ቀዳማዊ ምኒልክ እና ሰሎሞናዊ ሥርወ-መንግሥት አመሠራረት! ዓይናለም ደበበ

Date:

ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ ሺህ ዓመት አካባቢ በስተ-ምሥራቅ እስከ ማዳጋስካር በስተ-ሰሜንና በስተ-ምዕራብ እስከ ግብፅና ኑብያ ጠረፍ እንዲሁም በስተ-ደቡብ እስከ ኒያንዛ (ቪክቶሪያ) ሀይቅ ድረስ በነበረው ሰፊ የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በነገሠችው ንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከኢየሩሳሌም፣ ከግብፅ፣ ከሕንድና ከዓረብ ሀገራት እንዲሁም ከቀሪው ዓለም ጋራ በምታደርገው መጠነ ሰፊ የሸቀጥ ልውውጥና ጠንካራ የንግድ ትስስር አማካኝነት ስመ ገናና ነበረች። የንግሥቲቱ የንግሥተ ሳባ ዝናም በዓለም ላይ ሁሉ እጅግ የናኘ ነበር። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል›› ባሉት የታሪክ መፅሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት:- ‹‹በንግሥተ ሳባ ዘመን የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በእየሩሳሌም ነግሦ ነበር። በዚያንም ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ እየሩሳሌም የሚመላለስ ታምሪን የሚባል ነጋዴ ነበርና እርሱ በእየሩሳሌም ያየውን የሰሎሞንን ስራ ሁሉ ስለነገራት በጆሮ ከመስማት በዓይን ማየት ይበልጣል ብላ ከአክሱም ተነስታ ወደ እየሩሳሌም ወረደች››፡፡

ታምሪን አምስት መቶ ሃያ ግመሎችን ይጭን የነበረ ሰባ ሦስት ያህል መርከቦች የነበሩት በዘመኑ ስሙ የገነነ ታላቅ ነጋዴ ነበር። ክብረ ነገሥት ላይ እንደሰፈረውም፡- ‹‹በዚያን ግዜ ጠቢቡ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤት ይሰራ ዘንድ ወደደ። ነጋዴዎችም መጥተው ከርሱ ወርቅና ብር እንዲቀበሉና እሱም ከእነሱ ለስራው የሚያሻውን እንዲቀበል በምሥራቅና በምዕራብ፣ በደቡብና በሰሜን ወዳሉት ሀገራት ነጋዴዎችን ሁሉ ላከ። ስለ ከበርቴው ኢትዮጵያዊ ነጋዴም በሰማ ግዜ ከዓረብ ሀገራት የሚያስፈልገውን ቀዩን ወርቅ፣ ጥቁርና የማይነቅዝ እንጨትና ሰንፔር የተባለውን እንቁ እንዲያመጣለት ሻተ››፡፡ ከዚያም ታምሪን የንጉሡን መሻት ፈፅሞ እንዳበቃ ንጉሥ ሰሎሞን የሚፈልገውን ሁሉ አስበልጦ ለታምሪን ሰጠው። ታምሪንም በሩቅ ሲነገር የሰማውን በስራ አጋጣሚ በቅርበት ሆኖ የተመለከተውን የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት በመቻሉ በእጅጉ ተደሰተ። እግዚአብሔር በሰጠው ክብርና ሃብትም ተገረመ።

በጠቢቡ ሰሎሞን ዘመን ወርቅ እንደ ነሃስ ብር እንደ እርሳስም ሆኖ ነበር። ነሃስ፣ እርሳስና ብረትም እንደ እንጨትና የዱር ገለባ ሁሉ ነበር። እግዝአብሔር ለንጉሥ ሰሎሞን በሰጠው ጥበብ ከእርሱ በፊትም ሆነ በኋላ የርሱን ያህል ክብርና ሞገስ የተጎናፀፉ ነገሥታት ይኖራሉ ለማለት አያስደፍርም።

ቀደም ተብሎ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የሰሎሞንን ጥበብ ክብርና ሞገስ በዓይኑ የተመለከተው ከበርቴው ነጋዴ ታምሪን ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በእየሩሳሌም ያየውን የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ ለንግሥተ ሳባ ነገራት። እርሷም ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብ ከታምሪን በሰማችው ሁሉ ተደነቀች። ልቧ በሀሴት እንደተሞላ ወደ እርሱ ለመሄድም ተነሳሳች። መቼም የጠቢቡ ሰሎሞንን ጥበብ ለመመልከት የእየሩሳሌምን ግዛት ለመጎብኘት ቢጓጉ የተገባ ነውና ንግሥተ ሳባም ብዙ ወርቅና ዕንቁ እንዲሁም በአይነቱ የተለየ ሽቶ ይዛ ከአክሱም ተነስታ ባሕረ-ነጋሽን አቋርጣ ከግዛቷ የመን ብትደርስ በዚያ ያሉ ባላባቶች ብዙ ስንቅ በግመሎቻቸው ጭነው ይጠባበቋት ነበርና በብዙ አጀብ ታጅባ እየሩሳሌም ገባች። ንጉሥ ሰሎሞንም በታላቅ ደስታና ክብር ተቀብሎ የማረፊያ ስፍራ ሰጣት።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ‹‹ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ›› ባሉትና በመጠኑ አነስ ብሎ ባጨቀው የምርምር ሀሳብ ገዘፍ ብሎ በቀረበው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ፅፈዋል።

‹‹አንዳንድ የሀገራቸውን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ምሁር ተብዬዎች፣ ንግሥተ ሳባ ወንድ ፍለጋ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ዘንድ እንደተጓዘች ይናገራሉ። ይሄ እስዋን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም መስደብ ነው። ንግሥተ ሳባ ብዙ ስጦታ ይዛ ወደ እየሩሳሌም የሄደችበት ዋንኛው ምክንያት የመልከፃዲቅ እና የኢትዮጵ ተወላጆችና ኢትዮጵያ፣ ይመጣል ብለው ለአንድ ሺህ ዓመታት የጠበቁትን ‘የሰላሙን ንጉሥ’ የእስራኤልን መሲሕ አግኝታ ለመባረክ ነበር። ሰሎሞን ጠቢብ ነው ሲባል ስለ እሱ ዝናም በጣም በመስማቷ እና የጥበብ አፍቃሪም በመሆኗ የእሱን ጠቢብነት ለማጣራትም በዘዴ እና በእንቆቅልሽ ከፈተነችው በኋላ እሱ የእስራኤል መሲሕ እንዳልሆነና እራሱም መሲሑን ገና እንደሚጠብቀው ተረዳች››፡፡

ንግሥተ ሳባ ዐፄ እስያኤልን አስወግዳ በነገሠች ግዜ በድንግልናዋ ፀንታ እንደምትቆይ ለኢትዮጵያውያን ቃል በመግባቷ ምክንያት፣ እንዳሰበው ፈጥኖ አብሯት ለመተኛት ያልሆነለት ንጉሥ ሰሎሞን ብልሃት ማሰስ ያዘ። ታድያ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ ንግሥተ ሳባ ጉብኝትዋን አጠናቃ ወደ ሀገርዋ ለመመለስ ስትሰናዳ ንጉሥ ሰሎሞን ለስንብት ባዘጋጀው ግብዣ ላይ ቅመምና ጨው የበዛበት ምግብ እንዲዘጋጅ አዘዘ። ግብዣው ተጠናቆ ንግሥተ ሳባ ወደ መኝታ ቤቷ ከመግባቷ በፊትም ንጉሥ ሰሎሞን ከርሱ ፍቃድ ውጪ አንዳችም ነገር እንዳታደርግ ቃል በማስገባት ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ፍቃዱን በገዛ ፍቃዷ በመጣሷ አብሯት ለመተኛት የፈቀደች ስለመሆኗ ተስማምተው ተለያይተው ወደየመኝታቸው ሄዱ። ሆኖም ግን ንግሥተ ሳባ የተመገበችው ምግብ ከባድ የውሃ ጥም ለቆባት ስለነበር አልችል ብላ እኩለ ለሊት ላይ ከንጉሥ ሰሎሞን መኝታ አቅራቢያ የተቀመጠውን ቀዝቃዛ ውሃ ለመጎንጨት ካለበት ብትሄድ አጅሬ ይጠባበቃት ነበርና በውላቸው መሠረት ይዟት ይተኛታል። በዚያም ለሊት ቀዳማዊ ምኒልክ ይፀነሳል። ከዚያም ንግሥተ ሳባ በእየሩሳሌም ለሦስት ወር ያህል ያደረገችውን ጉብኝት አጠናቃ የተፀነሰውን ልጅ እድሜው ሲደርስ ወደ አባቱ እንደምትልክለት ቃል በመግባት ሰሎሞንን ተሰናበተችው። ወደ ግዛትዋ ኢትዮጵያ ከገባች ከአንድ ወር በኋላም ቀዳማዊ ምኒልክ ተወለደ። እርሱም እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ በኢትዮጵያ የቆየውን የሰሎሞናዊ ስርወ-መንግሥት መሠረተ።

ምኒልክ ካደገ በኋላ አባቱ ማን እንደሆነ እናቱን ቢጠይቅ ‹‹አባትህ የእየሩሳሌም ንጉሥ ሰሎሞን ነው›› ብላ ንግሥተ ሳባ ብትነግረው በእጅጉ ተደሰተ። አፍላ የወጣትነት እድሜው ላይ ሲደርስም አባቱን ንጉሥ ሰሎሞንን የማየት ፍላጎቱ በእጅጉ አይሎበት ወደ እየሩሳሌም አቀና። ምኒልክ አባቱን ንጉሥ ሰሎሞንን ይመስል ነበርና ሰሎሞን ልጁን ባየ ግዜ እጅግ ተደስቶ ካለው የሞላና የተትረፈረፈ ሃብት ሩቡን ያህል ሸለመው። በእየሩሳሌምም የአይሁዳውያንን ስነ-መንግሥት፣ ስነ-ሀይማኖት፣ ስነ-ምግባራት፣ ስነ-አምልኮ እና ልማዶችን ሲማር ቆየ። ሦስት ዓመታትን ያህል በእየሩሳሌም ከቆየ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በመፈለጉ ንጉሥ ሰሎሞን ከቤተ-መንግሥቱ ወታደሮች፣ ባለሟሎችና አገልጋዮች መካከል አርባ ሺህ ያህሉን መርጦ እንዲያጅቡት ሰጠው። ከእነርሱም ውስጥ አስራ ሁለት ሺህ ያህሉ አይሁዳውያን፣ አንድ ሺህ ያህሉ ወርቅና ብር አንጣሪ የሆኑ ኢያቡሳውያን እና ሃያ ሰባት ሺህ ያህሉ የእየሩሳሌምና የጋዛ ነዋሪዎች የነበሩ የዮቅጣን ነገዶች ነበሩ።

ንጉሥ ሰሎሞን የእስራኤልን አምላክ ዘንግቶ ለባዕድ አማልክት ይሰግድ ነበርና በዚያ ያሉ ሌዋውያን ልባቸው በሃዘን ተሰብሮ ነበር። የቢንያም እና የአይሁድ ነገዶችም በሰሎሞን ስራ ቅሬታ አድሮባቸው ነበር። በዚህም በተቃውሞ ውስጥ የሚገኙት ሦስቱ ነገዶች አንድነት ፈጥረው ዋናውን ፅላት በመውሰድ አምሳያውን በቤተመቅደስ እንዲቀመጥ አደረጉ። ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፍቃድ ከምኒልክ ጋር ታቦቱን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ጀመሩ። ከእየሩሳሌም እስኪርቁ ድረስም ታቦቱን መያዛቸውን ምኒልክ እንዳያውቅባቸው በምስጢር ያዙት። ግዜው ደርሶም ምኒልክ የሆነውን ሁሉ ባወቀ ግዜ በመጀመሪያ ባደረጉት አዘኔታ ቢሰማውም እየቆየ ግን በአባቱ የተቆጣው የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ተቀብሎ ፅላቱን በደስታ ይዞ ከሀገሩ ኢትዮጵያ ገባ። የታቦተ ፅዮን አምላክ የአስርቱ ትእዛዛት ፀሀፊና የፅላቱ አስቀራጭ እስራኤልን ለቅቆ በኢትዮጵያውያን መሀል መኖሩንም አመላከተ።

በዚህ ሁኔታ ቀዳማዊ ምኒልክ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሲገባ ንግሥተ ሳባም ልጅዋ ከእየሩሳሌም በሰላም በመመለሱ እጅግ ተደስታ በታላቅ ድምቀት ተቀበለችው። መሳፍንቱንና መኳንንቱን ባላባቶችንም ሁሉ ሰብስባም ልጄን ምኒልክን በህይወት እያለሁ ላነግሠው እፈልጋለሁና እንድትቀበሉት ይሁን ብላ ብትነግራቸው መሳፍንቱና መኳንንቱ ሁሉ ሀሳቧን በደስታ ተቀብለው ለልጇ ለቀዳማዊ ምኒልክ ዘውዷን አወረሰች። በሊቀ ካህን አዛርያስ እጅም ተቀብቶ ነገሠ።

ቀዳማዊ ምኒልክ በአባቱ በንጉሥ ሰሎሞን ከመጠራት ይልቅ በአያቱ በንጉሥ ዳዊት መጠራትን ይመርጥ ነበር። ከአባቱ ከሰሎሞን ይልቅም በአያቱ በዳዊት ታላቅነት ኩራት ይሰማው ነበር። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ቀደም ሲል በጠቀስኩት መፅሐፋቸው ላይ እንደፃፉት፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ስልጣን እንደተቆናጠጠ ከጋዛ በአንድነት ሆነው ከመጡት በተለይም እያቡሳውያን የሚግባቡበትን የግዕዝ ቋንቋን ለመንግሥቱ አዋለ። አጃቢዎቹንም ‹‹አግአዚ›› ብሎ ሰየመ። ስር ነቀል ለውጥ በማድረግም የዘውዱን አርማ የይሁዳ አንበሳን ምስል አደረገ። በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያን ሃያ አምስት ዓመት ገዝቶም በተወለደ በአርባ ዘጠኝ ዓመቱ አርፎ አክሱም ከእናቱ ከንግሥተ ሳባ መቃብር አጠገብም ተቀበረ።

የኛ የኢትዮጵያውያን ታሪክ እንዲህ ያለ ሆኖ፣ በታሪካችን መኩራት እንዲያም ሲል ዛሬ ‹‹ሀያል ነን!›› ለሚሉን ሀገራት ዓርዓያ ሆነን መገኘታችንን ማስመስከር ሲገባን፣ ባስነዋሪ አመለካከቶች በተወጠሩ ለዘመኑ በማይመጥኑ ኋላቀርና ግዴለሽ እንዲሁም ደካማና ስግብግብ በሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ሀሳብ ተጠምደን ስንንገላታ መገኘታችን እጅግ ያሳዝናል። በቸር ያቆየን!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...