
አባቷ አቶ አዱኛ ዋቆ ልጃቸው መልካም ባህርይ እንደነበራት ገልፀው ‹‹እኛ ምንም አንፈልግም፡፡ የምንፈልገው ፖሊስ ፍትህ እንዲያሰፍን ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡
ሞዴልና የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነችው ቀነኒ ከምትኖርበት አፓርታማ አምስተኛ ፎቅ ላይ ወድቃ ህይወቷ ማለፉን ፖሊስ መግለፁ ይታወቃል፡፡ በሀረር ነዋሪ የሆኑት አባቷ የልጃቸውን ህልፈት እንዴት እንደሰሙ ሲናገሩ ‹‹ስልክ ደውለው ከፎቅ ላይ መውደቋን ነገሩኝ፡፡ ሴት ልጅ ከፎቅ ላይ ልትወድቅ አትችልም፡፡ በተለይም ጨዋ የሆነች፣ ለለውጥ የምትለፋ፣ ራሷንና ቤተሰቧን ለመቀየር የምትጥር ነበረች›› ብለዋል፡፡
ጨምረውም ‹‹ስለነገ የምታስብ ነበረች፡፡ ስለዚህም እንደዚህ አይነት ነገር አታደርግም፡፡ ሌላ ሰው ካልጣላትና ካልገፋፋት በስተቀር እሷ ይህን ልታደርግ አትችልም፡፡›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አቶ አዱኛ በመግለጫቸው ልጃቸው ግልፅ ሴት እንደነበረችም አስረድተዋል፡፡ ‹‹ማለት የምትፈልገውን የምትናገር፣ ምንም የምትደብቀው ነገር የሌላት ናት›› ያሉት አባትየው ትላንት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል በተከናወነው የቀብር ስነስርአቷ ላይ ለመገኘት ችለው ነበር፡፡ ፖሊስ እስካሁን ስለልጃቸው ጉዳይ ጠርቶ እንዳላነጋገራቸው የጠቀሱት አቶ አዱኛ እሳቸው ግን ድምፃዊ አንዷለም ጎሳን አግኝተው በወቅቱ ስለተፈጠረው ጉዳይ ማነጋገር እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡
ሌላው በበርካቶች መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ በቀነኒና በአንዷለም መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው፡፡ የድምፃዊው ማኔጀር ሌሊሳ ኢንድሪስ ቀለበት ማሰራቸውንና በቅርቡም ጋብቻቸውን ለመፈፀም ማሰባቸውን መግለፁ ይታወሳል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ቀነኒን የድምፃዊ አንዷለም ሚስት በሚል መግለፁም አይዘነጋም፡፡ አባቷ አቶ አዱኛ ግን የሚሉት ሌላ ነው፡፡ ‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ አንዷለምና ቀነኒ ጥሩ ግንኙነት አላቸው›› ያሉት አባቷ ወደሁለት አመት ለሚሆን ጊዜ አብረው መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን በእጮኝነት ማሳለፋቸውን እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹ቀለበት አስረዋል የሚባለውን እኔ አላውቅም፡፡ እኛ ጋር እስካልመጡ ድረስም ቢያስሩም ተቀባይነት አንሰጠውም፡፡ ምክንያቱም እኛ ጋር ሽማግሌ አልተላከልንም›› ብለዋል፡፡ ጨዋ መሆኗን ጠቅሰውም ለቤተሰቦቿና ለዘመዶቿ ክብር ያላት ልጅ እንደነበረች ጨምረው መግለፃቸውን ቢቢሲ በአፋን ኦሮሞ ካቀረበው ዘገባ ተመልክተናል፡፡