መጪውን የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚበይነው ብሪክስ!      

Date:

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በበርካቶች ዘንድ አሜሪካ የምትኩራራበትን ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚንድ፣ ዶላርን ከተራ ወረቀት የሚያስቆጥር ባላንጣ ‹‹ሳይመጣባት አይቀርም›› የሚለው ድምጽ ጎላ እና ገፋ ብሎ መሰማት ጀምሯል፡፡ ይኽ ባላንጣ ሥሙ ‹‹ብሪክስ›› ይሰኛል፡፡ ‹‹BRICS›› የሚለው ቃል አምስቱ አባል አገራቱ ከሥያሜአቸው የመጀመሪያ ፊደል ወስደው ያበጁት ቃል ነው፡፡ (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ)፡፡

ሀገራቱ እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ ተከታታይነት ያለው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ማድረግና መቧደን የጀመሩት አንዳች ፖለቲካዊ አጋርነት አልያም መደበኛ የሆነ የንግድ ትስስር ስላላቸው ሳይሆን ተፅእኖ ፈጣሪ የኢኮኖሚ ዞን የመገንባት ብቃት አለን ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ በዚህም በዶላር ላይ ያላቸውን ጥገኝነት በመቀነስ የዶላርን ዋጋ ዝቅተኛ ማድረግ እንችላለን ባይ ናቸው፡፡ ይህን ሐሳብ ፈር ቀዳጅ ኾነው ከፊት የሚመሩት ደግሞ አሜሪካ ርዕዮተ ዓለማዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ባላንጣ ናቸው የሚባሉት ቻይና እና ሩሲያ ናቸው፡፡ ለዚህ አስረጂ የሚኾነው በአንድ ወቅት ቭላድሚር ፑቲን ‹‹እኛም ልክ እንደዶላር ያለ የቡድኑ አባላትን የመገበያያ ገንዘቦች ያካተተ አዲስ አለም አቀፍ የመጠባበቂያ ገንዘብ እንፈጥራለን›› ብለው የነበሩ መኾናቸው ነው፡፡

ሩሲያ የጂኦፖለቲካል ጥቅሙ እንዳለ ሆኖ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባቷ መነሾ በምዕራቡ ዓለም ከሚመራው የዶላር ኢኮኖሚ እንድትገለል መደረጓ ቀደም ብላም ስታስበው የነበረውን አዲስ የመገበያያ ገንዘብ የማቋቋምን ሐሳብ የብሪክስ አባል አገራት አጥብቀው እንዲያስቡበት ግድ እንዳላትም ይታመናል፡፡ እዚህ ላይ የሩሲያ የቀድሞ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ራያብኮቭ ‹‹አንዳች ከምዕራቡ ዓለም ጫና ነፃ የሆነ ሌላ አማራጭ የኢኮኖሚ ዞን በመፍጠር በዶላር ላይ ያለንን ጥገኝነት መቀነስ አለብን›› የሚለው ንግግራቸው በአባሪነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ሌላኛዋ የስብስቡ መሪ ቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ደግሞ በአንድ ወቅት ለአባል አገራቱ አድርገውት በነበረው ንግግር ‹‹የዓለም ኢኮኖሚ ነጻ እንዲሆን መሥራት፣ በጋራ የንግድ ነፃነትን በማመቻቸት እና በማስተዋወቅ፤ አዲስ ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት መፍጠር እና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አለብን›› ማለታቸው ዶላር እንዳንገሸገሻቸው ማሳያ ነው ሲሉ ነገሩን የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ እንደሚታወቀው ቻይና የዶላርን የበላይነት ደጋግማ ስትወቅስ ነው የኖረችው፡፡ ኾኖም የቻይና ፖሊሲ አውጪዎች ይኽንን የዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ገንዘብ በተመለከተ መላ ለማበጀት የሚረዳ ሁነኛ ዕቅድ ማዘጋጀት ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ይኽ በመኾኑ ደግሞ የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ የአሜሪካ ዶላር ጥንካሬ ለቻይና ንግድ እና ቴክኖሎጂ እንቅፋት መኾኑ ታየ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ቻይና አማራጭ የኢኮኖሚ ዞን በመፍጠር ከዶላር ጋር ለመለያየት የወሰነችው፡፡    ነኖሐሖ

ሌላኛዋ ሀገር ሕንድ ደግሞ ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር ያላትን ተቃውሞ የተመለከቱት አሜሪካኖች አገሪቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላት አጋር እና በኢንዶ-ፓስፊክ ቀጠና ደግሞ ወዳጅ እንደኾነች ቢያምኑም፣ ዳሩ በፖለቲካ ዓለም ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም በሚለው፣ ሕንድ ሩሲያና ቻይና ዶላርን ዋጋ ለማሳጣት የሚሄዱበት መንገድ፣ ባለፉት ዓመታት ሕንድ በአሜሪካ ዶላር ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ የሚያስችሏትን መንገዶች ማማተር መጀመሯ ስብስቡን ለመቀላቀል ገፊ ምክንያት ኾኗታል፡፡ እ.አ.አ በ2012 የሕንድ የንግድ ሚኒስቴር የሕንድ የመገበያያ ገንዘብ ሩፒን በሌሎች አገራት ውስጥ አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን ሀሳብ የሚያጤን አንድ ግብረ ሀይል አቋቁመው ነበር፡፡ ታዲያ የምንዛሪ ተለዋዋጭነት እና አሜሪካ በሩሲያ እና በኢራን ላይ እንደጣለችው የነዳጅ ማዕቀብ ያሉ የጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች እና ቻይና ዮዋንን ዓለምአቀፍ የመገበያያ ገንዘብ ለማድረግ ያቀደችው እቅድ ህንድንም ሩፒን ለአለም አቀፍ ግብይት ልጠቀምበት የሚል አቋም እንድትይዝ አስችሏት የኋላ ኋላ የስብስቡ ቀንደኛ አባል ሀገር ለመኾን በቅታለች፡፡

ኾኖም ይህ በዶላር ላይ ያላታን ጥገኝነት ለመቀነስ የምትሄድበት ጎዳና ለህንድ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 86 በመቶ የሚሆን አገሪቱ ከውጭ የምታስገባው ምርት የዶላር ጥገኛ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 በመቶ ያክሉ ከአሜሪካ የሚመነጭ ነው፡፡ በተጨማሪም ሕንድ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት 86 በመቶ የሚሆነው በአሜሪካ ዶላር የሚሸጥ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አሜሪካ የምትገዛው 15 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ በመኾኑም ሕንድ ምንም እንኳ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ በማሳጣት ሂደቱ ላይ ትልቅ የሚባል ሚና መጫወት ባትችልም የአካባቢያዊ ገንዘቦች አለምቀፍ መገበያያ እንዲሆኑ የተጀመረውን እንቅስቃሴ መደገፏ አይቀሬ ኾኗል፡፡

ሌላኛዋ ሀገር ብራዚል ወደ 9ዐ በመቶ የሚሆነው ኤክስፖርቷ የሚወራረደው በዶላር ቢኾንም በሚያሳዝን ሁኔታ አሜሪካ ከዚህ ሁሉ የብራዚል ኤክስፖርት የምትገዛው 17 በመቶውን ብቻ መኾኑ፣ እንግዲህ እንዲህ ያለው የጥቅም አለመመጣጠን የብራዚልን ፖሊሲ አውጭዎች ብሪክስን እንዲደግፉ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ይነገራል፡፡ በአንድ ወቅት ፕሬዘዳንቷ ሉላ ዳ ሲልቫም ‹‹እኛ ብሪክስን የፈጠርነው ለመከላከል ሳይሆን ለማጥቃት ነው›› የሚል ኃይለ ቃል መናገራቸው ብራዚል በዶላር ምክንያት ያቄመው አንጀቷን ለማሻር አንዳች መላ እንደምትፈልግ ማሳያ አድርገው ብዙዎች ይጠቅሱታል፡፡

የአፍሪካ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የኾነችው ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ በኩል እ.አ.አ 2011 በብሪክስ ስብሰባ ላይ ባሰማችው አቋም የደቡብ አፍሪካ በዶላር ምንዛሬ ተለዋዋጭነትና አለመረጋጋት ላይ ሥጋቷን ገልጻለች፡፡ እንደ አማራጭም እንደ ራንድ ያሉ ገንዘቦችን በአካባቢያዊ የመገበያያ ገንዘቦች ላይ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት አመላከተች፡፡ ይኽንኑ ሐሳብ እ.አ.አ በ2013 የብሪክስ ስብሰባ ላይ ደግሞ በማንሳትም ንግድን በአካባቢያው ገንዘብ ለማቀላጠፍ የሚያስችል ፕሮቶኮሎ እንዲዘጋጅ እስከመጎትጎት ደርሰዋል፡፡ በዚህ መልክ ሀገራቱ ብሪክስን በመቀላቀል ከአሜሪካ ዶላር ጥገኝነት ለመላቀቅ አዲስ ፍኖት መትረዋል፡፡

ብሪክስን ለመቀላቀል ኢትዮጵያን ጨምሮ እስካሁን 44 ያህል ሀገራት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ዋነኞቹ ደግሞ አርጀንቲና እና ኢራን ናቸው፡፡ ‹‹አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል በማሰብ አሁን ደግሞ ምን ላድርግ በምትልበት ወቅት፣ ኢራን እና አርጀንቲና ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል›› ሲሉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ተናግረው ነበር። እአአ በ2022 ደግሞ አልጄሪያ በይፋ ብሪክስ ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርባለች። አልጄሪያ ላቀረበችው ጥያቄ ቻይና እና ሩሲያ ድጋፍ መስጠታቸውን በፍጥነት አስታውቀዋል። ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ቱርክ እና ግብፅ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ። ጥያቄ ከማቅረብ ውጭ እስካሁን ቀዳሚዎቹን አምስት አገራት ለመቀላል የቻለ አገር እስካሁን የለም። ብዙዎች ታዲያ የብሪክስ ሀገራት መዳረሻ የጋራ የመገበያያ ገንዘብ በመፍጠር ብቻ የሚገደብ አይደለም በማለት፣ የዓለምን የኃይል ሚዛን ለመገለባበጥም አንዳች ግልጽ እየኾነ የመጣ ውጥን መኖሩን ያነሳሉ፡፡ በተለይም ኢራንና ሳውዲ ዐረቢያ ስብስቡን የሚቀላቀሉት ከኾነ ነገሩ ልክ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣሊያን እና ካናዳን እንዳካተተው የቡድን 7 አባል ሀገራት ያለ ወደረኛ ኃይል ኾኖ የመውጣት እና የዓለምን ፖለቲካል ኢኮኖሚ መበየን የሚችልበትን መዶሻ ሊጨብጥ ይችላል ተብሏል፡፡ ‹‹ቡድን ሰባት›› የተሰኘው የምዕራቡ ዓለም ስብስብም፣ ለጊዜው አምስት አገራትን ካቀፈው እና በርካታ ሀገራት ለመቀላቀል ጥያቄ እያቀረቡለት ካለው ‹‹ብሪክስ›› ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥመውም እንዲህ ያሉ የአገራት ስብስቦችን በትኩረት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...