Home Uncategorized ልጆች ኦቲዝም እንዳለባቸው እንዴት መገመት ይቻላል?

ልጆች ኦቲዝም እንዳለባቸው እንዴት መገመት ይቻላል?

ልጆች ኦቲዝም እንዳለባቸው እንዴት መገመት ይቻላል?

(መላኩ ብርሃኑ)

ኦቲዝም እጅግ በርካታ ምልክቶች አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል ግን የሚከተሉት ስምንት ባህሪዎች የኦቲዝም ቀይ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ አንድ ልጅ እነዚህ ስምንት ምልክቶች የሚታይበት ከሆነ በአብዛኛው ኦቲዝም ሊኖርበት እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

እያንዳንዱ ህጻን እድገት ይለያያል፡፡ ነገር ግን በህጻናት ዕድገት ሁሉም ህጻን ሊያልፍባቸው የሚገባ ወሳኝ የሚባሉ የዕድገት ደረጃዎች (development milestones) አሉ፡፡ እነዚህ ደረጃዎች ጤናማ የልጆች እድገትን ለመመዘን ይረዳሉ፡፡ የህጻናቱ በእድሜያቸው ሊኖራቸው ከሚችል የዕድገት ደረጃ ዘግየት ማለት የኦቲዝም ማስጠንቀቂያ ቀይ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡

እነዚህ ቀይ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች “ቋንቋ፣ ማህበራዊ ክህሎት እና ድግግሞሽ ያለውና ያልተለመደ ባህሪ” በማለት በሶስት ይከፈላሉ፡፡

  1. የቋንቋ ችሎታን ማጣት
    ልጆች 18 ወር ሞልቷቸው ምንም ቃል የማያወጡ ከሆነ ወይም 24 ወራት ሞልቷቸው ቢያንስ ሁለት ቃላትን አቀናጅተው መናገር የማይችሉ ከሆነ ፣

ብዙ ህጻናት በ18 ወራቸው ቢያንስ 10 ቃላትን ያወጣሉ፡፡ 24 ወራት ሲሞላቸው ደግሞ ሁለት ቃላትን አቀናጅተው መናገር ይችላሉ (ለምሳሌ አባባ መጣ፣ ውሻ ሄደ)

  1. የሚፈልጉትን ነገር በጣታቸው ማመልከት የማይችሉ ከሆነ ወይም በአካላዊ ገጽታቸው ስሜታቸውን መግለጽ ሲያዳግታቸው

ወደሚፈልጉት ነገር በጣት ማመልከት በህጻናት እድገት ውስጥ ወሳኝና ምንም ቃላት ሳይጠቀሙ ስሜትና ፍላጎትን መግለጫ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ህጻናት መጀመሪያ አንድ ነገር ሲፈልጉ በሁለቱም እጃቸው ወደዚያ ነገር ያመለክታሉ፡፡ ቀስ በቀስ እያደጉ ሲመጡ ግን ወደሚፈልጉት ነገር በጣታቸው ማመልከት ይጀምራሉ፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ በፊትና በአካላዊ ገጽታ ያለንግግር ሃሳባቸውን መግለጽም ይችላሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን አንዱ የኦቲዝም ምልክት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

  1. ለስም ጥሪ ምላሽ መስጠት አለመቻል፣

ህጻናት አንድ አመት ሲሞላቸው በስማቸው ሲጠሩ ወደጠራቸው ሰው ይዞራሉ ፣ አለያም የሚጠራቸው ሰው የት እንዳለ በአይናቸው ይፈልጋሉ፡፡ ስማቸው ተጠርቶ ወይም የተለየ ድምጽ ሰምተው ወደዚያ ድምጽ የማይዞሩ ወይም ምንም አንዳልሰማ ዝም የሚሉና የያዙትን ነገር የሚቀጥሉ ህጻናት ግን ኦቲዝም እንዳለባቸው መጠርጠር ይቻላል፡፡

  1. ቀደም ሲል የነበራቸውን የቋንቋ ክህሎት ማጣት (ወደኋላ መመለስ)

የኦቲዝም አንደኛውና ዋናው መገለጫ ባህሪ ህጻናቱ የጀመሩትን የቋንቋ ክህሎት በድንገት ማሳጣቱ ነው፡፡ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው እስከሁለት አመታቸው መናገር ጀምረው የነበረ ቢሆንም በድንገት መናገርና ወደሚፈልጉት ነገር በጣት ማመልከታቸውን መተዋቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህ ወደኋላ መመለስ የሚባለው የኦቲዝም አንዱ መገለጫ ባህሪ ነው፡፡

  1. ማህበራዊ ክህሎትን ማጣትና ዐይን ማየት አለመቻል

የኦቲዝም ህጻናት አንደኛው መገለጫ ዐይን ማየት አለመቻላቸው ነው፡፡ ከአይን ራሳቸውን ያርቃሉ፡፡ በተጨማሪም ከእንግዳ ሰዎች ጋር መቀላቀል አይችሉም፡፡ አንዳንዶች አንደአይንአፋርነት ቢቆጥሩትም ይህ ግን የኦቲዝም አንዱ ምልክት ጭምር ነው፡፡

  1. ነገሮችን አቀናጅቶ የመረዳት ክህሎት ማጣት

ብዙ የኦቲዝም ልጆች እየሰሩ ካለው ስራ ወየም እያደረጉ ካለው ነገር የተለየ ነገር ላይ ማተኮር አይችሉም፡፡ በሌላ አባባል በአንድ ጊዜ ከአንድ ነገር በላይ ትኩረት ማድረግ አይችሉም፡፡ ነገሮችን በትኩረት መስራት አቀናጅቶ መስራት አለመቻል የኦቲዝም መገለጫ ምልክት ነው፡፡

  1. ድግግሞሽ ያላቸው ተግባራት መከወን ወይም ያልተለመዱ ነገሮችን ማድረግ

የኦቲዝም ህጻናት እጃቸውን ወይም እግራቸውን ባልተለመደ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ የማንቀሳቀስ ነገር ይታይባቸዋል ወይም ያልተለመዱ ድምጾችን ያወጣሉ ፡፡ ብዙ ኦቲዝም ያለባቸው ህጻናት ጣቶቻቸውን ወደአይናቸው አስጠግተው ያንሳቅሳሉ ወይም ያጨበጭባሉ ወይም እጆቻቸውን ያውለበልባሉ ወይም በእግር ጣታቸው ይቆማሉ ወይም ይራመዳሉ ወይም በተደጋጋሚ ጊዜ ይሽከረከራሉ ወይም በቆሙበት ይወዛወዛሉ ፡፡ይህንን መሰል ድርጊት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያዘወትሩትና ሊተዉት የማይችል ሲሆን ኦቲዝም አንዳለባቸው ማወቂያ ሌላው ምልክት ነው፡፡

  1. ያልተለመዱ ፍላጎቶች መኖር

ብዙ ኦቲዝም ህጻናት መጫወቻ ካልሆኑ ነገሮች ጋር ያላቸው ቁርኝት ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ ማንኪያ ወይም ፎጣ ወይም ትራስ ወይም ብርድልብስ ወይም በቤት ውስጥ የሚያገኙት አንድ ነገር ከእጃቸው እንዲለይ አይፈልጉም፡፡ ልጆች እንዲህ አይነት ምልክት ሲታይባቸው የኦቲዝም መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡

በአጠቃላይ ልጆች ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች የሚታይባቸው ከሆነ ቀይ ማስጠንቀቂያዎች ስለሆኑ በጊዜ ወደህክምና ባለሙያዎች ጋር ሄዶ ማስመርመርና ኦቲዝም መሆኑ ከተረጋገጠ የሙያ ክህሎት፣ የንግግር ክህሎት፣ የጨዋታ ክህሎትና የባህሪ ማረቅ ህክምናዎችን እንዲከታተሉ ማድረግ ይመከራል፡፡ ነገሮችን እያዩ ችላ ብሎ መዘግየት ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ለበለጠ መረጃ “የኦቲዝም ምስጢሮች” የሚለውን መጽሃፍ ገዝተው ያንብቡ፡፡ የአለም ኦቲዝም ቀንን ከናንተ ጋር መጋቢት 28 በጎልፍ ክለብ እናከብራለን፡፡ አንድ ቲሸርት በ500 ብር በመግዛት ነህምያ ኦቲዝም ማዕከልን ይደግፉ፣ የኦቲዝም ልጆችን ነገ ብሩህ ያድርጉ!
CBE 1000009335308 Nehemiah Autism Center

Melaku Berhanu
Goodwill Ambassador!