ሥጋት ያጠላበት የሰሜኑ የሰላም ቀጋ!

Date:

ለሁለት ዓመታት በከባድ ጦርነት የከረመው የሰሜን ኢትዮጵያው ፖለቲካ አሁን ላይ የሰላም ዘንባባ ያጠላበት ይመስላል፡፡ “የሞተ ተጎዳ” እንዲሉ፣ የያኔዎቹ አዋጊዎች እና ፍጅት ቀስቃሾች ዛሬ ተቃቅፈው ናፍቆታቸውን ተገላልጸዋል፡፡ “ሽብርተኛ፣ ጁንታ፣ ፋሺስት፣…” ወዘተ ስድቦች ሳይቀር ኋላ ኪስ ገብተው ሙገሳ እና መወድሱ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ሂደቱ ይበል የሚያሰኝና እርቅ መውረዱ ደስ ቢያስብልም ሰላም መውረዱ ላይቀር አንድ ሚሊዮን ሰዎች ጭዳ ኾነው መቅረታቸው “አይ ፖለቲካ” ብለን ከንፈር መምጠጥን እረፉ ሊለን የሚሞክር ሰው መኖር የለብንም፡፡ የኾኖ ኾኖ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የትግራይና የፌደራል መንግሥት ጦርነት ጦሱን፣ መዘዙን፣ እና የጸብ እሳት አሎሎውን ወደ አማራና ኤርትራ የወረወረ ይመስላል፡፡

ይህን የሚያረጋግጥልን ደግሞ “ሰላም እንዲሰፍን እና በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ በአስቸኳይ ይውጡ” ሲል የትግራይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መጠየቁ ነው። ጉባኤው ባወጣው መግለጫ “አሁንም በተደረሰው የሰላም ስምምነት የትግራይ ሕዝብ ሰላም እንዳያገኝ በግፈኞቹ በኤርትራ ኃይሎች እና ፋኖ በሚባሉ የአማራ ታጣቂዎች እየተፈፀሙ ያሉ ዝርፍያዎች፣ ግፎች እና የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች አሳዝኖናል” ብሏል። በተጨማሪም “ግፈኞቹ በሚያደርሱት ግፍ ምክንያትም የሃይማኖት ተቋማት ያለ አማኞች፣ አማኞችም ያለ ሃይማኖት ተቋማት እየቀሩ ነው” ሲል የጉባኤው መግለጫ አመላክቷል። ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ፍትሕ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለፀው የትግራይ ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መግለጫ “በሕዝባችን ላይ የተፈፀሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በገለልተኛ አካላት በአስቸኳይ ተጣርተው ሕዝባችን ፍትሕ ሊያገኝ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

ይህ የሃይማኖት ጉባኤው መግለጫ የሚያመለክተው ከፍ ሲል እንደተገለጸው ቀጣዩ ቀውስና ውጊያ ከማን ጋር ሊኾን እንደሚችል ነው፡፡ ፖለቲከኞች የዘለሉትን ጉዳይ የሃይማኖት ጉባኤው አሳስቦት ይህን መሰል መግለጫ ማውጣቱ እየተደረገ ያለው የሰላም ስምምነት ፍሬው ምን ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችልም ጠቋሚ ነው፡፡ ምንም እንኳን ፖለቲከኞች የለበጣ ፎቶ እየለቀቁ ለሕዝብ አጀንዳ ሊሰጡት ቢሞክሩም ጉዳዩ በቀላሉ የሚቋጭ አለመኾኑ ግን አያጠራጥርም፡፡

በእርግጥ  የፌደራል መንግሥትም ቢኾን ያለማቅማማት እየተንደረደረ አንዴ ናይሮቢ ሌላ ጊዜ መቀሌ እየሄደ ከህወሓት እግር ሥር የሚለጠፈው ወዶ አለመኾኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን “FITCH” የተባለው ተቋም ኢትዮጵያ ያለችበት ፋይናንሻል ሁኔታ ሉዓላዊነቷን የሚፈታተን እንደኾነ አመላክቶ ነበር። እንደተቋሙ ገለጻ ለአንድ ሉዓላዊ ሐገር CCC- አይሰጥም። ኢትዮጵያ ግን ካለፈው ዓመት ጀምራ ያለችው CCC- ላይ ነው። ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ኢትዮጵያ የጀመረችውን “የሰላም ስምምነት” 100% ተፈፃሚ ከማድረጓ በተጨማሪ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች መቸብቸብ ከቻሉ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ቀውስ መታደግ ይቻላል ብለው ያምናሉ። በዚህ በኩል መንግሥት ቴሌ፣ ባንክና አየር መንገድን ለመቸብቸብ መዘጋጀቱን ካሳወቀና መሸጥ ከጀመረ ከዓመት በላይ ኾኖታል፡፡ ቅሉ ግን ከሐገሪቱ የፖለቲካና ፀጥታ አለመረጋጋት አንፃር ገዢዎች በረከሰ ዋጋ እሱንም ፈራ ተባ እያሉ ስለኾነ እየገዙ ያሉት የሚፈለገውን ያህል እዳ ሊሸፍንና ሊከፍል አልቻለም።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ወደ አሜሪካ አቅንተው ልዩ ልዩ ብድራት ቃል ቢገባላቸውም አንዳቸውም ከሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት በፊት ተፈጻሚ እንደማይኾኑ ተጠቁሟል፡፡ ለምሳሌ የአውሮፓ ሕብረት ለኢኮኖሚው ማንሰራርያ ድጋፍ ሊለግሰው የነበረውን $1 ቢልዮን ዩሮ የሰላም ስምምነቱ ጫፍ ካልደረሰ እንደማይሰጥ አስታውቋል። እንደ “FITCH” ገለጻ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት 2023 ብቻ በእዳዋ ላይ የ$1.6 ቢልዮን ዶላር ወለድ ይጨምርባታል፡፡ ያ ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ ላይ ያለው ገንዘብ አሁን ካለውም ዋጋ የበለጠ ዋጋ እያጣ ይሄዳል ማለት ነው። ይህ ሁለገብ ኢኮኖሚያዊም ይሁን ፖለቲካዊ ጫና መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተው ባይታጣም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ በሚከት ዓይነት መንገድ የፖለቲካ ቁማር በዜጎች ላይ ለመሥራት መሞከር ግን አዋጪ አይኾንም፡፡ ይህ ከህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው “የሾላ በድፍን” ስምምነት ሄዶ ሄዶ ቀውስ እንዳያመጣ መጠንቀቅ ያስፈለልጋል፡፡ ሰላም በማንም የሚጠላ ተግባር ባይኾንም ጥንቃቄ እንደሚያሻው ግን መካድ አይቻልም፡፡ አሁን ላይ አማራ ላይ የዘር ፍጅት ለመሥራት ያቀዱ ኃይሎችን አደብ ማስገዛት የተሳነው መንግሥት ነገ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አይከብደውም፡፡

በተለይም አማራ ላይ “የአማራ ሸኔ፤ ጽንፈኛ ፋኖ” ወዘተ እያሉ የመግደያ ቅጽሎችን ማመቻቸት ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ህወሓትን ላይ እንደሀገር ዘመቻ ተደርጎ አማራ ብቻውን ጠላት ተደርጎ የሚሳልበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ የሰላም ስምምነቱ “ፋሺስት” የሚለውን የስድብ ስም ከመንግሥት ላይ እንደስነሳለት ሁሉ በፋኖ ላይ የሚወረወረውንም የጥላቻ እና የበሬው ወለደ ስድቦችን ሊያስቆምለት ይገባል፡፡ ካለዚያ ግን መቀሌና አዲስ አበባ ብቻ በመምከር እርቀ ሰላም መፈጸም አይቻልም፡፡ ባሕርዳርና ሰመራም የስምምነቱ አካል ሊኾኑ ይገባል፡፡ ያ ካልኾነ ግን የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሷል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ባላ ሁኔታ የፕሪቶሪያው ሥምምነት እየተጣሰ ያለው በህወሓት ብቻ ሳይኾን በፌደራል መንግሥቱም ጭምር ነው። የፌዴራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት ህወሓት ላይ ያገኛቸውን “concessions waive” የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን እያሳየ ነው።

እንደሚታወቀው ህወሓት በአንድ እጁ ሰላም በሌላው ነውጥ የሚቀናው ድርጅት ነው፡፡ በዚህም ስለሰላም እየደሰኮረ ከሰሞኑ የአገው ሸንጎ የሚባሉ ታጣቂዎችን በመሳሪያ እንየደገፈ እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ። የአገው ሸንጎ የሚባሉት ካሁን በፊት የህወሓትን ዓላማ የሚያስፈፅሙ እንደነበሩ ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ሰሞኑን ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ድጋሚ ወደ ሰቆጣ ተፈናቅለዋል። ህወሓት ትጥቁን በዚህ መልኩ ለፌደራሊስት ሀይሎች በመስጠት ትጥቁን ለማቆየት እና ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ሰሞኑን 13 ተሽከርካሪዎች በራያ በኩል ከመቀሌ ታጣቂዎችን አመላልሷል። 23 መድፎችንም በተመሳሳይ አንቀሳቅሷል። በራያ ኦፍላ ወረዳ ኮረም ዙሪያ ሰሞኑን ለብልፅግና መንግሥት መረጃ ትሰጣላችሁ የተባሉ ሰዎች ታግተው ተወስደዋል፤ የተገደሉም አሉ።

በተመሳሳይ በጎንደር የሚገኘው የህወሓት ተላላኪ የኾነው የቅማንት ቡድንም ተዘውታሪ የኾነ የፖለቲካ መሣሪያነቱን ቀጥሎበታል፡፡ የህወሓትን ዓላማ ለማስፈጸም ሲል ጎንደርን የወንበዴዎች መናኸሪያ አድርጓታል፡፡ ሰሞኑን በርካታ የጎንደር ክፍል ሀገር ከተሞች ከፊል ጎንደር ከተማን ጨምሮ ያለመብራት እንዲከርሙ ተገደዋል፡፡ የዚህ እኩይ ዓላማ ዋና ተዋናይ ደግሞ ተላላኪው የቅማንት ቡድን እንደኾነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ በኩል ወደ ትግራይ በገፍ የሚገባው እርዳታ በመቶሺህ ለሚቆጠሩ የአፋርና የአማራ የጦርነት ሰለባዎች ግን አይደርሳቸውም፡፡ ይህ እራሱን የቻለ የፖለቲካ ሸፍጥ ነው፡፡ በጥቅሉ መንግሥት ወደ ልቦናው ተመልሶ ነገሮችን እያጤነ ቢሄድ መልካም ይኾናል፡፡ ከህወሓት ጋር የሚደረገው ግልፅነት የጎደለው ድርድር ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለባቸውን የሕዝብ አጀንዳዎች ለህወሓት እና ለጠላቶች አሳልፎ አሳልፎ መስጠት እንዳይኾን መጠንቀቅ ይጠበቅበታል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ሥልጠና አከናወነ

ኩባንያችን ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመተባበር...

የኔታንያሁ ድንገተኛ ማስጠንቀቂያ እና የቢሊዮን ዶላር የጋዝ ሚስጥር!

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከታሪካዊቷ የግብፅ ምድር የሚሰማው...

ኤርትራ ሠራዊቷን በአስቸኳይ ከግዛቷ እንድታስወጣ እና ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች

የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጣሯቸዋል ካላቸው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንዲወጣ እና...

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች ቁጥሩ ከ5.46 ሚሊየን በላይ መድረሱን ገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2018 አ.ም የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀሙን...