ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነርቭ፣ የወገብ፣ የዲስክ መንሸራተት (የጀርባ አጥንት) ተያያዥነት ያላቸው ሕመሞች ሳቢያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችን እያሰቃየ ይገኛል። የእነዚህ በሽታዎች መንስኤ ‹‹እንዲህ ነው›› ተብሎ የሚታወቅ በቂ ምክንያት ባይኖርም ነገር ግን ዲስክ መንሸራተት ከባድ እቃዎችን በማንሳት፣ ስልክ አዘውትሮ ሲጠቀሙ ጎንበስ ማለት፣ መኪና ብቻ እያሽከረከሩ መዋልና የእግር መንገድ አለማድረግ፣ በአደጋና በድብደባ ወዘተ የበሽታው ተጠቂ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከጠቀስኳቸው ሕመሞች በሁለቱ ማለትም በዲስክ መንሸራተትና በነርቭ ለከፍተኛ ስቃይ ከተዳረጉት አንዱ ነኝ! በተለያዩ ሆስፒታሎች ላለፉት ረጅም አመታት ምርመራ ከማድረግ ባሻገር አዲስ አበባን ጨምሮ አጎራባች ከተሞች ድረስ እየሄድኩ በሽታውን ‹‹ይፈውሳሉ›› የተባሉትን ያለመታከት ለማግኘት ሞክሪያለሁ፡፡
ቅድሚያ ያደረኩት ለዲስክ መንሸራተት ምርመራ ማድረግ ነበር። ቦሌ በሚገኝ አንድ ከፍተኛ ሆስፒታል ለካርድ፣ ለኤክስሬይ ምርመራ በድምሩ አምስት ሺህ ብር ስከፍል፣ MRI ደግሞ 13 ሺህ ብር ከፈልኩ። የምርመራ ውጤቱን በደብዳቤና በሲዲ ጭምር ይዤ ሰዎች የሚጠቁሙኝ ቦታ መዞር ጀመርኩ። በተጨማሪ ብዙ አድማጭ – ተመልካች አላቸው በሚባሉ አንዳንድ የቲቪ ‹‹መዝናኛ›› ሚዲያዎች ‹‹ታዋቂ የዲስክና የነርቭ ፈዋሽ፣ አዳኝ›› ብለው ያቀረቧቸው ግለሰቦች (አንዳንዶቹ ዶክተር ብለው ለራሳቸው ማእረግ ሰጥተዋል) እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ‹‹ታዋቂ ፀሐፊ›› የተባሉ በሚለቀልቁላቸው ‹‹አዳኝ ፈዋሽ ተብዬዎች›› ዘንድ መሄድ ቀጠልኩ፡፡
ሰበታ መንገድ፣ የካ አባዱ፣ ሳር ቤት፣ ወለቴ፣ ኮተቤ፣ ለቡ፣ ቃሊቲ… ወዘተ እግሬ እስኪቀጥን ከተመላለስኩባቸው ይጠቀሳሉ። ቅድሚያ ከ20 እስከ 80 ሺህ ብር መክፈል ግድ ነው! ሰበታ መንገድ የሚገኘው ሰው ዘንድ ለሕክምና በየቀኑ የሚጎርፈው ሕዝብ በሺህ የሚቆጠር ሲሆን ሁሉም ታማሚ የሚሄደው በአንድ ሚዲያ ላይ ‹‹ፈዋሽ ናቸው›› ተብሎ በመነገሩ ነበር – የታማሚው ቁጥር በእጥፍ እንዲጨምር ያደረገው። ተበድረው፣ ያላቸውን ጥሪት አሟጠውና ሸጠው፣ እርዳታ ጠይቀው፣ ደም ተፍተው ሰርተው ‹‹ፈውስ ፍለጋ›› የሚመጡ ታማሚዎች ሰባና ሰማኒያ ሺህ ብር ቅድሚያ ከከፈሉ በኋላ ‹‹ሐኪም ነኝ›› የሚለውን ማግኘት የሚችሉት ሦስት የቀጠሮ ቀናት ብቻ ነው፡፡ በቅጥር ግቢው የሚገኙ ወጠምሻ ጋርዶችን አልፎ መግባትና ሰውየውን ማግኘት አይቻልም፡፡ ‹‹ከገንዘቤም ከሕክምናውም አልሆንኩም›› ብለው የሚያማርሩ እጅግ ብዙ ታማሚዎች ሲሆኑ ‹‹ፈዋሽ ነኝ›› የሚለውን ግለሰብ የማግኘት እድል ያገኙ ሰውየው የሚሰጣቸው መልስ እጅግ አስገራሚና አሳዛኝ ነው ፤ የሚሰጠው ምላሽ ‹‹የሚያዘኝ አምላክ ላንተ/ላንቺ የፈውስ ኃይሉን ሊሲጠኝ አልቻለም›› የሚል ነው። ገንዘብ እንዲመለስላቸው የሚጠይቁትን በጋርዶቹ ገፍትሮና አዋርዶ ከግቢው ለቀው እንዲወጡ ያስደርጋቸዋል። አብዛኞቹ ማለት ይቻላል ይህ እየተፈፀመባቸው ከፈውስም፣ ከገንዘባቸው ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የዚህ ሰለባ የሆኑ፣ በአስር ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ የተበሉ በርካታ ታማሚዎችን በአካል አግኝቼ አነጋግሪያለሁ፡፡ ሳግ እየተናነቃቸውና እንባ እያፈሰሱ በምሬት ሃዘናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የእነዚህን ወገኖች ሃሳብ የሚያጠናክር ነጥብ የምናገኘው ‹‹ፈዋሽ ነኝ›› የሚለው ግለሰብ በቀረበበት ‹‹ሰይፉ ሾው›› ሚዲያ ላይ በዩቲዩብ ከሥር የተፃፉ የበርካታ ታማሚ ተበዳዮች አስተያየት የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ከነዚህም ‹‹በእኛ የደረሰ ግፍና በደል በእናንተም እንዳይደርስባችሁ፣ ገንዘባችንን ተበልተን መሄጃና መድረሻ አጥተን፣ የት ሄደን ፍትህ እንደምንጠይቅ ግራ ገብቶን በሃዘን ቁጭ ብለናል፣ ስለዚህ ሌሎች ታማሚ ዜጎች ተጠንቀቁ፣ ከእኛ ተማሩ›› የሚል ይዘት ያላቸው አስተያየቶች ይገኛሉ።
በየካ አባዱም ሌላው ‹‹ፈዋሽ ነኝ›› ባይ እናገኛለን። በስመ አክትቪስትነት ከሚነግዱ ኮሚሽን ተከፋዮች የሰውየውን የሌለ ‹‹ሥም፣ ዝና፣ ፈዋሽነት›› እየለጠጡ በማኅበራዊ ሚዲያ እየለቀለቁ እንዲሁም ታማሚዎችን አነፍንፈው እያገኙና የተጠቀሰው ቦታ እንዲሄዱ በሹል ምላሳቸው እያሳመኑ ምስኪን ወገኔን ኪስ ያራቁታሉ፡፡ ታማሚው ቅድሚያ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር እንዲከፍል ከተደረገ በኋላ ሳይማር ‹‹ዶክተር›› የሚል ማእረግ በጮሌ ደላሎቹ የተሰጠው ግለሰብ ጋ ይቀርባል። አለብላቢ ምላሱ አይጣል ነው፤ የታዋቂ ሰዎችን ስም እየጠራ ‹‹እከሌን የፈወስኩት እኔ ነኝ፣ እነ ማንትስ የተባሉ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ድረስ መጥተው ተፈውሰው ሄደዋል›› እያለ የፈጠራ ውሸቱን ይደረድራል። የሚገርመው ከሚጠቅሳቸው ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ሁለቱ በጭራሽ እንደማያውቁትና ደላሎቹ ‹‹እሱ ዘንድ ሂዱ›› ሲሏቸው እንዳልሄዱ ሲናገሩ፣ አንዱ ደግሞ ‹‹አንድ ቀን ነው ያገኘሁት፣ ሁኔታው ስላላማረኝ መልሼ ማግኘት አልፈቀድኩም›› ይላል። አንድ ታማሚ 50 ሺህ ቅድሚያ ሲከፍል ጮሌ ደላሎቹ ኮሚሽን 7,500 (ሰባት ሺህ አምስት መቶ) ብር ኮሚሽን ይወስዳሉ። ታማሚው ከከፈለው ገንዘብ በተጨማሪ ለትራንስፖርት የሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው። ርቀቱና መጉላላቱ እንዳለ ሆኖ! እነዚህ ተደምረው ታማሚው ተስፋ ቆርጦ ይተወዋል።
አንድ የራዲዮ ስፖርት ጋዜጠኛ በቅርቡ የገጠመው ማንሳቱ ግድ ይላል፡፡ ጋዜጠኛው የታመመው እና ሐኪሞች በምርመራ ያሳወቁት ሌላ ሲሆን ደላሎቹ ግን የካ አባዱ አጭበርባሪው ጋ እንዲሄድ ያግባቡታል፣ ፈውስ እንደሚያገኝ ይሸነግሉታል። ለጋዜጠኛው ከውጭና ከአገር ውስጥ የተሰበሰበ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዳለ አውቀዋል። ቁጭ ይበሉ ‹‹ፈዋሽ ነኝ›› ባይ ዘንድ ታማሚው ይሄዳል። ‹‹በአጭር ጊዜ እፈውስሃለሁ፣ ችግርህ ዲስክና ነርቭ ነው፣ ቅናሽ አድርግልሃለሁ፣ 400 መቶ ሺህ ብር ቅድሚያ ትከፍላለህ›› ይለዋል በምላጭ ምላሱ። ታማሚው ጋዜጠኛ በቶሎ መፈወስ ስለሚፈልግና ስለሚጓጓ እሺታውን ሲገልፅለት አጭበርባሪው ከእነ ግብረአበሮቹ ‹‹አገኘነው፣ በላነው›› እያሉ በልባቸው ሳይቋምጡ አልቀረም ፤ ምኞታቸው በባዶ ቀረ እንጂ! ጋዜጠኛው ገንዘቡ እንዳይበላ የመከሩት ሰዎች ሐሳብ ሰምቶ ቀረ። አጭበርባሪውና ደላሎቹ ደጋግመው ቢደውሉም ስልክ ሳያነሳ ‹‹ነቅቻለሁ›› ብሎ ኩም አደረጋቸው። በሆስፒታል ሕክምና ተከታትሎ ጤንነቱ ለውጥ እያመጣ ሄደ!..
የወለቴው ‹‹ዶክተር›› ነኝ ባይ ደግሞ ለየት ይላል። እሱም ሳይማር ለራሱ ያከናነበው ሲሆን ታማሚው ‹‹ዶክተር›› እያለ ካልጠራው የሚከፋው ዐይነት ሰው ነው። ‹‹የመፈወስና ማዳን ሥልጣን ከላይ ነው የተሰጠኝ›› ይላል። ክብ ቅርፅ ባለው አሎሎ አይነት ድቡልቡል ብረት የታመመውን ቦታ በኃይል እያሽከረከረ ለሦስት ደቂቃ ገደማ ካሸው በኋላ ‹‹ተፈውሰሃል›› ይላል። የተለየ የሚያደርገው ይህን ያክል ክፈል አይልም። ‹‹ከላይ የተሰጠኝ ችሮታ ስለሆነ ደስ ያለህን ክፈል›› ይለሃል። ታማሚው ኪሱ የፈቀደውን ይሰጣል። ‹‹ተፈወስኩ›› የሚል ማግኘት ግን ዘበት ነው!
የቃሊቲው ደግሞ አስደንጋጭ ነው! የእጅህን መዳፍ ጨብጦ ይዞ ‹‹ነርቭና የአጥንት ህመም አለብህ፣ እጀ ሰብ፣ ሰላቢ፣ አባይ ጠንቋይ፣ መተት ተደርጎብሃል ወይም አልተደረገብህም›› ይልሃል። እሱም ሳይማር ‹‹ዶክተር›› የሚል ስያሜ ለራሱ ሰጥቷል። ‹‹ይፈውስሃል›› ብሎ የሚሰጥህ ከቅጠልና ምንነቱ ከማይታወቅ ሥራ ሥር ‹‹የተጨመቀ›› ብሎ የሚጠጣ ፈሳሽ ነው። ፈሳሹ በሰውነት ውስጥ ገብቶ የሚያደርሰውን ጉዳትና ሌላ ተጨማሪ በሽታ ሊያሳድር (ሊፈጥር) እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ አያስገባም። ምክንያቱ ደግሞ የሚመለከተው አካል ምርመራ ያላደረገበት፣ ማረጋገጫና እውቅና ያልሰጠበት ስለሆነ!
ወደ ለቡ አቅጣጫ ስትሄድ ሌላ ቁጭ በሉ ታገኛለህ። የካርድ ከፍለህ ስታበቃ ‹‹ፈዋሽ ነኝ›› የሚለው ግለሰብ ዘንድ ትቀርባለህ። የሰውነት አካልህን እየነካካ ‹‹ስንፈተ ወሰቢ፣ ሌሊት መቃዠት፣ ሽንት መቆራረጥ፣›› ወዘተ እያለ ከሕመምህ ጋ ምንም ግንኙነት የሌላቸው ጉዳዮች ይዘርዝርልሃል። ‹‹አባይ ጠንቋይ ቤት ነው እንዴ የመጣሁት?›› ብለህ ራስህን ብዥታ ውስጥ ገብተህ እንድትጠይቅ ያደርገሃል። ይህን ካለህ በኋላ ‹‹በቶሎ ትፈወሳለህ፤ 40 ሺህ ብር ክፈል›› ይልና ካሸርው ጋ ክፍያውን እንድትጨርስ ትእዛዝ ጭምር ይሰጥሃል። አፈ ጮሌው ያለህን ከከፈልክ በኋላ እፈወሳለሁ ብለህ ስትጠብቅ ወፍ የለም! በዚህ ዐይነት መልኩ ሁሉም ‹‹ፈዋሽ›› ነን ባዮች በታማሚው ሕብረተሰብ ክፍል እያታለሉ መጠነ ሰፊ ሽቀላና ዝርፊያ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጽሑፌን ሳጠቃልል ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ በማቅረብ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውና ያልተጠቀሱ ‹‹ፈዋሽ አዳኝ ነን›› ባዮች በሕመም በሚሰቃየው ማኅበረሰብ ላይ የሚፈፅሙትን ማጭበርበር አያውቁትም ይሆን!? ‹‹ዶክተር›› እያሉ ለራሳቸው የውሸት ማእረግ እየሰጡ በአደባባይ የማጭበርበር ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ማነው ፈቃድ ወይም እውቅና የሰጣቸው!? በአስር ሺህና በመቶ ሺህ የሚበሉ ታማሚ ወገኖች እስከመቼ ነው በእነዚህ የአደባባይ ቁጭ በሉ አጭበርባሪዎች ጥሪቱን እየተበላ የሚቀጥለው!? በ90 ዎቹ መጨረሻ ዓመታት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አንድ ትእዛዝ ወይም መመሪያ ይፋ ተደርጎ ነበር። ‹‹የባህል ሕክምና ፈዋሽ ነን የሚሉ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና ያልተሰጣቸው አካላትን ማስታወቂያ ማስነገርም ሆነ በጋዜጣ እና መፅሄት ማውጣት ክልክል ነው›› የሚል ጥብቅ ሕግ መደንገጉን አስታውሳለሁ። ይህን መመሪያ ጥሶ የሚገኝ ሚዲያ በሕግ እንደሚጠየቅ አያይዞ አስታውቆ ነበር።
ከዚሁ ጋ በተያያዘ ‹‹የኢትዮጵያ የአጥንትና የአደጋ ሕክምና ስፔሻሊስቶች ብሔራዊ ማኅበር›› ያደረገውን ጥናት ተመርኩዞ በይፋ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ ለአጥንትና ለመገጣጠሚያ ጉዳቶች በሚሰጥ የባሕል ሕክምና የሚከሰቱ ውስብስብ የጤና ችግሮች፣ ቋሚ የአካል ጉዳትና እስከ ሞት የሚያደርሱ መሆናቸውን በመግቢያው ይጠቅሳል። የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኤፍሬም ገብረሃና እንዳሉት ‹‹በአገራችን ውስጥ በትክክለኛ ሕክምና በቀላሉ መታከምና መስተካከል የሚችል ቀላል ጉዳት፣ በባሕላዊ ሕክምና ምክንያት ለሞትና ለአካል መጉደል ምክንያት ሆነዋል›› ይላሉ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአጥንት ሕክምና በመስፋፋቱ፣ ከባህላዊ አጥንት ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮች መቀነስ ሲገባቸው በተቃራኒው እየጨመሩ መሆናቸውን የሚገልፁት ፕሬዚዳንቱ፣ በጤና ተቋማት ውስጥ በየእለቱ በርካታ ታማሚዎች ቀላል የሚባል የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ፣ ወደ ባሕላዊ የአጥንት ሕክምና በመሄድ ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ተጋልጠው ሲመጡ ማየት የተለመደ ነው ብለዋል። ጥናቱ ሲደረግ በወጌሻ ሕክምና የተጎዱ ታካሚዎችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ከማድረጉ በተጨማሪ ከስድስት የተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ ስምንት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን ያካተተና ከመቶ በላይ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስቶች፣ ሀኪሞችና ሬዚደንት ሐኪሞች እንደተሳተፉበት ታውቋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሐኪም እንዲሁም የጀርባ አከርካሪ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር መንግሥቱ ገ/ዮሐንስ እንዳሉት ‹‹ጥናቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያና በአገር አቀፍ ደረጃ በአስር ከተሞች የሚገኙ ከሦስት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተካተቱበትና ችግሩን በጥልቀት ለመፈተሽ የተሞከረበት ነው። ከጤና ተቋማት በተሰበሰበ መረጃ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 460 ሕፃናት በጥናቱ የተካተቱ ሲሆን፣ የጥናቱ ዋና ግኝት እንደሚያሳየው ሕፃናት ከአዋቂዎች የበለጠ ከፍተኛ ለሆኑ ውስብስብ ጉዳቶች የተጋለጡ ናቸው›› ብለዋል። የጥናቱ ዳሰሳ ከሞላ ጎደል ይህን ሲመስል እንደዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ትዝብት ግን ‹‹ጥናቱ መፍትሔ አመላካች›› ሆኖ አላገኘሁትም! አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ‹‹የባሕል ሐኪሞች ነን›› እያሉ ከላይ የተገለፀውን ችግር በታማሚዎች ላይ የሚፈፅሙ አጭበርባሪዎችን በሕግ አግባብ የሚጠየቁበትን፣ ጉዳያቸው በጤና ሚኒስቴር የሚታይ ከሆነም ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግ፣ ‹‹ዶክተር›› የሚል ሳይማሩ ያለእውቀት ለራሳቸው ማእረግ ጭነውና በግልፅ ቢሮ ከፍተው፣ ታፔላ ለጥፈው፣ ማስታወቂያ እያስነገሩ የሚነግዱ ጨካኝ አጭበርባሪዎችን በጤና ቢሮ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ወዘተ… የመፍትሔ አቅጣጫ በጥናቱ ባለመመልከቱ ጎዶሎ ያደርገዋል። ለማንኛውም በታማሚ ዜጎች በሚነግዱ የአደባባይ ግፈኛ አጭበርባሪዎች ክትትል ተደርጎ አስቸኳይ እርምጃ ይወሰድ ስንል ለሚመለከተው አካል ደጋግመን ጥሪያችንን እናቀርባለን!
