
ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያን የተመለከቱ ሦስት ዐበይት ጉዳዮች የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ኾነው ሰንብተዋል፡፡ ቀዳሚው ሩሲያ ወደ ዩክሬን የሚያመሩ መርከቦችን በተመለከተ በሰጠችው ማስጠንቀቂያ የስንዴ ዋጋ መናሩ ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ፑቲን በ’ብሪክስ’ ጉባዔ ላይ እንደማይሳተፉ ደቡብ አፍሪካ ያስታወቀችው ዜና ነው፡፡ ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ የቫግነር ተዋጊዎች ወደ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ መግባታቸው ነው፡፡ ሁሉንም አጀንዳዎች እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን፡፡
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ወደቦች የሚያመሩ መርከቦችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፏን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የስንዴ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ሩሲያ እነዚህን መርከቦች እንደ ወታደራዊ ኢላማም ሊቆጠሩ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያም ነው ያስተላለፈችው። በዚህ ሳምንት በጥቁር ባህር በኩል እህል ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለማጓጓዝ ከሚያስችለው ስምምነትም እንደወጣች ሩሲያ አስታውቃለች። ሩሲያ በእቃ ጫኝ መርከቦች ላይ ለሚደርስ ጥቃት ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ እያቀደች ነው ሲሉም የዋይት ሃውስ ቃለ አቀባይ ከሰዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ካገኙ አገራቸው ወደ ስምምነቱ በአፋጣኝ እንደምትመለስም ተናግረዋል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የሩሲያን የግብርና ባንክን ከዓለም አቀፉ የክፍያ ስርዓት ጋር ማገናኘት አንዱ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን የወደብ ከተማ ማይኮላይቭ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል። በኦዴሳ ወደብም ላይ እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ የአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ሩሲያ በጠቀለለቻት ክሪሚያም በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በደረሰ ጥቃት አንዲት ታዳጊ መገደሏን የአካባቢው ባለስልጣን ተናግረዋል። በኦዴሳ ወደብ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን አስመልክቶ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሩሲያ ሆን ብላ የእህል ወጪ ንግድ መሰረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲሉ ከሰዋል። ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በዚህም ተጋላጭ አገራትን ለበለጠ አደጋ ጋርጣለችም ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ በጥቁር ባህር አካባቢ ያሉ ሌሎች አገራትም የእቃ ጫኝ መርከቦች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ማለፍ እንዲችሉ ጣልቃ መግባት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
“ሐምሌ 12፣ በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ በጥቁር ባህር በኩል ወደ ዩክሬን ወደቦች የሚያመሩ መርከቦች የጦር መሳሪያ ጫኝ መርከቦች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ” ሲልም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አትቷል። “እነዚህ መርከቦች ከኪየቭ አገዛዝ ጎን ቆመው በዩክሬን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑም ይቆጠራሉ” ሲል አክሏል። ይህንም ተከትሎ በአውሮፓ የአክሲዮን የገበያ ልውውጥ የስንዴ ዋጋ ረቡዕ 8.2 በመቶም ጨምሯል። በዚህም አንድ ቶን የስንዴ ዋጋ 219. 78 ዩሮ እንዲሁም የበቆሎ ዋጋም 5.4 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል። የአሜሪካ የስንዴ ገበያም 8.5 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል። ይህም ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የታየ ከፍተኛ ጭማሬ በሚልም ተመዝግቧል። የዩክሬን የግብርና ሚኒስትር ማይኮላ ሶልስኪ እንዳሉት በጥቃቱ 60 ሺህ ቶን ያህል እንደወደመ እንዲሁም የእህል ወጪ ንግድ መሰረተ ልማትም መጎዳቱን ነው። ሩሲያ ከእህል ስምምነቱ በወጣች በሰዓታት ውስጥ ነው የዩክሬንን ወደቦች ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው።
በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በሚቀጥለው ወር ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲመጡ ጠብቆ የበቁጥጥር ስር የዋመዋል ሐሳብ በሩሲያ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው ብለው መናገራቸው የሳምንቱ ዐበይት አጀንዳ ነበር፡፡ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚፈለጉት ፑቲን ከሩሲያ ከወጡ በስምምነቱ ፈራሚ አገራት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ቢጠበቅም፣ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ስምምነት ፈራሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፑቲንን ለማሰር መሞከር በሩሲያ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው የሚሆነው ሲሉ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ይህንን ያሉት ቭላድሚር ፑቲን የተጋበዙበት ዓለም አቀፍ ስብስብ የሆነው የብሪክስ አገራት ጉባኤ በአገራቸው ሊካሄድ ሳምንታት ሲቀረው ነው። የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ፑቲን ከሩሲያ ምድር ወጥተው ወደ የትኛውም የዓለም ክፍል ከሄዱ በተገኙበት ይታሰሩ ይላል። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ስትሆን፣ ተከሳሹን በመያዝ የመተባበር ግዴታ አለባት። ይሁን እንጂ ደቡብ አፍሪካ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተቀብላ ታስፈጽማለች ተብሎ አይጠበቅም። አገሪቱ የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከዚህ ቀደም ሳትፈጽም ቀርታለች።
የደቡብ አፍሪካ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ዲሞክራቲክ አሊያንስ ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚመጡበት ጊዜ እንዲታሰሩ ባለሥልጣናትን ለማስገደድ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል። የፍርድ ቤት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ይህንን ጉዳይ በፍጹም እንደማይደግፉት ነው። “ደቡብ አፍሪካ የፕሬዝዳንት ፑቲንን እስር ለማስፈጸም ግልጽ ችግር አለባት” ብለዋል። “የሩሲያን ፕሬዝዳንት ለማሰር መሞከር ጦርነት ማወጅ መሆኑ ግልጽ ነው። ከሕገ መንግሥታችን ጋር በሚጣረስ መልኩ በሩሲያ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ነው” ብለዋል ራማፎሳ።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ግጭት እንዲያበቃ የሁለቱን አገራት መሪዎች ካነጋገሩ የአፍሪካ አገራት መካከል ራማፎሳ አንዱ ናቸው። ይህንን የሰላም ጥረት በሚቃረን መልኩ ፑቲንን ለማሰር መሞከር ግን መዘዙ የከፋ ነው ብለዋል። ባለፈው ወር የአፍሪካ ልዑካን ሩሲያን እና ዩክሬን ለማደራደር ጦርነቱን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱት ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካም። የተባበሩት መንግሥታት በሩሲያ ላይ ያወጣውን የውሳኔ ሐሳብ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት አልተቀበሉትም ነበር።
በሦስተኛ ደረጃ የዜና ማእከላት ሽፋን የነበረው ጉዳይ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያው ቫግነር ቅጠረኛ ቡደን ተዋጊዎች ወደ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ የመግባታቸው ዜና መሰማት ነው። ከቫግነር ጋር ግንኙነት ያለው መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ተዋጊዎች ትናንት ዕሁድ ወደ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ መግባታቸውን ገልጿል። የቡድኑ አባላት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የጥበቃ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሕዝበ ውሳኔው ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ፎስቲን-አርቻንጌ ተውዴር ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር ስለመቻላቸው ውሳኔ ይሰጥበታል። ቫግነር ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። እራሱን ‘የግል ኩባንያ’ ነኝ በሚል የሚገልጸው ቡድኑ፤ ከመካከላኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በተጨማሪ በአፍሪካ ከ10 ባላነሱ አገራት ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል አልያም ተሰማርቶ ነበር።
ሊቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን ቫግነር ከተሰማራባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ነው። ይህ የሩሲያ ቅጠረኛ ቡድን ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ከሩሲያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ቁልፍ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። ይሁን እንጂ የቡድኑ መሪ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ አመጽ ከቀሰቀሰ በኋላ፣ በዩክሬን ያለው ተጽእኖ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን አሜሪካ ገልጻለች። በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ ቀስቅሶ ሩሲያን ለ24 ሰዓታት ትርምስ ውስጥ ከቷት የነበረው ቫግነር፣ አመጹ ከከሰመ በኋላ መሪው ወደ ቤላሩስ እንዲያመራ ተደርጎ ቡድኑ ደግሞ የከባድ መሳሪያ ትጥቅ እንዲፈታ ሆኗል።
ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ የቡድኑ ተዋጊዎች ክስ ሳይመሠረትባቸው የሩሲያን ጦር መቀላቀል፣ ወደ ቤላሩስ ማቅናት አልያም ትጥቅ ፈትተው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚችሉ በፑቲን አስተዳደር አማራጭ ተሰጥቷቸው ነበር። የቅጠረኛው ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ እንዲያመራ አማራጭ ተሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ የቭጌኒ አሁን መገኛው የት እንደሆነ በትክክል አይታወቅም። ቅዳሜ ዕለት የወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቫግነር ቅጠረኛ ቡድን አባላት ከሩሲያ ወደ ቤላሩስ ገብተዋል። ምንጭ፡- ቢቢሲ አማርኛ