የኢትዮጵያ አጠቃላይ ብድር 51.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ይፋ ሆኗል

Date:

ኢትዮጵያ  በድጋፍ መልክ ከአሜሪካ በየዓመቱ  በመንግስት በኩል ፈሰስ የሚደረግ የ1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ የምታገኝበትን ስምምነት ሁለቱ አገራት መፈራረማቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለፓርላማ ተናግሯል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ይህን የተናገረው ከሰሞኑ የዘጠኝ ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የስራ ክንውን ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ብድር 51.8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ  33.5 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ብድር እዳ እንደሆነ እና  ቀሪው 18.3 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ የሀገር ውስጥ እዳ መሆኑን አቶ አህመድ አብራርተዋል።

ከ33.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ ውስጥ ደግሞ  22.1 ቢሊዮን ዶላሩ የፌደራል መንግስት እዳ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ቀሪው 11.5 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እዳ እንደሆነም አክለዋል።

ከሀገር ውስጥ ብድሩ ማለትም ከ18.3ቢሊዮን ዲላር ውስጥ ደግሞ 17.5 የፌደራል መንግስት እዳ እንደሆነ እና 0.8 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ነው ብለዋል አቶ አህመድ ።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች እዳ ዝቅ ያለበትን ምክንያት  አቶ አህመድ ሲያስረዱ በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት አብዛኛው ከንግድ ባንክ ተበድረው የነበረው ብድር ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር በመዞሩ በበጀት መከፍል በመጀመሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።

አጠቃላይ የኢትዮጵያ እዳ ሁኔታ በእሳቸው አገላለጽ “በጣም በጣም “ጤናማ እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው ያስረዱት ሚኒስትሩ የውጪ እዳ የመክፈል አቅማችንም “ከጊዜ ወደ ጊዜ “እየጨመረ ነው ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ብድር ደግሞ ጭማሪ አሳይቷል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል፡፡

ይህ ደግሞ ለማስተካከል በዘላቂ (sustainable) የፋይናንስ መርህን በመከተል የሚሰራ ስራ ይኖራል ነው ያሉት ሚኒስትር አህመድ።

በእዳ ክፍያን ክንውን ሪፖርታቸው ደገሞ በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥ እና የውጪ እዳ ክፍያ 463.4 ቢሊዮን ብር ተመድቦ የነበረ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአግልግሎት ክፍያን ጨምሮ 226.5 ቢሊዮን ብር ተከፍሏል።

እንዲሁም የውጭ ሃብት አሰባሰብን በተመለከተ በዓመቱ ከተለያዪ ተቋማት 4 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ማታቀዱን እንዲሁም በዘጠኝ ወሩ ደግሞ 3.1 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ታቅዶ ከዛ ውስጥ 2 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከእቅዱ በ1.1 ዶላር ያነሰ ተግኝቷል ተብሏል።

ይህም የእቅዱን 65.1 በመቶ ሲሆን ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ 914.2 ሚሊዮን ዶላሩ ከአለም ባንክ መገኘቱን አቶ አህመድ ተናግረዋል።

የውጪ ሃብት ግኝቱ በቀጣይ ሁለት ወራት ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስረዱት ሚኒስትሩ ባለፈው አሜሪካ ተደርጎ በነበረው የአልም ባንክ እና የገንዘብ ድርጅት ስብሰባ ላይ ለበጀት ድጋፍ ለአደጋ ምላሽና ለነዳጅ ማሻሻያ ማስኬጃ የሚያስችሉ ምላሾች መገኘታቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ ሪፖርት ያክላል።

የአሜሪካ የተራድዖ ድርጅት እርዳታ መቋረጥ የጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና የእቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ጫና መፍጠሩን ያስታወሱት ሚኒስትሩ በቅርቡ ድርድር በማድረግ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በዓመቱ በመንግስት በኩል ፈሰስ እንዲደረግ ከአሜሪካ መንግስት ጋር  የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል ብለዋል።

ይህም ስምምነት በቅርቡ በካቢኔ እንደሚጸድቅ አቶ አህመድ ጠቁመዋል።

ሸገር 102.1

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የሲ.ኤን.ኤን መስራች ቴድ ተርነር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የዓለማችን ግዙፍ የዜና አውታር ሲኤንኤን መስራች ቴድ ተርነር በ87...

ከ8 ሺህ በላይ ጥንታዊ የብራና ጽሑፎችን እና ሰነዶችን ወደ ዲጂታል ተቀየሩ

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት፣...

አቶ ዳውድ ኢብሳ ከምርጫው ራሳቸውን አገለሉ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በኦሮሚያ...

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ‹‹ሁሉን አቀፍ ስምምነት›› እንደምትፈልግ ገለጸች

ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነት ለማቆም ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው...