‹‹ሥልጣን ይልቀቁ ፤ ፓርላማውም ይበተን››

Date:

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለጠ/ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥያቄ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባሳለፍነው ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም አካሒዷል፡፡ በጉባዔው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከምክር ቤት አባላት በ2015 የፌደራል መንግስት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡ ጥያቄዎቹም በሠላምና ደህንነት፣ በልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አጠቃላይ ተግባራት ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በምክር ቤቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረቡት መሀመድ አህመድ፤  “ህወሓት አሁንም ከዉድቀቱ ያልተማረ መሆኑ እና ዛሬም የትግራይ ክልልን እና መላዉ ኢትዮጵያን መልሶ ጦርነት ዉስጥ ለመክተት እየተንቀሳቀሰ እንዳለ አሁንም ይነሳል። ወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ ማብራሪያ ይሰጥበት?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ሌላው የምክር ቤት አባል አዳነ ተሾመ፤ “ዜጎችን በማገት በሚሊዮን ገንዘብ መጠየቅ የዜጎችን ሰላም ወጥቶ መግባት ጥያቄ ዉስጥ ከትቶታል። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ምን እየተሰራ ይገኛል? ልዩ ሀይሎችን ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ማደራጀት ላይ በተለይም በአማራ ክልል የተፈጠረዉን ችግር መንስኤዉን ለይቶ ለመፍታት ምን ታስቧል? እንደ አገርስ በኹሉም ክልሎች ያለዉ የመልሶ ማደራጀት ስራዉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?” ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

የአብን እና የምክርቤቱ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ “ሙሉ አማራ ክልል አዲስ የጦርነት ቀጠና ሆኗል፤ ከፊል ኦሮሚያ በተመሳሳይ የጦር ቀጠና ናቸዉ። ከ 200 ሺሕ በላይ ሰዎች በመንግሥት ቤታቸዉ ፈርሶ ሜዳ ላይ ወድቀዋል። እንደ ብልጽግና ሹማምንት አባባል ህጋዊ ደሃ ተደርገዋል። በሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በጦርነቱ እና በማንነት ጥቃት ተፈናቅለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለዚህ ሁሉ ቀዉስ ዋነኛ ተጠያቂው የብልጽግና መንግስት እና የእርሶ (የጠ/ሚኒስተሩ) የወደቀ አመራር ነዉ።” ብለዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አክለውም፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ ኢኮኖሚዉ ታሟል፣ ወጣቶች አገራቸዉ ዉስጥ ተስፋ በማጣታቸው ስደትን ምርጫቸዉ አድርገዋል፣ ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ይታገታሉ፣ ብልጽግና መራሹ ፓርቲ አገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር ማዉጣት ስለማይችሉ ስልጣኖን ለጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያስረክቡ ፓርላማዉንም እንዲበትኑ እና ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ” ሲሉ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በሰሜኑ ክፍል ትግራይ ፣ አማራና አፋር ፋይዳ ባልነበረው ጦርነቱ መድቀቃቸውን የተናገሩት ዶ/ር ደሳለኝ፣ ይህ ጦርነትም ‹‹የብልፅግና እና የህወሓት የሥልጣን ጦርነት›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች የም/ቤት አባላትም የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ አሰጣጥን ለማስቀረት የተሠራውን ሥራ፣ ሙስና ለመዋጋት የተቋቋመው ኮሚቴ ያከናወነውን ተግባራት፣ በሱዳን የሚኖሩ ዜጎችን በሚመለከት ምን እየተሰራ የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርበዋል።

በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመንግስት የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የብድር እዳ ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት(ጂዲፒ) የሚይዘው ምጣኔ 59 በመቶ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል። ይሁንና በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ በተከናወኑ ስራዎች የእዳ ምጣኔ ከጂዲፒው አንጻር ወደ 38 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሆና ያለባትን ብድር በመክፈል ላይ ትገኛለች ብለዋል። በቀጣይ ሦስት ዓመት ውስጥ የእዳ ምጣኔውን ከ30 በመቶ በታች ዝቅ ለማድረግቅ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹እንደተባለው የህወሓት እና የብልፅግና ችግር ከነበረ አብኖች (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ) የት ነበራችሁ?›› ሲሉ ጠይቀዋል። ‹‹እዚህ ላይ ‹ለምን አታስታርቁም ነበር› የሚል ጥያቄም ይነሳል›› ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ‹‹አስታራቂ ሲጠፋ ነው ግጭት የሚበዛው›› ብለዋል። ‹‹ድግሱን ስናፋፋም ቆይተን አሁን ጉዳዩን ለተወሰነ ወገን መስጠት ተገቢ አይደለም›› ያሉት ጠቅይላይ ሚኒስትሩ ‹‹ግጭቱን ማንም ይጀምረው ማንም ጥሩ አይደለም፤ ጥፋት ነው ብሎ መቀበል›› እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ መሆኗና ለዚህም ተጠያቂው ገዢው ብልፅግና ፓርቲና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደቀ አመራር በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸውን እንዲለቁና ስልጣናቸውን ለሚቋቋም ጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ፤ ፓርላማውም ተበትኖ ለምርጫ መንገድ እንዲጠርግ በሚል ለተጠየቀው ጥያቄ ደግሞ ‹‹እንዲህ ያለው ንግግር ለዛሬ ፌስቡክ፣ ለዛሬ ዩትዩብ ጥሩ ነው ፤ አቶ እንትና እንትና እንዲህ አደረጉ ለሚለው ለፌስቡክ ፍጆታ ጥሩ ነው ለትውልድ እና ሀገር ግን አይጠቅምም›› ብለዋል። ‹‹ቆም ብለን እኛ ማናየውን በማሳየት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመውን ሃሳብ ብናቀርብ ጠቃሚ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።

‹‹በኢኮኖሚ፣ በሰላም እና በአንዳንድ ጉዳዮች የቀረቡትን የምንወስዳቸውና የምንሰራባቸው እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም›› ያሉት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ‹‹በጥቅሉ ኢትዮጵያ ጨለማ ውስጥ ናት ከተባለ ግን ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት በኢኮኖሚ 3ኛ ናት፣ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ናት ፣ ትላልቅ ተቋማትን እየገነባች ያለች ሀገርናት የሚል መልስ ሆኖ ያልቃል›› ሲሉ ተናግረዋል። ምርጫን በተመለከተ ‹‹ምርጫ ይካሄድ የሚለውን ሃሳብ በጣም አደንቃለሁ ፤ ብዙ ጊዜ የተቃዋሚዎች ችግር ምርጫ አይፈልጉም ዝም ብላችሁ ልቀቁና እኛ እንያዝ ነው የሚሉት ፤ አሁን ምርጫ ይደረግ የሚለው በጣም ጠቃሚ ነው ግን ሶስት ዓመት መታገስ አለብን›› ብለዋል።

‹‹በየሳምንቱ ምርጫ ስለማይደረግ ፤ ሶስት አመት ታግሰን ያለንን ሃሳብ ይዘን ቀርበን እኛም ይዘን ቀርበን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈርደውን ፍርድ በፀጋ መቀበል ነው ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት የፈረደውን ፍርድ አልተቀበልኩምና አሁን ፓርላማው ፈርሶ ምርጫ ካልተካሄደ አሁንም ፈርሶ ቢካሄድና ቢመረጥ ካልተመረጥን ይቀጥላል ጉዳዩ በየሁለት አመቱ ምርጫ ለማካሄድ አቅም ስለሚያንሰን በተቀመጠው መንገድ በ5 ዓመት እናደርጋለን›› ብለዋል። ‹‹ምርጫ ሲደረግ ያሉ ሀሳቦች ለህዝብ ቀርበው እኛ ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ካላገለገልንና ካልጠቀምን ህዝቡ በምርጫው ሲቀጣን እጅ ስመን፣ ባንስምም እጅ ነስተን እናስረክባለን ፤ እስከዛ መታገስ ጥሩ ነው ፤ ፍርዱን ለህዝብ እንተወው›› ሲሉ መልሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ጋር በተያያዘ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ህዝብ በመረጣቸው የምክር ቤት አባላት ሲጠየቁ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በመልቀቅ ‹‹ላለው ችግር የመፍትሄው አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ? በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ እንዲሁም በማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማፅዳት እና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ኖት?›› የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር። በወቅቱ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ ‹‹ኃላፊነት መውሰድ ካለብን በጋራ ቢሆን መልካም ስለሆነ ‹ስልጣን ብንለቅ› ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ማለት አስፈፃሚ ብቻ አይደለም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸው ነበር።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...