Home የጣይቱ ገጽ ሥራ ፈጣሪዎች እንደ የሠላም ተዋናዮች ከእየሩሳሌም (ሣራ) ሐረገወይን

ሥራ ፈጣሪዎች እንደ የሠላም ተዋናዮች ከእየሩሳሌም (ሣራ) ሐረገወይን

ሥራ ፈጣሪዎች እንደ የሠላም ተዋናዮች ከእየሩሳሌም (ሣራ) ሐረገወይን

ውድ አንባቢያን፦ በዚህ አምድ ከባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ጀምሮ ኢኒሽየቲቭ አፍሪካ ከሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሆነው “ንግድ ለሠላም” በተሰኘው ፕሮጀክቱ በንግድና ሠላም ዙሪያ አንዳንድ የመወያያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሃሳቦች ማካፈል መጀመራችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ጽሁፍም በሥራ ፈጠራ እና በሠላም መካከል ያሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የሠላም ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ ሰኔ 2017 ያወጣውን ጥናት መሠረት አድርገን የመነጋገሪያ ሃሳቦችን እናነሳለን፡፡

ሥራ ፈጠራ (Entrepreneurship) አገር በቀሉን የንግድ ዘርፍ በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማልማትና ማስፋፋት ይችላል። ጠንካራ አገር በቀል የንግድ ዘርፍ ሠላምን ለመገንባት እና ሠላማዊ ሁኔታን ለማቆየት በቀጥታ እና በተጨባጭ አስተዋፅዖ ሊያደርግም ይችላል። ለምሳሌ፡- በኮሎምቢያ እና በቱኒዚያ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ሰላምን ለማደራጀት እና ለበለጠ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ዘይቤዎች ለመደራደር በንቃት አስተዋፅኦ ማድረጋቸው  ታይቷል።

እ.ኤ.አ. 1990 ዎቹ መገባደጃ ላይ በኮሎምቢያ በፕሬዚዳንት አንድሬስ ፓስትራና አስተዳደር ጊዜ በመንግስት እና በፍዌርዛስ አርማዳስ የኮሎምቢያ አብዮተኞች መካከል በተካሄዱ የሠላም ውይይቶች የግሉ ዘርፍ ዋነኛው ተዋናይ ነበር። ምንም እንኳን እነዚያ ንግግሮች ባይሳኩም፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የንግዱ ዘርፍ በሠላም ግንባታ ውስጥ ያለው ተነሳሽነት  የበለጠ ጠንካራ እና የተራቀቀ ሆኗል።

በሠላም ግንባታ ሂደቶች እና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ላይ አካዳሚያዊ እና ቴክኒካዊ ዕውቀትን ለማራመድ በኮሎምቢያ የንግድ ማህበረሰብ  የተቋቋመው ፈንድሲዮን ሀሳቦች ፓራ ላ ፓዝ የተሰኘው የአሳቢዎች ቡድን መመሥረቱ እንደ አንድ ምሳሌ የሚጠቀስ ነው። በፕሬዚዳንት ሁዋን ማኑዋል ሳንቶስ አስተዳደር በሚመራው እና በቅርብ ጊዜ በተካሄደው የበለጠ ስኬታማ ድርድር የግሉ ዘርፍ አስፈላጊ የድጋፍ ምንጭ ነበር፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የልማት  ፕሮግራም የተደገፈውና የገጠር ሥራ ፈጣሪነትን እንደ አንድ መንገድ በመጠቀም የትጥቅ ግጭቱ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለመደገፍ የተተገበረው መርሃ- ግብርም የድርድሩን ስኬታማነት አጉልቶታል።

በቱኒዚያ በርካታ ትናንሽ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ጨምሮ150,000 ያህል የግል ኩባንያዎችን የሚወክለው የቱኒዚያ የኢንዱስትሪ፣ የንግድ እና የእጅ ሥራዎች ኮንፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. በ2015 የኖቤል የሠላም ሽልማትን ያሸነፈው የቱኒዚያ ብሔራዊ የውይይት ኳርቴት ተፅዕኖ ፈጣሪ አባል ነበር። ኳርቴት ለወራት ከተካሄዱና አገሪቱን ካዳከሙ ማህበራዊ ተቃውሞዎች በኋላ ሁሉን ያካተተ ውይይትን ያቀናጀ ሲሆን ከአብዮት በኋላ የነበረውን የአገሪቱን ሽግግር ወደ ማረጋጋት የመራ ስብስብ ነበር።

የቱኒዚያ የኢንዱስትሪ፣ የንግድ እና የእጅ ሥራዎች ኮንፌዴሬሽን እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2016 በጀመረውና በቱኒዚያ የ2020 ዘላቂ የዕድገት ፕሮግራም በኩል ለመዋቅራዊ ማሻሻያዎች ተሟግቷል። በቱኒዚያ እና በኮሎምቢያ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ተነሳሽነት ሊጨምር የቻለው የዜግነት ኃላፊነት እና የንግድ ፍላጎት ከማህበረሰቡ ፍላጎት ጋር መጣመር በመቻሉ ነበር።

ከዚህ የምንገነዘበው የንግድ ዘርፍ ሥራው ሠላም በሚሆንበት ጊዜ የአገር በቀሉ የግል ዘርፍ እንደ ሕጋዊ የሠላም አደራዳሪ ሆኖ ሊያገለግል መቻሉን ነው።

ሥራ ፈጣሪነት እንደ አንድ ተስማሚ የሥራ መንገድ

ዘላቂ ሠላም ለመገንባት የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል አስፈላጊ አካላት ናቸው፤ነገር ግን ለሠላም በቂ ሁኔታዎች አይደሉም። ከማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት በተቃራኒ እኩል አለመሆን ሲባባስ፣ ማኅበራዊ መገለል እና የኢኮኖሚ እጦት አዙሪት ውስጥ ይገባና ሠላምን ሊያደናቅፍ ይችላል። ከዚህም በላይ እኩል አለመሆን ከማንነት ፖለቲካ ጋር ሲገናኝ የማህበራዊ ትስስሩን በእጅጉ ያዳክመዋል። ስለዚህ በሥራ ፈጠራ ላይ መወሰን ብቻ ሳይሆን ስለ “ተስማሚ ሥራ” ማሰብም አስፈላጊ ነው። በእርግጥ የተባበሩት መንግሥታት ከአጸደቃቸው 17 ዘላቂ የልማት ግቦች መካከል 8ኛው ዘላቂ የልማት ግብ “ ዘላቂ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ሙሉ እና ምርታማ የሥራ ስምሪት እና ለሁሉም ተስማሚ ሥራ” ማስተዋወቅን ይጠይቃል።

የብሮኪንግስ ተቋም የመጋቢት 2017 አጭር መግለጫ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ያሉ የተለያዩ ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ ሞዴል እንዴት ከፍተኛ የሥራ አጥነት እና የኢኮኖሚ መገለል በተለይም በወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል ላይ እንደደረሰ ይመረምራል። ይህንን የሥራ ፍላጎት ደግሞ በመንግሥት ዘርፍ ቅጥር በኩል  በዘላቂነት መፍታት አይቻልም።

በተመሳሳይ  በቅርብ ጊዜ በአልጄሪያ፣ በግብፅ፣ በቱኒዚያ እና በፍልስጤም በተደረገ የዳሰሳ ጥናት  ከ 80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የራስን ሥራ መጀመር ጥሩ የሙያ ምርጫ እንደሆነ ማመናቸውን አሳይቷል። ምንም እንኳን ይህ የሥራ ፈጣሪነት ጉጉት የሚያሳድር ቢሆንም፣ እውነታው ግን በርካታ ሀገራት ለሥራ ፈጣሪነት እንቅስቃሴ ማደግ ምቹ ከባቢ እና ማበረታቻዎች የላቸውም። ይህ ወጣቱ በሚመኘው እና በሚኖሩት ዕድሎች መካከል ያለው አለመመጣጠን የሰውን ልጅ ለስደት እና ላለፉት አሥርት ዓመታት በክልሉ ውስጥ አመፅን ለፈጠረው ተስፋ መቁረጥ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከአዎንታዊ የሠላም እይታ አንጻር፣  በወጣቶች ልማት፣ በማህበራዊ ሥራ ፈጣሪነት እና በሠላምን ዘላቂነት ግንኙነት ላይ የኢኮኖሚክስ እና ሠላም ኢንስቲትዩት ያደረገው ጥናት በአዎንታዊ ሠላም ማለትም ሠላምን የሚደግፍ ጠንካራ የአመለካከት ፣ የተቋማት እና መዋቅሮች መለኪያ እና የወጣቶች ልማት መረጃ ጠቋሚመካከል ጠንካራ ትስስር እንዳለ አእሳይቷል። የወጣቶች አቅም ሊያድግ በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ፣ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የመረጋጋት እና ለሥራ ገበያዎች በተለይም ከግጭት በሚያገግሙ አገሮች ውስጥ የመቋቋም ደረጃን ወደነበረበት ለመመለስ አስተዋፅኦ ያደርጋል።ይህም የሚባለው በሥራ መርሃ ግብሮች እና በሠላም መካከል ቀለል ያለ ወይም ቀጥተኛ ግንኙነትን ለመጠቆም ሳይሆን ሠላማዊ እና ጠንካራ ማህበረሰቦች ከወጣቶች ልማት እና በወጣቶች ከሚመራው ሥራ ፈጣሪነት በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማጉላት ነው።

ወደ ሥራ ፈጣሪነት የሚያተኩሩ የትምህርት እና የሙያ ሥልጠና መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት የወጣት ሥራ ፈጣሪነትን ለማሳደግ አንድ ተጨባጭ ፖሊሲነው ። በሁለተኛ እና በከፍተኛ ደረጃዎች ብቻ የተገደበ ሳይሆን ገና በልጅነት በሁሉም ልጆች ውስጥ የመነሳሳት እና ራስን የመቻል መንፈስ የሚያሰፍን ሙያን ያማከለ ትምህርት መነደፍና መስፋፋት አለበት።

ፈጠራን ለማስተማር እና ለማበረታታት፣ እንዲሁም ወድቆ ለመነሳት ከፍተኛ የሥነ- ልቦና ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም እንደ የመማር እና የፈጠራ ሂደት አካል ሆኖ በትምህርት ሥርዓቱ መጠናከር እና መታቀፍ አለበት። በበርካታ ማህበረሰቦች እንደታየው ሥር የሰደደ ስጋትን የማንገስ እና ውድቀትን የመፍራት ባህል ለሥራ ፈጠራ ባህል ማደግ አስተዋፅኦ ማበርከት አይችልም፤ ግለሰቦችም ገንቢ በሆነ ሁኔታ ግጭትን ጨምሮ መከራን ለመቋቋም የሚያስፈልጓቸውን የሕይወት ክህሎቶች እንዲያዳብሩ አይረዳም።

ማህበራዊ ሥራ ፈጠራ እና ዘላቂ ሠላም

በግጭቶች የተጎዱ ማህበረሰቦች ብዙውን ጊዜ በዝቅተኛ የማህበራዊ ትስስር ይሰቃያሉ፡፡ በብሔር፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ወይም በፖለቲካ መስመሮች በከፍተኛ ሁኔታ ይከፋፈላሉ። ነገር ግን ምንም ዓይነት የማኅበራዊ እና የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩ፤ የአንድ ሰው ኑሮን በማሻሻልና በኢኮኖሚ የመበልፀግ ፍላጎቱ ላይ በተለያዩ ቡድኖች መካከል የጋራ መግባባት ይኖራል። ልዩነቱ “እንዴት?” የሚለውን በመመለስ ላይ ነው፡፡

የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነት በዚህ የጋራ ፍላጎት ላይ በመመስረት ለቡድን ማኅበራዊነት መድረኮችን መፍጠር ይችላል፤ ይህም ለማህበራዊ ትስስር እና ዘላቂ ሠላም መመስረት የሚያስችል ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ፡- ጁሱር በሊባኖስ ውስጥ መጪው የሶሪያ የንግድ ባለቤቶች ትውልድ ጦርነቱ ያፈረሰውን እንዲገነቡ ለማስተማር የታለመ የሥራ ፈጠራ ፕሮግራም ነው ። በተመሳሳይ፣ የፔሬስ የሠላም እና ፈጠራ ማዕከል እና የአይሁድ- አረብ ኢኮኖሚ ልማት ማዕከል በጋራ ለእስራኤላውያን እና ለፍልስጤም ነጋዴዎች የንግድ ሥራ ችሎታ ሥልጠና እንዲሁም ሙያዊ እና የግል ግንኙነቶችን ለመፍጠር እድሎችን ይፈጥራሉ። እነዚህ ተነሳሽነቶች የኑሮ ዘይቤን እና  አዲስ ችሎታዎች እና ግንኙነቶች በመገንባት ረገድ ለተፈናቀሉ ሰዎች፣ ለአስተናጋጁ ወይም ለአልፎ ሂያጅ ማህበረሰቦች የሥራ ፈጠራን አስፈላጊነትና የሚኖረውን አስተዋፅኦ ያጎላሉ።

በእንደዚህ ዓይነት ሥራ ፈጣሪ ስትራቴጂ ላይ የተመሰረቱ ግን ዋና ዓላማቸው “ትርፍን ማበልፀግ ሳይሆን የተወሰኑ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግቦችን ማሳካት፣ እንዲሁም በማህበራዊ መገለል እና ሥራ አጥነት ችግሮች ላይ አዳዲስ መፍትሄዎችን የማምጣት አቅም ያላቸው የንግድ ተቋማት፣ በተለምዶ “ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች” ተብለው ይጠራሉ። ምንም እንኳን የ “ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪነት” ትርጓሜዎች አከራካሪ እና በተወሰነ ደረጃ ትክክል ባይሆኑም፣ በሥራ ፈጣሪነት እና በሠላም መካከል ያለውን ግንኙነት በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ለማገናዘብ ጠቃሚ ሆኖ ይታያል።

ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪነት ብዙውን ጊዜ በዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍል ደረጃ ይከናወናል፡፡ በዚህም የማህበረሰብ ፍላጎቶች እና የግጭት ነጥቦች ላይ የበለጠ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖር ያስችላል። ከላይ በተዘረዘረው መሠረት፣ ነባርም ሆኑ አዲስ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚደግፉ እና የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች የሚፈለጉት የግል ሥራን ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ከፍ ለማድረግ እና ለማህበረሰቡ መስተጋብር አዳዲስ መድረኮችን ለመፍጠር ጭምር ነው። ባለፉት ጥቂት ዓሥርት ዓመታት፣ ለማህበራዊ ሥራ ፈጣሪነት የተሰጠው ትኩረት በእጅጉ አድጓል።

በተለይም በወጣቶች የሚመራው የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪነት ብዙ አዎንታዊ ውጤቶች ሲኖሩት ተስተውሏል፡፡ ማህበራዊ ትስስርን በማሳደግ፣ በወጣቶች መካከል ክህሎቶችን በማስተላለፍ እና በማንቃት በማንነት ቀውስ፣ በመራራቅ እና መብትን በመነፈግ ዙሪያ ያሉ አስፈላጊ ጉዳዮችን መፍታት ችሏል። እንደ አንድ የንግድ ማህበረሰብ ክፍል ሥራ ፈጣሪዎች በአስቸጋሪ አካባቢዎች ውስጥ እንኳን በጽናት እና በፍጥነት በማደግ፤ አካባቢያቸውን፣ ማህበረሰባቸውን እና አገራቸውን የበለጠ ጠንካራ እንዲሆኑ በማድረግ አስደናቂ ጥንካሬን አሳይተዋል፤ በማሳየትም ላይ ናቸው።

ፍትዊ የንግድ ምዳር ለሠላም ግንባታ

ፍትሃዊ እና ተወዳዳሪ የሆነ የንግድ ሁኔታ የመልካም እና ፍትኃዊ የኢኮኖሚ አስተዳደር አንዱ ጠቋሚ ሲሆን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ሥርጭት ዕድልን ይጨምራል። ለንግድ ተስማሚ ያልሆኑ ደንቦች ያላቸው አገሮችም የሁከት መንሥዔ እና ሁከት አባባሽ የሆነውን ከፍተኛ የገቢ አለመመጣጠን ሊገጥማቸው ይችላል። ደንቦች በሥራ ላይ ካልዋሉ ወይም በገለልተኛነት ካልተተገበሩ አለዚያም ሆን ተብሎ ኢ- ፍትኃዊነት ሲሰፍን፣ የካፒታል ተደራሽነት እና ንግድ ለመጀመር የሚያስፈልጉት ፈቃዶች በጥቅመኛ አውታሮች፣ በዘመድ አዝማድ እና በጉቦ ላይ ጥገኛ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው።

ስለዚህ የንግድ ከባቢን ለማሻሻል የታለሙ ፖሊሲዎች “የበለጠ ውጤታማ፣ ተጠያቂነት እና አካታች ተቋማትን የመገንባት” ዘዴ ሊሆኑ ይችላሉ። ዘላቂ ሠላም የመገንባት እና ጤናማ የንግድ አከባቢን የመፍጠር ዓላማዎች በተለይም ከንግድ ደንቦች አቀራረጽ እና አፈፃፀም ጋር የሚዛመዱ የአስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታትን ያጠቃልላል።

የኢኮኖሚክስ እና የሠላም ኢንስቲትዩት ጤናማ የንግድ ሁኔታን “የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ጥንካሬ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ሥራን የሚደግፉ መደበኛ ተቋማት መኖር ሲሆን ይህም ከስምንቱ የአዎንታዊ ሠላም ምሰሶዎች አንዱ ነው” በማለት ይገልጸዋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ አስተያየት የቁጥጥር ሥርዓቶች መኖር ለንግድ ሥራዎች ተስማሚ እንደመሆናቸው የንግድ ተወዳዳሪነት እና ኢኮኖሚያዊ ምርታማነት በጣም ሠላማዊ ከሆኑ አገሮች ጋር የተቆራኙ መሆናቸው እሙን ነው።

መደምደሚያ

በሥራ ፈጠራ እና በዘላቂ ሠላም መካከል በርካታ የመተሳሰሪያ ነጥቦች አሉ። በጥቅል በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ፤ ሥራ ፈጣሪነት ግጭት ቀስቃሽ ወይም አባባሽ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን እንደመፍቻ መንገድ ሊታይ ይችላል። በግጭት፣ በሠላምና በኢኮኖሚው መካከል ያለውን ውስብስብ ግንኙነት በመረዳት የሥራ ፈጠራን እንደ ግጭት መፍትሄ አድርጎ ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ በሥራ ፈጣራ እና በሠላም መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ተለዋዋጭነት ማጠንከር ላይ ማተኮር የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

አራት እንደዚህ ያሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ከላይ በዝርዝር ተዳሰዋል፡፡ እነኝህም፡- አካታች አካባቢያዊ የግሉ ዘርፍ መፍጠር፣ ተስማሚ ሥራን ማስተዋወቅ፣ ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪነትን መደገፍ እና ጤናማ የንግድ አካባቢን ማጎልበት ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በሠላምና በሥራ ፈጠራ መካከል ያለው መገነባባት በከፍተኛ ሁኔታ አውድ ተኮር በመሆኑ በጥሩ ልምዶች ብቻ ማጠቃለያ መግለጫ መስጠትን አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ምንጭ፦ ዓለም አቀፍ የሠላም ኢንስቲትዩት፣ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2017