Home ለዛ ስለቼክ አራት መሠረታዊ መረጃዎች፡-

ስለቼክ አራት መሠረታዊ መረጃዎች፡-

ስለቼክ አራት መሠረታዊ መረጃዎች፡-
  • ቼኩን ተቀብሎ ክፍያ እንዲፈፅም የታዘዘው የባንክ ቤት ስም በግልፅ በቼክ ላይ ሊኖር ይገባል።ይህም ባንክ በህግ የባንክ ቤትን ስራ ለማከናወን ስልጣን የተሰጠው ተቋም ብቻ መሆን ይኖርበታል።በኢትዮጽያ ከሚገኙ ባንኮች ተመሳስሎ የሚፃፋ የባንክ ቤት ስሞች ስለሚኖሩ ቼኩ ላይ የተፃፈው ባንክ በኢትዮጵያ እውቅና ያለውና  ሕጋዊ ፈቃድ አውጥቶ በስራ ላይ የሚገኝ  ባንክ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
  • ለቼክ አውጪው ሊከፈለው የሚገባውን የገንዘብ መጠን በግልፅ ሊፃፍበት ይገባል።  ይህም ሲባል ገንዘቡን ወጪ ለማድረግ ሌሎች መሟላት የሚገባቸውን ቅድመሁኔታዋች ያላመላከተ መሆን ይጠበቅበታል።
  • ቼኩ የወጣበት ቦታ እና ጊዜ በቼኩ ላይ የተፃፈበት መሆን አለበት። ቼኩ የወጣበትን ቦታናጊዜ የማይገልፅ ከሆነ ህጋዊ ቼክ አይደለም።
  • በቼኩ ላይ የተገለፀው ገንዘብ ከመቼ ጀምሮ ወጪ መደረግ እንደሚችል ቀኑን ወሩን እና አመተምህረቱን የተገለፀበት እንዲሁም ገንዘቡ የሚከፈልበትን  የባንክ ቤት ስም ወይም ቦታ የሚገልፅ መሆን አለበት።ይህን ያላሟላ ቼክ ህጋዊ ያልሆነ ሀሰተኛ ቼክ ሲሆን ሀሰተኛ ቼክ ማለት ቼክን ለማተም ስልጣን ባለዉ ባንክ ቤት ታትሞ ያልተሰጠ ወይም ታትሞ ከተሰጠዉ ጋር ተመሳስሎ የተሰራ ቼክ መሳይ ሰነድ ነው። 

የወንጀል ተጠያቂነት

ማንም ሰዉ ይህንን ሀሰተኛ ቼክ የሰራ፣ የተገለገለ ወይም ህጋዊ አስመስሎ ለሶስተኛ ወገን ያስተላለፈ እንደሆነ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 375 ና በተከታዮቹ አንቀፃች እንዲሁም በተደራቢነት በወ.ህ.ቁ 692 መሰረት በማታለል ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።

ድንቃይ

በሀገረ ኬኒያ በመኪና አስመጪነት የምትሰራው ቱጃሯ ኔሊ የትዳር አጋሯ በመኪና አደጋ ከሞተ በኋላ ሶስት ባሎችን አግብታለች። ለምን ሶስት ባል አገባሽ ? አንዱ አይበቃሽም ወይ ? ተብላ ብትጠየቅ ”ባሌ በመኪና አደጋ ሲሞትብኝ ልቤ ተሰብሮ ነበር።ከባድ ሀዘን ውስጥ ነበርኩኝ።ምናልባት አሁን አግብቼ ቢሞትብኝ ሀዘኑ ለኔ እጅግ ከባድ ነው።ለዚህ ነው አንዱ ቢሞትብኝ በሌሎች እፅናናለሁ በማለት ሶስት ባሎች ያገባሁት” ብላለች። አንድ ቤት ሶስት አባወራ አይከብድም ወይ ተብለው የተጠየቁት አባወራዎቹ ”እድሜ ለኔሊ ምንም ሳይጎልብን ሁሉ ተሟልቶልን በፍቅር ነው የምንኖረው”ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከእንስሣት ዓለም

ኦራንጉታን፡-

  • ኦራንጉታኖች የሚገኙት በማሌዢያ እና በኢንዶኔዥያ፤ ሱማትራ እና ቦርኔኦ በሚባሉ ደሴቶች ብቻ ነው። ፊታቸው ጠፍጣፋ ነው
  • ወንዱ ኦራንጉታን ከሴቷ ኦራንጉታን በእጥፍ ክብደቱ ይበልጣል። ማለትም ሴቷ 50 ኪሎ ገደማ ስትሆን ወንዱ ደግሞ 100 ኪሎ ይመዝናል
  • የሰው ልጅ ኦራንጉታኖችን አሰልጥኗቸው በምልክት ቋንቋ ከሰው ጋር እንዲግባቡ ማድረግ ችሏል።
  • ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላኛው ዛፍ ለመሄድ እንደ ጦጣ አይዘሉም። አንዱን ቅርንጫፍ ከያዙ በኋላ ሌላውን በመልቀቅ (በመንጠላጠል) ነው የሚጓዙት። ያረጁ ወንዶች ግን ከ ክብደታቸው እና ከእድሜያቸው አንፃር መሬት ወርደው ከተጓዙ በኋላ የሚፈልጉት ዛፍ ጋር ሲደርሱ ይወጣሉ።
  • እግሮቻቸውም ሆነ እጆቻቸው እኩል እንደ እጅ ነው የሚያገለግሉት በሁሉም መጨበጥ ይችላሉ። በቀላሉ ባለ አራት እጅ ማለት ይቀላል
  • አዲስ የተወለዱ ኦራንጉታኖችን የምትንከባከበው እናትየዋ ብቻ ናት። አባት ኦራንጉታን ልጅ አያሳድግም
  • ቁመታቸው እንደ ሰው ከ 1.4ሜትር እስከ 1.8 ሜትር ይሆናል
  • አማካኝ የእድሜ ጣርያቸው 45 ነው

ምንጭ :- National Geographic Wild

ጠቅላላ እውቀት

ተሽከርካሪ ላይ የሚፃፉ የእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃላት ምንነትና ትርጉማቸው፡-

ተሽከርካሪ ላይ በአጭሩ ስለሚፃፉ ፅሁፎች አብዛኛው ሰው በቂ ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት የሞተር አይነቶችን ለተሽከርካሪው ስያሜ ሲጠቀሙት ይስተዋላል::

V8

ቪ ኤት 8 ሲሊንር ያለዉ እና ቅርፁ V የሆነ ሞተር ነዉ። V የሞተሩን ቅርፅ ማለትም የሲሊንደሮችን አቀማመጥ 8 ደግሞ የሲሊንደሮችን ብዛት ይወክላሉ፡፡ ሲሊንደሮቹ ሞተር ላይ በሁለት ረድፍ እኩል ብዛት ኑሯቸዉ (አራት አራት) ትይዩ ሆነው ይቀመጣሉ። በተመሳሳይ V6 ኢንጅን 6 ሲሊንደሮች ያሉት ሲሆን አቀማመጣቸዉ ከ V8 ኢንጅን ጋር ተመሳሳይ ነዉ። ስለዚህ V8 የሞተር አይነት እንጂ የመኪና መጠሪያ ስም (ብራንድ) አይደለም::

D-4D

ዲ ፎር ዲ በተመሳሳይ የመኪና ብራንድ ስያሜ ሳይሆን የሞተር አይነት ነው:: ዲ ፎር ዲ የናፍጣ ሞተር ሲሆን D-4D የሚለው የእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃል ሲተነተን – (Direct Injection 4 Cylinder Common Rail Diesel Engine) የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ይህ ሞተር (ኢንጅን) አራት ሲሊንደሮች ያሉትና በሲሊንደሮች ውስጥ የገባው አየር ከታመቀ በኋላ ሰዓቱን ጠብቆ በእያንዳንዱ ሲሊንደር በቀጥታ ናፍጣ በመርጨት ኃይል ማምረት የሚችል የሞተር አይነት ነዉ::

GDI

ዘመናዊ የቤንዚል መኪኖች ላይ GDI የሚል ጽሑፍ አለ። GDI ማለትም ጋዞሊን ዳይሬክት ኢንጀክሽን ማለት ሲሆን የነዳጅ አረጫጭ ስርዓት ነዉ። ይህን የነዳጅ አረጫጭ ዘዴ የሚጠቀሙት ዘመናዊ የቤንዚን መኪኖች ናቸዉ። በብዛት በቤንዚን ሞተር ነዳጅና አየር በካርቡሬተር አማካኝነት ተቀላቅሎ ወደ ሲሊንደር የሚገባና በስፓርክ ፕለግ (ካንዴላ) አማካኝነት የሚቀጣጠል ሲሆን ይህ GDI ሞተር ግን ካርቡሬተር የለዉም። ነዳጅና አየር በአንድ ላይ ተቀላቅሎ ወደ ሲሊንደር አይገባም:: እንደ ናፍጣ ሞተር መጀመሪያ አየር ወደ ሲሊንደር ከገባ እና ከታመቀ በኋላ ቤንዚን በጉም መልክ ወደ ሲሊንደር ይረጭና የመቀጣጠልና ሀይል የማምረት ስራ ይካሄዳል። ጂ ዲ አይ ኢንጅን ነዳጅ የሚረጨዉ በከፍተኛ ግፊትና በቀጥታ በያንዳንዱ የሲሊንደር ኮምበስሽን ቻምበር ላይ ነዉ። ይህም ሰዓቱን የጠበቀ የነዳጅ አረጫጭ እና የተመጠነ ነዳጅ እንዲረጭ ያደረገዉ ሲሆን ነዳጅ ቆጣቢ እንዲሆንም አድርጎታል። በካይ ጋዝ ልቀትንም እንዲቀንስ አስችሎታል።