ሱዳን ስለምን ቤኒሻንጉልን?

Date:

ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ መከፋፈል ሲገጥመን ጠላቶቻችን ለማጥቃት አመቺ ጊዜ ያገኙ እንደሚመስላቸው በተለያዩ ዘመናት የታየ ሀቅ ነው፡፡ የሀገራችን የሩቅም ኾነ የቅርብ ጠላት የምንላቸው ሀገሮች አጋጣሚዎችን ጠብቀው የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማፍረስ እና ሕልውናዋን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ታትረው ይሠራሉ፡፡ በዚህም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት አጎራባች ቅኝ ገዥ ኃይሎች (ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣሊያን) ተክለውብን የሄዱት ጦስና ሰንኮፍ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ እንግሊዝ በቅኝ የያዘቻቸውን ኬንያን፣ ሱዳንን፣ ግብጽንና ሱማሌ ላንድን በኢትዮጵያ ላይ ስታስነሳ ፈረንሳይ ደግሞ በበኩሏ አንዱ የኾነውን የኢትዮጵያን ግዛት ቆርሳ በእቅፏ ሥር በማስገባት ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ በዝባዥ እንድትኾን አድርጋለች፡፡ ጣሊያንም ብትኾን ከጉርብትናም በላይ ወራሪ ኾና በመምጣት በሀገራችን ላይ አድርሳው የነበረው ቀውስ የደም ምሥክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡

እንግሊዝ በጉርብትና ዘመኗ ቀብራው ከሄደችው ፈንጅ አንዱ ከ50 ዓመታት በፊት በእብሪተኛው ዚያድባሬ በኩል ፈንድቶ እልባት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይህ የእንግሊዝ ሴራ የኬንያን መነሻ ያራቀው ቢመስልም ግብጽና ሱዳንን ግን በየጊዜው በኢትዮጵያ ላይ እንዲፏንኑ አስችሏቸዋል፡፡ እንግሊዝ ለዘመናት ዓይኗን ጥላበት የነበረው የጣና ሐይቅ በዓባይ መገደብ እልባቱ እያገኘ ሲመጣ ትናንት የእግሯ መረገጫ የነበሩት ግብጽና ሱዳን የክፋት ሰይፋቸውን በኢትዮጵያ ላይ ለማሳረፍ ተማምለው ተነሱ፡፡ በተለይም ያለፉትን ሦስት ዓመታት ከውስጣዊ ኃይሎች ጋር በመጣመር ኢትዮጵያን ለማፍረስና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመቀራመት ሁለገብ ዘመቻቸውን አጧጡፈውታል፡፡ በዚህም መሠረት ከሳምንታት በፊት አንዳንድ የግብጽ የፖለቲካ ተንታኞች ሱዳንን ተጠቅመው ኢትዮጵያን ከመውረር አልፈው “ቤንሻንጉል” የተሰኘውን የኢትዮጵያ ግዛት ከሱዳን ጋር ለመቀላቀል ተግተው እንደሚሠሩና የዐረቦችን ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጥሩ አስገንዝበዋል፡፡

ይህን የግብጽን እብሪታዊ አገላለጽ ተከትሎም ሱዳን “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንደሚባለው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የምታደርገው ድርድር እና በኹለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ያደረገችው ወረራ ያነሰ ይመስል፣ አሁን ላይ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ “የሉዓላዊነት ጥያቄ አነሳለሁ” የሚል ማስፈራሪያ አዘል ቀረርቶን ይዛ ቀርባለች፡፡ የሱዳን ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ የኹለቱ አገሮች ልዩነት በግድቡም ኾነ በድንበር ውዝግባቸው መበርታቱን የሚጠቁምና እዚህ ግባ የማይባል የከረረ ትችትን በኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረ ነበር፡፡ የሱዳን ማስጠንቀቂያ የተደመጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መርየም አል-ሳዲቅ በግድቡ ጉዳይ የአገራቸውን አቋም ለማስረዳት እና ድጋፍ ለማሰባሰብ በአፍሪካ አገራት ጉዞ በማድረግ ላይ በሚገኙበት ወቅት ነው። እኚህ ግለሰብ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሱዳን ዳርፉር የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል “ይውጣልን” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዚህ መግለጫው፤ ሱዳን ኢትዮጵያን በዓባይ ውሃ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ከተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ለማቆራኘት እየሠራች ነው እያሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች በጥልቅ ሀዘኔታ እየተከታተለ መኾኑን ገልጿል። በተጨማሪም መግለጫው “አገራት እና መንግሥታት በቀደሙ አገዛዞች እና መንግሥታት ለተፈረሙ ስምምነቶች እና ውሎች ቁርጠኛ መኾናቸው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መሠረት የጣለ ልማድ ነው” በማለት ያብራራ ሲኾን “ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ውሎችን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እነርሱን የሚቃረን የሕዝብ አስተያየት በማደራጀት ገሸሽ ማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚበክል፣ ለአንድ ወገን ፍላጎት ተጋላጭ የሚያደርግ፣ ቀውስን የሚያስፋፋ፣ የጥሩ ጉርብትና መሠረትን የሚያናጋ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ሲል የከረረ ተቃውሞውን በኢትዮጵያ ላይ ሰንዝሯል።

ስምምነቶች ሲፈረሙ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ሱዳን በአንፃሩ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች በመግለጫው የጠቀሰው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተናጠል የትኞቹ ስምምነቶች እንደኾኑ ማብራሪያ ሊሠጥ አልፈለገም። “ለፕሮፓጋንዳ እና ለሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምክንያቶች እንዲህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እየመረጡ ውድቅ ማድረግ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ካለው ስምምነት ለመድረስ የማይረዳ ጎጂ እና ዋጋ የሚያስከፍል እንደኾነ ለማሳሰብ እንወዳለን” ሲልም ዝቷል፤ መግለጫው። የሱዳን ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመግለጫው “አሳሳች ሀሳብ ማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶችን ውድቅ ማድረግ ማለት ከስምምነቶቹ በአንዱ ከሱዳን ተላልፎ በተሰጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ መክተት እንደኾነ ለኢትዮጵያ ማስታወስ አያስፈልገንም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይዞታ “ቀደም ሲል የሱዳን አካል ነበር” የሚለው ክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና መገናኛ ብዙኃን ዘንድ በተደጋጋሚ እየተነሳ ይገኛል። ይህ የኾነው ደግሞ ከፍ ሲል መግቢያው ላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በግብጽ ስፖንሰርነት የተደረገና ኢትዮጵያን ለማዳከም አልፎም ሉዓላዊነቷን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ሲባል የተፈተለ ሴራ መኾኑ ለማንም የሚጠፋ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሱዳን የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የግንባታ ስፍራ የኾነውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን “ይገባኛል ማለቷ አግባብነት የሌለው ነው” ሲል ኮንኖታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በሱዳን በኩል የተጣረሱ መረጃዎች እየወጡ ነው ብለዋል። ቃል አቀባዩ “በሱዳን በኩል ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መግፋቷ ሳያንስ አሁን ደግሞ የታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለበትን የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ይገባኛል ማለቷ ያልተገባ ተግባር ነው” ያሉ ሲኾን የሦስቱን ሃገራት ድርድር በተመለከተ ኢትዮጵያ ባላት አቋም እንደጸናች መኾኗንም ገልጸዋል። ይህ የሱዳን በእብሪት የተሞላ ፍላጎት ምንጩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ተግዳሮት ከግምት ያስገባና የግብጽን አይዞሽ ባይነት ስንቁ ያደረገ ስለመኾኑ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ሱዳን በተለይም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ከስልሳ ኪሎሜትር በላይ ገስግሣ እንድትገባ ያስቻላት ህወሓት ሀገሪቱ ላይ የፈጠረው ሽንቁር መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ የህወሓት እብሪትና ሀገር የማዳከም እርምጃ ፍሬ አፍርቶለት ሀገሪቱ በሁሉም ማዕዘናት የችግር ቋጠሮዎችን እንድትሸከም አስችሏታል፡፡ በተለይም መጠሪያው ማንም ይኹን ማን በሀገሪቱ ውስጥ እንደፈለገ እየተንቀሳቀሰ የዜጎችን አንገት የሚቀላ፣ ከተሞችን የሚያቃጥል፣ ሀብትና ንብረትን የሚዘርፍ ሰው በላ ቡድን በማደራጀት በኩል ህወሓት ውጤታማ የኾነበት ስልቱ ነው፡፡ ይህን የተረዱት ግብጽና ሱዳንም በኢትዮጵያ ላይ መሳየፋቸውን ተያይዘውታል፡፡ የሀገራችን  ግራ ዘመም ፖለቲከኞችና ልሂቃኖችም የጠላት እንጀራ ቅልብተኞች ከኾኑ ሰነባብተዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው አብዛኛዎቹ ሀገር አፍራሽ ሚዲያዎች መሰራጫ ጣቢያቸው ካይሮ መኾኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በየትኛውም ዘመን ከጠላት ተላቅቃ አታውቅም፡፡ ነገር ግን የዚህ ዘመኑን ልዩ የሚያደርገው ውስጠ ከድ ባንዳዎች ብዙ መኾናቸውና በውጭ ኃይሎች ከሚጠበቀው በላይ መደገፋቸው ነው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...