ችግርና የፖሊሲውን ውድቅነት ነው፡፡ ይህን ለታዘበ ሰው መንግሥት ትልቅ የፖሊሲና የመተግበር ችግር እንዳለበት ይረዳል፡፡
ግዮን፡- የኦሮሞ ልኂቃንን ጉዳይ ካነሳህ፣ ዐዲስ አበባ ላይ ያላቸውን አቋም እንዴት ታየዋለህ? በተለይ አሁን ላይ በየትምህርት ቤቶቹ የሚደረገውን የክልሉ መዝሙርና የባንዲራ ሰቀላ ሂደት እንዴት ታዘብከው?
ክንፉ፡- አንድ ተግባር ሲከወን ጊዜና ሰዓቱን በጠበቀ መልኩ መኾን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አንድ መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግ በሦስት ደቂቃ ውስጥ ካላለቀ ይከሽፋል፡፡ ከዚህ አንፃር ዐዲስ አበባ እንኳን የኦሮሚያ “የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ትሁን” ቢባል ብዙ ግርታ የሚፈጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው አስተሳሰባችንና ሕገ መንግሥቱ ላይ ነው፡፡ ወደ የትኛውም ክልል ሲኬድ ፍተሻ አለ፡፡ የፍተሻ ሥርዓቱ ግን የሀገርነት ባሕሪ ያለው ነው፡፡ ይሄ መዋቅራዊ መፍትሔ እንዲያመጣ ከተፈለገ መጀመሪያ ሕገመንግሥቱ መቀየር ይኖርበታል፡፡ ምክንያት ከተባለ፣ ተሞክሮ ስለከሸፈ፤ የሰውን ሕይወት ዋጋ እያስከፈለ ስለኾነ፤ ሶቭየትንና ዩጎዝላቪያን ያፈረሰ በመኾኑ ነው፡፡ እኛም ሀገር ያ ሳይመጣ በፊት መቀየር ይኖርበታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ካልተቀየረ ግን ችግሮች አሁንም ይቀጥላሉ፡፡ እንደሚሉት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ዐዲስ አበባ መኾኗ፣ ባንዲራ መስቀሉ፣ መዝሙር መዘመሩ፣… በእኔ እምነት ችግር አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን እኔ ችግር የምለው ይህ የተደረገበት ጊዜ ትክክል አይደለም፡፡ ሰው በዘሩ በሚጨፈጨፍበት ጊዜ ላይ ይህን ማድረግ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ዘርን ማዕቀፍ ያደረገ የአስተዳደር ሥርዓት ይዞ ይህን መሰል ተግባር ማከናወን ጥፋቱ ግዙፍ ነው፡፡
ግዮን፡- “ይህ የሚደረገው በተረኝነት ስሜት ነው” የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ምን ትላለህ?
ክንፉ፡- የተረኝነት ስሜቱ በተለይ በታችኛው የሥልጣን እርከን ላይ በግልጽ ይታያል፡፡ በላይኛው የመንግሥት አወቃቀር ላይ ግን ይኼ በግልጽ አይታይም፡፡ ለምሳሌ መሬትን በተመለከተ ያለው ሥርዓት ይህን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ መሬት ወስደው በመሸጥ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ ነው፡፡ ይኼ በዓይኔ ያየሁት ነው፡፡ በተለይ በገጠር ቀበሌዎች በዐዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት አመራሮች በዚህ መንፈስ የተጠመቁ ናቸው፡፡ ይሄ በሕብረተሰቡ ውስጥ የተለየ ስሜትን ፈጥሯል፡፡ ነገር ግን በሚኒስትር ደረጃ ተረኝነት አይታይም፡፡ ይሁን እንጂ የታችኛው አመራር እንዲህ እንዲኾን ያስቻለው የላይኛው አመራር ነው፡፡ ምክንያቱም የላይኛው አመራር ኃላፊነቱን በአግባቡ ቢወጣና በዚህ ዙሪያ ድክመት ባይኖርበት ኖሮ ይህ ችግር አይከሠትም ነበር፡፡
————————ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን፣ ከጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ በሚቀጥለው ዕትም በቅርቡ ስላሳተመው መጽሐፍ ይዘት እና ስለምርቃት ሥነ ሥርዓቱ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስለነበረው ቆይታና ሌሎች ጉዳዮች ያደረግነውን ጭውውት ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡
