አቦነህ አሻግሬ ዘኢየሱስ
ብጻይ መለስ ዜናዊ ጫካ እያሉ የጻፉት “ዘወትር የሚንኩዋኩዋዉ በር“ የተሰኘ ትግርኛ ልቦለድ ወደ ድራማ ተለወጦ በዩኒቨርሲቲዉ በመዘጋጀቱ፣ በዚህ ታሪካዊ አቅርቦት ላይ ተገኝቼ ሙያዊ አስተያየት እንዳበረክት ተጋብዤ መቀሌ ገባሁ፡፡ ዋናዉ ያጉዋጉዋኝ ያንን አስቸጋሪ ስራ እንዴት ወደተዉኔትነት እንደለወጡት ለማት ነበር፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ልቦለዱ ከትግርኛ ወደ አማርኛ ተተረጎሞ ስለነበረ፣ በፊልም ከመቅረጽ፣ ወይም ወደ ድራማ ቀይሮ በብሄራዊ ትያትር መድረክ ላይ ከማቅረብ፣ ወይ እንዳለ አትሞ ከማሰራጨት የትኛዉ ተመራጭ እንደሆነ ሀሳብ እንዲቀርብ ተጠይቆ መገምገሙ ትዝ ይለኛል፡፡ ግርግር የተባለ የእኩይ ገጸባህርይ አሳሳል እዉናዊ ሆኖ፣ደራሲ መለስ አጭበርባሪነትን፣ አታላይነትንና አስመሳይነትን በምን ያህል ጥልቀት እንደሚያዉቁ የሚያሳይ ነዉ፡፡ ይሁንና ከልቦለድ አጻጻፍ ብልሀት አንጻር የገጸባህርይ ምጣኔዉ፣የሴራ አወቃቀሩ፣ በድርጊያ ምሰልን ከመፍጠር ይልቅ በረጃጅም የፖለቲካ መቀስቀሻ ዲስኩሮች መገንባቱ ስነጥበባዊነቱን መገደዳደሩ፣የጎላ እጥረትን ስለሚያሳይ፣ከሶስቱም አማራጮች በአንዱ ቢቀርብ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ስምና ክብር የማይመጥን መሆኑ ተገልጾ፣ ሌላ ሰዉ ነካክቶ ከሚያበላሸዉ እሳቸዉ ራሳቸዉ እንዲያዳብሩት አስተያየት ተሰንዝሮ ነበር፡፡ስራ ስለበዛባቸዉ ሊሆን ይችላል.. አስተያየቱን ሊቀበሉ ግን አልቻሉም፡፡
በዚህ ሁኔታ ለሶስት አሰርት ተንጠልጥሎ የቆየ ፕሮጀክት በምን አኩዋሃን እንደተተገበረ ማየት አጉወጊ ስለነበረ በቦታዉ እንደተገኘሁ፣ ያ ክፉ የጨጉዋራ በሽታዬ ተቀስቅሶብኝ ድራማዉን ሳልጨርሰዉ አቁዋርጬ ወደሆቴሌ ተመለስኩ፡፡
እግረ መንገዴን አንዳንድ ጽሁፍ ለመሞጫጨር ለቀናት ቃለመጠይቅ ሳካሄድ ሰንብቼ ወደ አዲስ አበባ እንደነገ ልመለስ ስል የጦር አይሮፕላ ቦምብ ፍንዳታ ምድሩን ብቻ ሳይሆን ልቤንም አንቀጠቀጠዉ፡፡ በደመ ነፍስ እራሴን ከአልቤርጎ አልጋዬ ስር አገኘሁ፡፡
ቀልቤን ከገዛሁ በሁዋላ ሰሞኑን ስሰጋበት የነበረዉ ጉዳይ አሳሰበኝ፡፡ ካረፍኩበት ሆቴል ዉስጥ ምናልባት ፖለቲከኞች ስለሚኖሩ የጦር ጄት ኢላማ ልሆን እችል ይሆናል በማለት፣ አዘወትራት ከነበረዉ ከሰሞኑ ደንበኛ ከአዴይ እርግቤ ጠላ ቤት ሮጬ ገባሁ፡፡
አደይ እርግቤ ድንጋጤ ዉስጥ የነበሩ ቢሆንም፣ እንደ ወትሮዉ ተጣድፈዉ መቀመጫ ጠራረጉልኝና እንኮይ የመሰለዉን ጠላቸዉን በምኒልክ ዋንጫ ሞልተዉ አስያዙኝ፡፡ አደይ ጫወታ ያዉቃሉ፡፡ በ ለ እና ን ፊደል እያወዙ ጣፋጭ ወሬያቸዉ ሲያጫዉቱኝ፣የሚታየኝ ደግነታቸዉ፣ ርህሩነታቸዉ፣ሰዉ አፍቃሪነታቸዉና ትህት ናቸዉ ነዉ፡፡
ከዚህ ቀደም ያየሁዋቸዉ ሶስት ትግራዋይ እናቶች በባህርይ እጅጉኑ ይመሳሰላሉ፡፡ ከመሀል አገር ወደ እነሱ የሄደዉን እንደባእድ ከማየትና ከመጥላት ይልቅ፣ለእንግድነቱ ክብር ሰጥተዉ፣ወገን ሳይለዩ ልዩ ፍቅር የሚለግሱ ቅዱሳን ናቸዉ፡፡ የመቀሌዋ የሙሉጌታ አረጋዊ እናት ትዝ ይሉኛል፡፡ ደርግ ገንጣይ ተገንጣይ አጠፋለሁ ብሎ ሰራዊት ባዘመተበት ዘመን፣የተጠሙና የተራቡ ወጣት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ሲያዩ “ አወይ እናታችሁ እንዲህ ተጎሳቁላችሁ ብታያችሁ እንዴት ትሆን ይሆን?“ እያሉ በማዘን በቀና ልቦና ወደቤታቸዉ እያስገቡ ቡና ያፈሉላቸዉ ነበር፡፡ ለሳቸዉ ቁቡ ደርግና ወያኔ ሳይሆን ሰዉ ነበር!
በ1984 ዓም ማትሪክ ለመፈተን ኩኽያ (በቀደለታ የሰሜን ጦራችን የተተነኮሰበት ስፍራ) በተላክሁበት ወቅት ያጋጠመን የአዴይ (ስማቸዉ ተዘናጋኝ) ሁኔታም እንዲሁ የሚያስገርም ነበር፡፡ የፒካፕ መኪናዉ ሹፌር፣ በከተማዋ አለች ከምትባል ፎቅ ብጤ ሆቴል በራፍ አስጠግቶ የፈተና ወረቀት የተሞላባቸዉን ጆንያዎች አወረደልኝ፡፡ ሊቀበሉን ወደደጅ ለወጡት የሆቴሉ ባለቤት “እዚ ናይ መንግስቲ ማትሪክ ፈተና ስለዘኮነ ማእጸዉ ተሪር ዝኮነ ቁልፊ ዘለዎ ክፍሊ ሀብዎም፡፡፡ አባይ ሰብ መንግሰቲ እዮም፡“ ብሎ ተሰናብቶኝ ሄደ፡፡
አዴይም እየተጣደፉ ወደ ጉዋሮ መኝታ ክፍሎች እንዳመሩኝ፣ ገርበብ ያሉትን ክፍሎች በመስኮታቸዉ እያየሁ ትንሽ ሰፋ ያለዉን ክፍል መርጬ ስገባ፣ አዴይ ራሳቸዉ ጆንያዎቹን እየጎተቱ እዚያዉ አስገቡልኝ፡፡
የከተማዋ ዋና ሆቴል ስለተባለች በአንጻራዊነት ዉድ መሆንዋ አይቀርም በማለት ዋጋዉን ጠየቅሁ፡፡
“አርባአተ ቅርሺ“! አሉ ወደሌላ ክፍል እየተጣደፉ፡፡
እዉነትም ደረጃዋ የከፋ አይደለም፡፡
ክፍሌ ሆኜ በመስኮት ሳያቸዉ በአንዲት ረዳት እየታገዙ ከፊት ለፊት ካለዉ ክፍል እቃ ወደዉጭ ያግዛሉ፡፡ ክፍሉዋ ከሁሉም የሰፋች ከመሆንዋ ሌላ ሲሚንቶ ወለልዋ በጥቁር ሬንጅ የተወለወለ ነዉ፡፡ በግድግዳዉና በየጠረጴዛዎች ላይ የቅዱሳን ስእሎች እና የአዴይ ፎቶግራፎች ተደርድረዋል፡፡ አልጋዉ የፋሚሊ እንጨት ከመሆኑ በተጨማሪ የፍራሹ ዉፍረት ከፍ ያለ ነዉ፡፡ መኝታ ክፍላቸዉ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ቶሎ ቶሎ ፎቶዎችን ካወረዱና አዲስ አንሶላና ብርድ ልብስ ካነጠፉ በሁዋላ ወደኔ ክፍል መጥተዉ የፈተና ኬሻዉን እየታገሉ ከክፍሉዋ አስገቡ፡፡
“አብዚአትዪም የአረፉ፡፡“ አሉ በትህትና፡፡
“ይሄ ርስዎ መኝታ መስሎኝ ነበር“ አልኩ የምለዉ ግራ ገብቶኝ
“እወ፡፡ አነይ ሌላን ቦታ ንተኛለሁ፡፡“ አሉ በአማርኛ ድብልቅ ሊያስተናግዱኝ፡፡
እዚህ ላይ ትንሽ ሀሳብ ገባኝ፡፡ እኚህ ነጋዴ ፣ ባለስልጣን መስያቸዉ መኝታቸዉን በጥሩ ዋጋ ሊያከራዩ ይሆናል ብዬ ጠረጠርኩ ፡፡
“ክንዴ ዩ?“ አልኩዋቸዉ ትግርኛንም እግረ መንገዴን ልለማመድ ስል፡፡
“አርባአተ ቅርሺ፡፡“
“እማማ ደግ አላደረጉም፡፡ ለኔ እኮ የቅድሙ ክፍል ይበቃኛል፡ እንኩ፡፡“ የኪራዩን ሂሳብ ዘረጋሁላቸዉ፡፡
“ዋይ! ድሀራይ፣ ምን ያስሸኩላል!“ አሉ፡፡
ድምጻቸዉን ከፍ አድርገዉ “ምጽላላ! ንእንግዳ ቡና ዐቀልጥፍዮ፡፡“
ክቡር አልጋቸዉን ለእኔ ለእንግዳዉ ለቀዉ፣ እኔ መተኛት ከነበረበት ቦታ መተኛታቸዉ አስደንቆኛል፡፡ እንዲያ ለሳምንት እንደልጃቸዉ ተንከባክበዉኝ የፈተና መልሴን ሸክፌ በሽሬ አክሱም ገባሁ፡፡ ከዚያም ፈታኞች ወደየአቅጣጫችን ልንሰማራ ተዘጋጀን፡፡ በቅድሚያ ግን አንድ ነገር መወሰን ነበረበት፡፡
የትግራይ ክፍለ ሀገር ባሉት ትምህርት ቤቶች የሚፈትኑ የዩኒቨርሲቲ መምህራን አዉቶብስ ሞልተን ደህና አገር እያየን ከሊማሊሞ ጠመዝማዛዉ መንገድ ስንደርስ፣ ቁልቁል የገደሉን ርቀት እያየን ነፍስ ግቢ ነፍስ ዉጪ ሆነ፡፡ የቡድናችን መሪ ፕሮፌሰር አለማየሁ ሀይሌ ከሾፌሩ ጎን ተቀምጠዉ ለጥንቃቄ የሹፌሩን አነዳድ ሲከታተሉ፣ ደረጃዉን የጠበቀ አልሆንላቸዉ ሲል ግሳጼ መሰንዘር አከታትለዋል፡፡ እኛም ጥፋተኛ ነበርን፤ ጠቀም ባለዉ ዉሎ አበላችን ሆቴል ገብተን ጥሩ ምሳ ስንበላ፣ ለማበረታቻ ያህል አዋጥተን ሹፌሩ ለመጋበዝ አላስታወስንም፡፡ ምናልባት በዚህ ተቀይሞ፣ ወይንም የፕሮፌሰር ቁጣ እልክ አጋብቶት፣ ወይ ባልታወቀ ምክንያት ያንን ገደል ተዝናንቶ መሪዉን በአንድ እጅ ብቻ ያዞራል፡፡ ፡ “በሁለት እጅህ ንዳ“ ብለን ሲንጮህበት እሺ ይልና አዘናግቶን እንደገና ባንድ እጅ፡፡ ደግሞ ለተንኮሎ የአዉቶብሱን አፍንጫ ከመንገድ ጠርዝ ወደገደሉ አስቀስሮ እሪ! ያስብለናል፡፡ ሁዋላ አክሱም እንደደረስን አንጋፋ ምሁራኑ በዚያ መንገድ በፍጹም በአዉቶቡስ እንደማይመለሱ ለፕሮፌሰር አሳስበዉ፣ እኛም አድማዉን ተቀላቅለን በአይሮፕላን እንድንመለስ ተወሰነ፡፡እንኩዋን አየር ወለድ ወታደር አልሆንኩ፡፡
አክሱም ካንድ ሆቴል እራት ስንበላ ከአዲስ አበባ ከመጣ አንድ ሰዉ ጋር ተገናኝተን ስንጨዋወት፣ የመጣዉ ነገ ለምትከበረዋ የአክሱም ጽዮን ስለት ለመስገባት እና ለታመመችዉ ባለቤቱ ጠበሉዋን ይዞ ለመመለስ እንደሆነ አጫወተኝ፡፡ ፋርማሲ አብረን ሄደን ፈሳሹን ባለቢልቃጥ የጨጉዋራ መድሀኒት እንድንገዛ ጠየቀኝ፡፡ በዚያን ወቅት እንደዛሬዉ ጠርሙስ እንደልብ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ቢኖር እንኩዋን መግዣዉ በጣም ዉድ ነበር፡፡ ጠርሙስ ስለማይገኝ መድሀኒቱን አፍስሶ ጠበል ሊይዚበት ነበር ብልሀቱ፡፡
ከሆቴሉ ፊትለፊት ፋርማሲ አገኘንና ገባን፡፡ አንዲት የሀገር ባህል ልብስ የለበሱ ቀይ ዳማ ደርባባ ሽሩቤ እመቤት ከባንኮኒዉ ቆመዋል፡፡ እንግዳዉ መድሀኒቱን አዘዘና እሜቴ ከተደረደረበት ሲያማርጡ አይኔ ተከትሎዋቸዉ፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከሳቸዉ በላይ ካለ የመጨረሻ መደርደርያ ላይ የቢቢታ ( ኦሬንጅ) ጠርሙስ ከጥግ ተወሽቆ አየሁ፡፡ ለሰዉየዉ አመላከትኩት፡፡
“ያ ጠርሙስ ይሸጣል?“ አለ፡፡ደፈር ያለ ቢጤ ነዉ፡፡
“ምናይ ኢሎም?“ በጣት ወደተጠቆመዉ ጠርሙስ ግራ በመጋባት አዩ፡፡ እንዳልገባቸዉ አወቅሁ፡፡
“ዚ ጠርሙሲ ናይ ጽዮን ጸበሊ ልወስድኮም፡፡ ክንዴ እዩ?“ አልኩ አማርኛዬን ወደትግርኛ አስጠግቼ፡፡ “ክንዴ እዩ“ን ግን በደንብ አዉቃታለሁ ፡፡
ገባቸዉና ወንበር በጠረጴዛ ላይ ሰቅለዉ፣ ከላዩ ላይ ወጥተዉ ተንጠራርተዉ አወረዱ፡፡ እኛን ባለንበት ትተዉ፣ ጠርሙሱን ይዘዉት ተሰወሩ፡፡ ጉዋዳ ዉስጥ ዉሀ ሲፈስና የሆነ ነገር እየታጠበ እንዳለ ይሰማናል፡፡
“ስንት ትጠይቅ ይሆን?“ አለኝ የደረት ኪሱን እየዳበሰ፡፡
“ሀምሳ ከሸጠችልን ጥሩ ነዉ፡፡“
“እስከ መቶ ልገዛት እችላለሁ፡፡“ ብር አዉጥቶ ያዘ፡፡
ባለፋርማሲዋ ወዳለንበት ተመልስዉ ጠርሙሱን በጨርቅ አደራረቁና ወልዉለዉ ከፊታችን አስቀመጡት፡፡
“ክንዴ እዩ ?“ አልኩዋቸዉ፡፡
“ምናይ?“ ግራ ተጋቡ፡፡
“ዚ ጠርሚሲ ዋጋ ክንዴ እዩ?“
“ዌለይ! ንጸበል እዲዩ ንበልካቱም?“
“እወ፡፡“
“እሞ ልጸበል ይከፈል ድዩ ገንዘብ?“
አመስግነን በሴትየዉ ደግነት ምልካምነት፣ሰዉነት እየተገረምን ወደመጣንበት ተመለስን፡፡ ዛሬ የቢራና የአረቄ ፋብሪካ በመብዛቱ ጠርሙስ መርከሱን አይተህ ያሄን እንደቀላል አታስብ ብርቅ ነዉ፡ እንዲያዉም በነጻ መስጠት መስዋትነት ነዉ፡፡ የደግ ኢትዮጵያዊት መገለጫ፡፡
እና ከጦር ጀት ድብደባ ለመጠለል ወደ ገባሁባት የአዴይ እርግበ ጠላ ቤት ልመልሳችሁ፡፡ ካስጨበጡኝ የምኒልክ ዋንጫ ጠላዬን እየተጎነጨሁ፣ ፋታ እየሰጠ ከሚፈነዳዉ ፈንጂ ድምጽ ተለማመድኩ፡፡ ቡና እያፈሉልኝ ሳለ፣ ወንድ ቅድመ አያታቸዉ ባለብዙ ላም ባለጸጋ ስለነበሩ በበጋ ወራት ከብቶቻቸዉን ሳር ለማብላት ከመንደፈራ ወደ ጸለምት እየሄዱ ለወራት ሲቆዩ ከጎንደሬ ሴት – ሴት አያታቸዉን እንደወለዱ፣ ሴት አያታቸዉን ኦሮሞዉ የንጉሱ ወታደር አግብቶ እናታቸዉ እንደተወለዱ፤ እናታቸዉን ደግሞ አንድ ወላይታ የወባ መከላከያ ሹፌር አግብቶ መቀሌ እንዳመጣቸዉ፣ እሳቸዉን ደግሞ ጎጃሜ አሰተማሪ አግብተዉ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደወለዱ፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅትታላቁ ልጃቸዉ የደርግ ወታደር ሆኖ፣ታናሹ ደግሞ ተጋዳላይ ሆኖ ሁለቱም በህይወትሳይመለሱ እንደቀሩ በሀዘኔታ አወጉኝ፡፡ በሀሳብ ሩቅ ሩቅ ወሰዱኝ፡፡
ስፈራ ስቸር ችግሬን አነሳሁባቸዉ፡፡ አሁን ጦርነቱ መጀመሩ ነዉ አዴይ፡፡ ባንክም ሆቴልም ስለተዘጋ ጉዴ ፈልቶዋል፡፡“ አልኩዋቸዉ፡፡እያፈርኩ ጠላዉን ፉት አርጌ፡፡
“ዋይ! ምን ጉዲ ይፈላል?“ እኔ እናትህ አለሁ አይደለም እንዴ! ምቾት ታጣለህ እንጂ እስኪያልቅ የምበላዉን ሽሮ እየበላህ ትቆያለህ፡፡ መኝታ ከሆነ ፍራሽ እዚያች ጥግ እየተነጠፈልህ ትሰነብታለህ፡፡ ምን ችግር አለ?“
አንባ መጣብኝ፡፡ ትላንት በአንድ አዳራሽ ተሰብስበዉ ሲመክሩ የነበሩ፤እህል ዉሀ ከአንድ ጠረጴዛ ሲቁዋደሱ የነበሩ፣ በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ሲሰለጥኑ የነበሩ፣ አገርን ከጠላት በመከላክል አላማ አንድ አይነት የኢትዮጵያ ሰራዊት ዩኒፎርም ለብሰዉ ተደባልቀዉ የሚኖሩ የአገር ልጆች፣ ጎራ ለይተዉ በአረህ ሲንጨራጨሩ፣ በሳንጃ ሲሞሻለቁ፣ አንገት ለአንገት ተናንቀዉ የእጅ ቦምብ እተጎራረሱ ነፍስና ስጋቸዉን ሲበታተኑ በምናቤ አይቼ ምርር ብዬ አለቀስኩ፡፡ በማያዉቁኝ አደይ እርግቤና በማላዉቃቸዉ የመሀል አገር ሰዉ መሀል የእናትነትና የልጅነት ፍቅር ተከስቶ ለነብሴ ዋስትና መሆኑን ሳስብ ይበልጥ ተንሰቀሰቅሁ፡፡ ልበ ብርሀናት የትግራዋይ እናቶች ኢትዮጵያዊነትን ከሊሂቃኑ በላይ በጥልቀት የመረዳታቸዉ ምስጢር አልገባ አለኝ፡፡
የጦርነትን አስከፊነት በምሬት እየገለጹ፣ ሰላም ተመልሶ መቀልበሱ ከልብ እያሳዘናቸዉ፣እኔን ሲያጽናኑ ሲባረታቱ ዉለዉ አመሹ፡፡ ሞባይል ስለማይሰራ ከህብረተሰብ መነጠል የሚያም ነበር፡፡ ኤሌክትሪክ ስለተቁዋረጠ በድቅድቁ ጨለማ አስጠይነት ሳብያ በጊዜ ወደየመኝታችን አመራን፡፡ የጀት ቦምብ ድምጽ እንቅልፍን ሲመታ፣ አይናችን በስጋት እየተበለጠጠ ሌሊቱን አሳለፍን፡፡ አደይ እርግበ ማዶ ከአልጋቸዉ ሆነዉ፣ እኔ ከወዲሁ ወለል ፍራሼ ላይ እየተገላበጥኩ፣ በደርግ ዘመን የነበረዉን ሁኔታ እየተረኩልኝ ነጋና በጠዋቱ ተነስተዉ ቡና አፍልተዉ፣ ቆሎ በሰሀን፣ ጠላ በማንቆርቆርያ አቅርበዉልኝ ዛሬን እንደትላንቱ ተያያዝኩት፡፡ በደጃፋቸዉ የሚያልፍ አንድም ሰዉ አልነበረም፡፡ ጸጥ ብሎዋል፡፡ ጸጥታ ይቀፋል፡፡ ጦርነት መቀሌን ህይወት ነስቶዋታል፡፡
ሳምንታትን እንደዚያ ዘልቄ፣ መቀሌ በትንሽ በትንሹ ነፍስ መዝራት ስትጀምር በአካባቢዉ ሁካታ ተሰማ፡፡ ወዲያዉ ወደ አስር የሚሆኑ ጎረምሶች እየተጨቃጨቁ ከደጃፍ ደረሱ፡፡
“አዴይ እርግበ፣ ጠላ ካለ አባክዎን ቶሎ ይስጡን… በቁም የምንጠጣዉ ፤ተቻኩለናል፡፡“ብለዉ ተቀመጡ፡፡
የአዴይ ጠላ ካላለቀ በስተቀርየመቀሌ ወጣት ሌላ ቤት ገብቶ አይጠጣትም፡፡ ከደግነታቸዉና ጨዋታ አዋቂነታቸዉ በላይ ሁለት ልጆቻቸዉን ከሁለት ጎራ በማጣታቸዉ ይታዘንላቸዋል፡፡ ገንዘብ የሌለዉ በብድር የመጠጣት መብቱም ይጠበቅለታል፡፡
“ምንድነዉ የሚያቻኩላችሁ በጠዋት?“ አሉ ኩባያ እያደሉዋቸዉ፡፡
“ስዩም መስፍንን ስለያዝን ለመንግስት ልናስረክብ ነዉ፡፡
“ምን ሲያደርግ ያዛችሁት?“
ወጣቶቹ በጣም ሳቁ፡፡
“ጁንታ ሆኖ ነዉ ፡፡“ አለ አንዱ
“ዋይ! አንተ ጁንታ አትበል፡፡“ ገሰጸዉ ጉዋደኛዉ፡፡
“ተጋዳላዩን ስዩም መስፍን?“ አሉ እንደመገረም ብለዉ፡፡
“እወ፡፡ ሀጎስ ነዉ የያዘዉ፡፡ እሱን ያስያዘ 10 ሚሊዮን ብር እንደሚሸለም አልሰሙም?“
“አንተ ሀጎስ፤ የት አግኝተህ ነዉ የያዝከዉ?“
“ከኛ እንግዳ ማረፍያ ራሱን ለዉጦ ተደብቆ ገብቶ፡፡ እሱማ በቤቱ የሚታወቅ አልመሰለዉም፡፡“ አለ ጠላዉን ጅዉ አድርጎ፡፡ በእድሜ ከእነሱ ከፍ ያለ ነዉ፡፡ ፊቱ በደስታ ይበራል፡፡
አንዱ ድግሞ “አደይ ርግበ፣ ገንዘቡን እንደወሰደ ዛሬዉኑ ይህቺን ጠላ ቤት ወደ ሆቴል መለወጥ አለበት፡፡ ያስረሳዎትን ብድር መክፈል አለበት፡፡“ አለና ስቆ ጉዋደኞቹን አሳቀ፡፡
“ሀጎስ ሲያጣ ነዉ የሚያስቸግረዉ እንጂ ሲያገኝማ ቸር ነዉ፡፡ ሆቴልማ ይከፍትልኛል፡፡ አትከፍትልኝም ወዲ ግርግር?“ እንደወትሮዉ እየቀለዱ፡፡
ስዩም መስፍን ለምን እንደ ተያዘ፣ እሱን ለያዘ ለምን ብዙ ብር እንደሚሰጥ፣ጁንታ ምን እንደሆነ በዉል ያጤኑት አልነበረም፡፡ እንደማንኛዉም የጠላ ቤታቸዉ ወግ ሊያዳምቁ ሲሉ ነዉ ጣልቃ እየገቡ የሚሳተፉት፡፡
“ቶሎ ድገሙና ተነሱ፡፡“ ሲል መመርያ ሰጠ ሀጎስ፡፡
“እንዴት ዝምብሎ ተያዘልህ ወዲ ግርግር?“ አሉ አደይ ለጫወታ ብለዉ፡፡
ተጣደፈ ለማስረዳት፡፡ “ሊሸዉደኝ ሲል ሸዉጀዉ! የአጥሩ በር ተመታ፡፡ የሰሞኑ ዘራፊዎች የመጡ መስሎኝ፣ ዱላዬን አፈፍ አድርጌ በቁልፉ ቀዳዳ አሹልቄ ሳይ አንድ ሰዉ ብቻ እንደቆመ አየሁ፡፡ ከአጠገቡ ኮብራ መኪና ቆሞዋል፡፡ ማነህ አንተ! ብዬ በቁጣ ጠየቅሁት፡፡ እኔ ነኝ፡፡ እባክህን ለሁለት ሰዉ አልጋ ፈልገን ነዉ፡፡ ክፈትልኝ አለኝ፡፡ ከፈትኩለት፡፡ ደህና ልብስ የለበሰ ስለነበረ መጠራጠር ተዉኩ፡፡
“መታወቂያ አሳየኝ“ ስል የሁለት ሰዉ አዉጥቶ ሰጠኝ፡፡ እንግዳ መቀበያዋ ክፍል ወስጀዉ ልመዘግበዉ ስል መብራት ስለሌለ የመታወቂ ጸሁፉ ትንንሽ እንግሊዝኛ ሆኖብኝ ማንበብ አቃተኝ፡፡
ከትክት ብለዉ ሳቁ ጉዋደኞቹ፡፡ “በመብራት አታሳብብ፡፡ አዴይ በትልልቁ ቢጻፍም እንግሊዝኛ የት ማንበብ ይችልና ነዉ “ሲል አንዱ ጎነተለዉና የበለጠ ጉዋደኖቹን አሳቀበት
“ልጄን አታናድዱት በደንብ ያዉቃል፡፡ እሺ.. “ ሲሉ አቁዋረጣቸዉና…“ማክስ ስላደረገ ፎቶዉ አያስታዉቅም፡፡ መመዝገቢያ ደብተር አዉጥቼ ለመጻፍም ጨለማዉ አስቸገረኝ፡፡ እሱ እንዲጽፈዉ ሰጠሁትና የሁለት ሰዉ ፈርም ሞላ፡፡ ወረቀቱን እያመሳከርኩ ለማረጋገጥ “ያንተ ስም ማን ነዉ ?“ አልኩ፡
“ሀብታይ ደብረጽዮን፡፡“
“ደብረጽዮን ያንተ ነዉ ያባትህ ስም ?“
“ያባቴ ምነዉ፡፡“
ከዚያ የሁለተኛዉን ሰዉዬ ስም እንዲያነብልኝ ጠየቅሁት፡፡
“ስዩም መስፍን፡፡“
“ምናይ በሉ?“ አፈጠጥኩበት፡፡
“ስዩም መስፍን፡፡ መጀመርያ የሳቸዉን ክፍል ቁልፍ ስጠኝ፡፡ በጣም ደክሞዋቸዋል፡፡“
እያሰብኩበት ሁለት ቁልፍ ሰጠሁት ፡፡ ስዩም መስፍን ካቦርት ደርበዋል፡፡ አንገታቸዉን በፎጣ ጠምጥመዋል፡፡ ቆባቸዉን ወደ መነጽራቸዉ ገፋ አድርገዉ ትልቅ ማስክ አስረዋል፡፡
“ከመይለሀ፡፡ የቁስል አልኮል በአጋጣሚ ይኖርህ ይሆን?“ ጠየቁኝ፡፡ ደንግጬ ዝም ስል ሀብታይን ተከትለዉ ትልልቅ ሞባይላቸዉን እያበሩ ከፎቅ ወጡ፡፡ ቶሎ ተመልሼ በመጀመርያ ለአምነአረጋዊ ምስጋና አቀረብኩ፡፡ ከዚያ ጽዳቱዋን ለታይን ጠብቂልኝ ብዬ በሩጫ ሄጄ ከነዚህ ጋር ከተመካከርኩ በሁዋላ በፍጥነት ስመለስ እንግዳ ማረፍያዉ ተከቦወል፡፡አራት መከላከያዎች መትረየስ ከወደረ መኪና ላይ ሆነዉ አፈጠጡብኝ፡፡ ከጣርያዉ ላይም የኮማንዶዎች ቆብ ትንሽ ትንሽ ይታየኛል፡፡ “እንዴ? እኔ ቀድሜ ያየሁትን ሌላዉ ሪፖርት አድርጎብኝ ይሆን ? “ ብዬ ክዉ አልኩ፡፡ ለመከላከያዊቹ በግልጽ ለመጠቆም ወደነሱ ስጠጋ “ ተመለስ!“ አለ አንዱ ጠመንጃ እንደደገነብኝ፡፡
“የመንግስት ምስጢር አለኝ፡፡ የተደበቀ ጁንታ እዚህ ዉስጥ አልጋ ይዞዋል፡፡“ አልኩ፡፡
አለቃዉ በፍጥነት ከመኪና ዘሎ ወረደና ተጠጋኝ፡፡ “የምን ጁንታ ነዉ?“
“ስዩም መስፍን ቆስሎ እዚህ ተደብቆዋል፡፡“ ወዲያዉ በእጅ ሬድዮዉ መነጋገር ጀመረ፡፡ ከዚያም ተቆጣና በፍጥነት ከዚያ እንድሄድ አዘዘኝ፡፡ ደንግጬ ሄድኩኝ፡፡ ወንድሜ ቤት አድሬ …“
“እንደምንም ሪፖርት ባታደርግ አንዱ ጉድ ያደርግህ ነበር፡፡ “ አለ ወንድሙ፡፡ ሀጎስ ብድግ ብሎ ራሱ ከማንቆርቆርያዉ ቀድቶ ጅዉ አደረገ፡፡
“ተነሱ! አደይ፣ ስንመለስ እከፍላለሁ፡፡“
“ዋ! ለኔ ሚኒባስ ነዉ የምትገዛ“ አለ ወንድሙ፣ “ለኔ ግን ጋራጅ ትከፍታለህ“ አለ ሌላዉ፡፡
በስጨት አለ፡፡ “ዋይ! ገንዘቡን ሁሉ ልትወሰወዱት ነዉ? አክሱም ሆቴል አይነት እሰራና ሁልሽም እዚያ ትቀጠርያለሽ፡፡“ ተያይዘዉ ወጡ፡፡
ይህን ተአምር ለማየት ከርቀት ተከተልኩዋቸዉ፡፡ ትንሽ እንደሄድን መንገዱ በሰዉ እየተጨናነቀ ሄደ፡፡ ስቀርብ ከአንግዳ ማረፍያ ፊትለፊት ያለዉ አስፋልት መንገድ ጢም ብሎዋል፡፡ እንደ ነብር አይናቸዉን ወዲያ ወዲህ በሚያበሩ ንቁ ሰራዊት መንገዱ ተወጥሮዋል፡፡ ወዲያዉ በወታደር የታጀቡ ሁለት መኪናዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየበረሩ ከእንግዳ ማረፍያዉ በር ላይ ቀጥ አሉ፡፡ ሁለት ሰዎች ወርደዉ ተጣድፈዉ ወደ ዉስጥ ዘለቁ፡፡ ላዕላይ ነዉ መሰለኝ በባትሪ የሚሰራ የድምጽ ማጉያ ይጎረጉራል፡፡ ከዚያም ወደ ዉስጥ የገቡት ተመለሱና ከፍ ካለዉ ደረጃ ላይ ቆሙ፡፡ ድምጽ ማጉያዉ ካስጮኸ በኋላ ያነገተዉን መነጋገርያ ወደ አፉ አቀረበ፡፡
“እንደምን አደራችሁ፡፡ በመጀመርያ ክቡር የትግራ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዴንት ዶክተር ሙሉ ነጋ አጭር መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡“ ብሎ መነጋገሪያዉን አቀረበላቸዉ፡፡ ሰላምታ ካቀረቡ በሁዋላ፣ ጦር ከፈታዉ ነገር የፈታዉ ብለዉ፣ የሚነዛዉን ወሬ ሁሉ ሳያጣሩ መቀበል እንደሌለባቸዉ አሳሰቡ፡፡ ወንጀለኛን ለመያዝ ህዝቡ ያለዉን ተነሳሽነት አደነቁ፡፡
ባለማይክራፎኑ “አሁን ደግሞ ክቡር የመቀሌ ከንቲባ አይተ አታክልቲ ሀይለስላሴ አጭር ንግግር እንዲያደርጉ አሳስባለሁ፡፡“ ከንቲባዉ ትያትርና ፊልም በመስራት በብዙዎች ዘንድ ስለሚታወቁ ብዙ ሰዉ ፊት ላይ ፈገግታ ታዬ፡፡
ከንቲባዉም፣ “ዶክተር ሙሉና አታክልቲ ታፍነዉ ተወስደዋል ተብሎ አገር ሲታመስ እንዳደረ ሁላችሁም የምታዉቁት ነዉ፡፡ ስለዚህ ክቡር ዶክተር ሙሉ የሰጡት ማሳሰብያ ትክክል ስለሆነ…“ ጩኸት አቁዋረጣቸዉ…
“አዉጡት ስዩም መስፍንን፣ አዉጡት ስዩም መስፍንን!“ መቀሌ ጨኸች፡፡
“እሺ እሺ ይወጣሉ፣ አንድ ደቂቃ፣ አንድ ደቂቃ .. “ አሉ ከንቲባዉ ፈገግ ብለዉ፡፡
ከህዝቡ ዉስጥ አንድ ጩኸት ተሰማ.. “እኔ ነኝ ያስያዝኩት! ቀርቤ ላስረዳ ይፈቀድልኝ፡፡“ ድምጹ የሀጎስ ግርግር መሆኑን ወዲያዉ አወቅሁ፡፡
ከንቲባዉ በርቀት ካዩት በሁዋላ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተንሾካሽከዉ “በል ቅረብ፣ አሳልፉት፡፡“ አሉ ፈገግ ብለዉ፡፡
ሀጎስ ግርግር በሚያምር አካሄድ በግርማ ሞገስ በተሰብሳቢዉ ፊት አልፎ ከንቲባዉን ጨበጠና ከጎናቸዉ ቆመ፡፡
“ስዩም መስፍን ይዉጣ ! ስዩም መስፍን ይታይ!“ ጩኸት፡፡
“አንድ ደቂቃ .. የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴ ኤታ አጭር ምልእክት….“ ጩኸት አቁዋረጣቸዉ፡፡
ከንቲባዉ ሳቅ እያሉ “እሺእሺ …“ ወደሁዋላ አየ፡፡ ተጣሩ፡፡ “ስዩም መስፍን ወደዚህ ፡፡“
ካፖርታቸዉን እያወለቁ ወደፊት መጥተዉ ፣ማስኩን አዉልቀዉ ድምጽ ማጉያዉን መታ መታ ሲያደርጉ አንደገና “ስዩም መስፍን ይዉጣ ! ስዩም መስፍን ይታይ!“ ጩኸት፡፡
“ይኸዉ ወጣሁ እኮ፡፡ የምታዩኝ እኮ መስፍን ስዩም ነኝ፡፡“ አሉ ሰዉየዉ ፈገግ እያሉ፡፡
ከንቲባ አትክልቲ ድምጽ ማጉያዉን ተቀበሉና “ክቡር የኢፌድሪ የሰላም ሚኒስትር ሚኒስትር ዴ ኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን፡፡ እንኩዋን ወደመቀሌ በሰላም መጡ እያልኩ አጭር ንግግር እንዲደርጉ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡“
እንደ ንብ የሚተም ድምጽ..
ሀጎስ ግርግር ሮጦ መነጋገርያዉን ነጠቃቸዉ፡፡ “ስዩም መስፍን ሲፈልግ እንደ እብድ፣ ሲፈልግ እንደቄስ ይሆን እንደነበረ ታዉቃላችሁ፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ሰላም ሚኒስቴ…
ተናግሮ ሳይጨርስ መቀሌ ሳቀች፡፡ ለሳምንታት አቁዋርጣ የነበረዉን ሳቅ በከፍተኛ ድምጽ ሳቀች፡፡
“ የሄ ሰበብ ሽልማት ልትከለክሉ ነዉ፡፡“ ብሎ ከንቲባዉ ላይ ሲፈጥ እየሳቁ አቀፉት፡፡
ዶክተር ሙሉ ነጋ ከመኪናቸዉ ገቢና አስገብተዉት እየሳቁ በረሩ፡፡
መቀሌ በፈገግት ፊት እያበራች ስትስቅ ዋለች፡፡ አቦ ስትስቅ እንዴት ያምርባታ! “መሳቅን የመሰለ ምን የሚጣፍጥ ነገር አለ!“ ይል ነበር ተስፋዬ ገሰሰ ነፍሱን ይማርና ከሳምንታት በፊት፡፡
