ትክክለኛ አኀዛዊ መረጃ ለማግኘት ቢያዳግትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከመቶ ሚልዮን እንደበለጠ ይታወቃል፡፡ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ውስጥ ከ80-85 በመቶ የሚሆነው በግብርና የሚተዳደር ነው የሚለው የተለመደ ገለጻ ዛሬም ብዙ የተቀየረ አይመስልም ፤ የሀገሪቱ የወጪ ምርቶች ያው እንደበፊቱ የግብርና ምርቶች መሆናቸውም እንዲሁ፡፡ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) መጠንም ከቀድሞው ከፍ እንዳለ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በሌላ በኩል የገንዘብ ግሽበትና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ከዋነኛ የማህበረ-ኢኮኖሚ ችግሮች መካከል ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ አውታሮች ረገድ በአሁኑ ወቅት ምናልባት ትንሽ ሲንቀሳቀስ የሚታየው በግለሰቦች የሚደረግ ግንባታና የሪል ስቴት ልማት ነው፡፡
የአገልግሎት ዘርፉን በተመለከተ መቼም የማይቀሩት የምግብና መጠጥ እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፉ እየተንገታገቱ አሉ፡፡ የግል ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥር አድጓል፡፡ ከሚልዮን አልፈው በቢልዮን ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ ቢመጣም በየትኛውም ሀገር የማህበረ ኢኮኖሚ ሚዛንን የሚጠብቀውና ወሳኝ ክፍል የሆነው የመካከለኛው መደብ የሕብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ እየቀነሰ መምጣቱን፣ ባለፉት ዓመታት ከድህነት መውጣት የሚባለው ነገር ቀርቶ ብዙ አዳዲስ ደሀዎች መፈጠራቸውን መናገር ይቻላል፡፡
ዛሬ ዛሬ ብዙ ሰዎች በተለይም በወጣትነትና በጎልማሳነት እድሜ ክልል ያሉ ሰዎች በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተው ቢታዩም በተለይ የአነስተኛውና የመካከለኛው ነጋዴ እንቅስቃሴ እንደተዳከመ ማንም የሚያስተውለው ነው፡፡ ከግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ ከበፊቱ ማደጉና በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ በመጠን ረገድ መጨመሩ በሌላ በኩል ደግሞ የጥሬ ገንዘብ እጥረት መኖሩ የማይካድ ነው፡፡ እዚህ ጋር ገንዘብ ማለት የቁጥር ጉዳይ ሳይሆን የመግዛት አቅም (ፐርቼዚንግ ፓወር) ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት አይገባም፡፡ ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የራሳቸው አሉታዊ ሚና ቢጫወቱም የውጪ ምንዛሪ እጥረት ዛሬም ያልተፈታ ሁነኛ መፍትሄ ያላገኘ ችግር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ብድር ካለባቸው ሀገሮች መካከል አንዷ መሆኗና ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደአይ ኤም ኤፍ አይነት ተቋማት ጋር ውዝግብ ውስጥ እንዳለችም ይታወቃል፡፡ በርግጥ በቅርቡ አንዳንድ የሀገሮችን የኢኮኖሚ ደረጃ የሚተነትኑ ተቋማት የኢትዮጵያን ብድር የመክፈል አቅም በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሰጥተው የነበረውን ደረጃ እንዳሻሻሉ ሲገለጽ ቢደመጥም ከፍተኛ የውጪ እዳ አሁንም ከዋነኞቹ የኢኮኖሚው ፈተናዎች መካከል ነው፡፡ ቀደም ባሉት አመታት ኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብም ይሁን በቴክኒካዊ እርዳታ መልኩ የምታገኛቸው ድጋፎች አሁን ብዙም የሌሉ መሆኑ ነገሮችን ይበልጥ አወሳስቧል ማለት ይቻላል፡፡ በቢሮክራሲና በህብረተሰብ ጠባይ ረገድ ጉቦ (ሙስና) ህጋዊ ሆኗል ሊባል በሚችል መልኩ የተንሰራፋ ትልቅ ችግር መሆኑ፣ ከግል ድርጅት እስከ ሀይማኖት ተቋማት ድረስ በመቶ ሺህዎች ጉቦ ከፍሎ ስራ መቀጠርና በሆነ የሀላፊነት ደረጃ ላይ መሾም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ሌብነትና ዝርፊያ ዛሬ የጀመረ ባይሆንም ነውርነቱ ግን የቀረ ይመስላል፡፡ ሽፍታና ዘራፊ እንደድሮው ጫካ መመሸግ አይጠበቅበትም ፤ ከተማ መሀል ሆኖ ሰው በማገት በሚልዮኖች ክፍያ መጠየቁ እየተለማመድነው የመጣነው አዲሱ የዝርፊያ መንገድ ሆኗል፡፡ በአንድ ወቅት በሕብረተሰቡ ዘንድ ክብርን የሚያሰጡት መማርና ማወቅ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው የማመን ፣ እንደመምህርነትን የመሰሉ ሙያዎችም አማራጭ ያጡ ሰዎች የሚሰማሩባቸው እየሆኑ መምጣታቸው ማንም የሚያስተውለው ሀቅ ነው፡፡ የዛሬው የግዮን የርዕሰ አንቀጽ መልዕክታችንም እነዚህን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ከተጣባን ሕብረተሰባዊ ጠባይና ዝንባሌ ጋር በወጉ መርምረን ምን ያህል ሁሉን አቀፍ ትክክለኛ የልማት መንገድ ላይ ነን የሚለውን መጠየቅ ይኖርብናል የሚል ነው፡፡ መልካም ሳምንት!
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 219 ሕዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም
