በአዲስ አበባ ከተማ ትክክለኛ ያልሆነ ሕገ-ወጥ የፋይዳ መታወቂያን በማተም ለግለሰቦች በሚሰጡ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርያስላሴ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ‘የፋይዳ መታወቂያን በአጭር ጊዜ እንጨርስላችኋለን’ በማለትና በአሰራሩ መሠረት መመዝገብ እንደማያስፈልግ በመግለጽ፤ ወዲያውኑ ፎቶ አንስተው ትክክለኛ ያልሆነ መታወቂያን በመስራት የሚሰጡ አካላት መኖራቸው ተረጋግጧል።
ይህንን ሕገ-ወጥ ሥራ በሚሰሩ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ እንዲሁም የሚቀርቡ ጥቆማዎችን መሠረት አድርጎ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ግን ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ መለያ ቁጥሩን ብቻ በመያዝ መገልገል እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዜጎች ግዴታ የታተመውን የፋይዳ መታወቂያ መያዝ እንደማይጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ የሀሰተኛ ሰነድ ስርጭት አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በዚህ ረገድ ገና መሠራት የሚገባው ከፍተኛ ሥራ መኖሩን ጠቁመዋል።
