Home ነጻ ሐሳብ ሕይወትን በአማራጭ የተሞላች የሚያደርግ የቋንቋ እውቀት

ሕይወትን በአማራጭ የተሞላች የሚያደርግ የቋንቋ እውቀት

ሕይወትን በአማራጭ የተሞላች የሚያደርግ የቋንቋ እውቀት

መታሰቢያ መልአከሕይወት

ቋንቋ ለሰው ልጆች መግባቢያ ከመኾን የዘለለ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ ከመግባቢያ ውጪ ቋንቋ ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ የሰው ልጆችን ኪነጥበባዊ ፍላጎት አገልግሎት ላይ ለማዋል ሊጠቅም ይችላል፡፡ በዓለማችን ከሚነገሩ በሺ የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ሕይወት በአማራጭ የተሞላ እንዲኾን የሚረዱ ቋንቋዎች እጅግ አናሳ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ጥሩ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ካለው ሕይወቱ እጅግ በሰፋ አማራጭ የተሞላ ይኾናል፡፡ እንግሊዘኛ ቋንቋን የሚያውቅ ግለሰብ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የፈለገውን ዓይነት መጽሐፍ ማግኘት ይችላል፣ ፊልም ማየት ቢፈልግ፣ ኢንተርኔት ውስጥ መረጃ ቢፈልግ፣ አንድ ዕቃ አጠቃቀሙን ማንበብ ቢፈልግ በቀላሉ ለመረዳት እና የፈለገውን ለማድረግ ዕድሉ በጣም የሰፋ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ አንድ ወጣት አማርኛ ተናጋሪ ከኾነ መኪና ሹፌር ቢኾን፣ የግንባታ ሠራተኛ ቢኾን፣ ነጋዴ ቢኾን፣ የመስተንግዶ ሠራተኛ ቢኾን በተጨማሪም የሌላ ሞያ ባለቤት ቢኾን በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመሥራት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ከአማርኛ ውጪ ያሉ ሌሎች ቋንቋዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖር ሰው ሰፊ የሕይወት አማራጭ አይሰጡም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን አማራጭ የማይሰጡ ቋንቋዎች ብቻ እንዲናገሩ በማድረግ የልጆቻቸውን የወደፊት ሕይወት ባያጨልሙት ይመከራል፡፡ የቋንቋ እውቀት አንድ ወጣት ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ከሚረዱ መንገዶች ቀዳሚው ነው፡፡ የወለድናቸው ልጆች ትምህርት ቤት የምንልካቸው ጥሩ ስብዕና ይዘው እንዲያድጉ እንጂ ቋንቋ፣ ባሕል ብቻ እንዲማሩ አይደለም፡፡ ለዚያ ካልኾነ የሚማሩት ልጆች ካደጉ በኋላ ወላጆቻቸውን ወቃሽ መኾናቸው አይቀርም፡፡

አንድ ወጣት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ በመላው ኢትዮጵያ አይሱዙ መኪና እየነዳ ሕይወቱን ለመምራት የግድ አማርኛ ተናጋሪ መኾን አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ወጣት አማርኛ እንዳይናገር መከልከል አይሱዙ መኪና እንኳን እየነዳ ሠርቶ እንዳይኖር መከልከል ነው፡፡ አንድ ሠው ወደ አረብ ሀገር ሄዶ ሠርቶ መኖር ከፈለገ አረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ መኾንና አለመኾን እጅግ ትልቅ ዓይነት ልዩነት አለው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ላለፉት 30 ዓመታት የትም አፍሪካ ሀገር የሌለ የቋንቋ መንግሥት ለመፍጠር በመሥራታችን በችግር ውስጥ ለመኖር ተገድደን እንጂ ምንም ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ከኛ በቀር አንድም ቋንቋን መሠረት አድርጎ የተመሠረተ ሀገር የለም፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች የቀኝ ገዥዎችን ቋንቋ እንደመግባቢያ በመጠም (ከአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በስተቀር) ተግባብተው በሰላም እየየኖሩ ነው፡፡ ወደፊት በምንኖርባት ዓለም ከእንግሊዘኛ ቋንቋ የበላይነት የሚኾን ሌላ ቋንቋ የማይኖር በመኾኑ ብልህ ወላጅ የወለዳቸውን ልጆች እንግሊዘኛ ተናጋሪ እንዲኾኑ ያደርጋል፡፡

እስቲ አንባቢያንን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ አንድ ኦሮምኛ ብቻ የሚናገር ሰው ሕይወቱ እንኳን በዓለም ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ አማራጭ የተሞላ ይኾናል ወይስ አይኾንም? ሌሎችም ቋንቋዎች ብቻ የሚናገር ሰው ሊኖረው የሚችለው አማራጭ ምንድነው? አንድ ወላጅ ልጁን የሚጠቅመውን ቋንቋ ብቻ ማስተማር (ማለት እንግሊዘኛ ብቻ በማስተማር) የልጁን ሕይወት በአስተማማኝ የተሻለ እንዲኾን ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎቻችን ካለፉት ባለሥልጣናት ምንም ባለመማር እነሱ የሠሩትን ስሕተት እየደገሙ ነው፡፡ የኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ሆዳቸውን ብቻ ሲያሳብጡ ልጆቻቸው ኮርተው ተከብረው የሚኖሩባትን ሀገር ሳይፈጥሩ ተዋርደው ተወገዱ፡፡ የደርግ ባለሥልጣናት ጡረታ ሲወጡ እንደ ዜጋ ተከብረው የሚኖሩባትን ሀገር ሳይፈጥሩ እነርሱም ልጆቻቸውም በውርደት እና በድህነት ለመኖር ተገደዋል፡፡ የህወሓትን ባለሥልጣናትም ምንም ሊነካቸው የማይፈለግ መንግሥት ተፈጥሮ እንኳን የግድ ተመልሰን ሥልጣን ካልያዘን በማለት ሲፋለሙ በየጥሻው በየገደሉ ወድቀው ቀሩ፡፡ አሁን የሀገሪቱን ሥልጣን የተቆጣጠሩት ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ልክ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት መሪዎች የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ብቻ በማሠብ ልጆቻቸው የማይኖሩባት እነሱ በጡረታ ዘመን በሰላም የማይኖሩባትን ሀገር እየፈጠሩ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ምን ያህል ከደረጃ በታች ያሉ ስብስቦች ሀገራችንን እየመሯት እንደኾነ በግልፅ ያሳያል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አሁንስ ምን እያደረግን ነው? የሚቀጥለው መሪ ያው እንደተለመደው እየዋሸ የባጥ የቆጡን የሚቀባጥር መሪ ይሆናል ወይስ ቢያንስ የተሻለ መሪ እንዲመጣ እየሠራን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንዱና ትልቅ ችግር አቅም ያለው፣ በገንዘብ የተጠናከረ፣ በቂ ምሁራንን ያቀፈ ስብስብ የሌለ መኾኑ ነው፡፡ ሥልጣን እጃቸውን ያገቡ ኃይሎች ምንም የሚፈሩት ነገር በማጣቸው ነው በሀገር እና በሕዝብ ላይ ይህንን ሁሉ ወንጀል የሚፈፅሙት፡፡ ገንዘብ በእጁ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ዕለት ዕለት ኑሮውን ከማሳደድ እና ሆዱን ከማሳበጥ ሌላ ሀገር እንዳለው እንኳን መገንዘብ የተሳነው ስብስብ ነው፡፡ በእጁ ላይ ያለ ሀብትና ንብረት ልክ እንደ ህወሓቶች በአንድ ጀንበር ሊጠፋ እንደሚችል መገንዘብ የተሳነው ስብስብ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት ከኃይለሥላሴ ጀምሮ ያሉ ባለሥልጣናት ልጆቻቸው እንኳን ሠርተው የሚኖሩባት ሀገር መፍጠር አለመቻል በተከታታይ በመጡ በሁሉም ባለሥልጣናት ላይ የታየ ተግባር ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚያጠናክር አንድ አጭር ታሪክ ልጥቀስ፤ ይህንን ታሪክ ያጫወተኝ ሰው በአንድ ወቅት አንድ ሴት ጓደኛ ይይዛል፡፡ ይህችን ጓደኛ ይዞ አብረው በጓደኝነት ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወንድየው ፍቅረኛውን አንድ ጥያቄ ይጠይቃታል፡፡ ይህንን ጥያቄ የተጠየቀችው ወይዘሪት አባቷ ከሥልጣን የወረደ የደርግ ባለሥልጣን የነበረ በመኾኑ ፍቅረኛዋን ልትደብቀው ብዙ ሞክራ ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን እነዚህ ፍቅረኛሞች አብረው ሲሂዱ ሌላ ሰው ያያቸው እና ይህ ሌላ ሰው ሌላ ቀን ወንድየውን ብቻውን ሲያገኘው “ለመኾኑ አንድ ቀን አብራህ ስትሄድ የነበረችው ሴት ምንህ ነች?” ብሎ ሲጠይቀው፤ “ፍቅረኛዬ ነች” ብሎ ይመልስለታል፡፡ ከዚያ ይህቺ ሴት የማን ልጅ እንደኾነች እና የደርግ ባለሥልጣኑን ስም ሁላ ይነግረዋል፡፡ በኋላ ይህ ፍቅረኛ ያለው ወንድ ሳይቀየማት ሌላ ጊዜ ሲያገኛት ያባቷን ታሪክ ከሌላ ሰው እንደሰማና የአባቷን ማንነት ለመደበቅ መሞከርዋ በጣም ገርሞት ሳይለያዩ አብረው መቀጠል እንደቻሉ አጫውቶኛል፡፡

ይህ ታሪክ የሚያስተምረን ወደ ሥልጣን የሚመጡ ስብስቦች ሁሌም ያለ እውቀት ሥልጣን እየያዙ ሀገር ሲያተራምሱ የዜጎችን ሕይወት ለመከራ ሲደርደርጉ ቆይተው በመጨረሻ ከሥልጣን ሲወገዱ ልጆቻቸው “እኔ የእገሌ ልጅ ነኝ” ማለት አንኳን እያሳፈራቸው ሕይወታቸውን ሁሉ እየተሳቀቁ ይኖራሉ፡፡ የሚገርመው ከኃይለሥላሴ አስከ ዶ/ር ዐብይ ያሉ ግለሰቦች ይህንን ስሕተት በቅብብሎሽ እየደገሙት መጡ እንጂ ሊያርሙት ሞክረው አያውቁም፡፡ በርዕሱ እንደተጠቀሰው ባለሥልጣናቱ በክልላቸው ያሉ ወጣቶችን የበለፀገ ሕይወት እንዲኖሩ የሚረዳቸውን የቋንቋ ማንነት እንዲይዙ ተግተው መሥራት ሲገባቸው ሕዝቡን “በአፍ መፍቻህ ቋንቋ ብቻ ተናገር” እያሉ የራሳቸውን የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራሉ፡፡ ነገ ከሥልጣን ሲወገዱ (ከላይ እንደተጠቀሰችው ሴት ወይዘሪት የአባቷን ስም እንኳን ለመጥራት እንዳፈረችው) የውርደት ሕይወት ለመኖር ይገደዳሉ፡፡

የበለፀገ ሕይወት የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የቤት አሰራር፣ የመጓጓዝ ወዘተ የሚቀይር ነው፡፡ የበለፀገ ሕይወትን ለመኖር ደግሞ የበለፀገ ቋንቋ ተናጋሪ መኾን ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ቻይና አድጋ እጅግ የበለፀገች ሀገር ሁናለች፤ ነገር ግን ቋንቋቸው በመላው ዓለም የሚነገር ቋንቋ አይደለም፤ ቻይናዎች ቋንቋቸውን ማበልፀግ ባይችሉም ከቀሪው ዓለም ጋር መግባባት ስለማይችሉ እንግዚዘኛ ቋንቋ መማር እንዳለባቸው ገብቷቸዋል፡፡ አዲስ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ትውልድ ለመፍጠር እየሠሩ ነው፡፡ የበለፀገ ቋንቋ ማለት የግድ ሁለት ባሕሪ ሊኖረው ይገባል፡፡ የመጀመሪያው ቋንቋው የማግባባት ብቃቱ በጣም ከፍተኛ መኾን አለበት፡፡ ሁለተኛ በመላው ዓለም የተስፋፋ መኾን አለበት፡፡ አሁን ላይ ይህንን መስፈርት የሚያሞላ ቋንቋ እንግሊዘኛ ብቻ ነው፡፡