የዱባዩ ግዙፍ የሆቴልና የእንግዳ ተቀባይነት አስተዳደር ድርጅት “ዘ ፈርስት ግሩፕ ሆስፒታሊቲ” ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በተፈራረመው ታሪካዊ ስምምነት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በይፋ መግባቱን አስታውቋል።
በናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ የወደፊት ሆስፒታሊቲ ጉባኤ ላይ የተፈረመው ይህ ስምምነት፤ በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በጅማ፣ በላንጋኖ እና በደንቢ የሚገኙ 10 የሆቴልና የሪዞርት ፕሮጀክቶችን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ያለመ ነው።
ፕሮጀክቱ በራሱ ብራንድ የሚተዳደሩ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የ”ማሪዮት” (Marriott) ሆቴል ስም የሚንቀሳቀሱ ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን ያካተተ ሲሆን፤ ግንባታቸው ተጠናቆ ስራ ሲጀምሩም በአጠቃላይ 1,140 የሚሆኑ ዘመናዊ የመኝታ ክፍሎችን ለዘርፉ የሚያበረክቱ ሲሆን ከ2026 እስከ 2031 ባሉት ዓመታት ውስጥ በደረጃ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ይጠበቃል።
