፩. መነሻ፡- አጭር ምንባባዊ ድራማ
አባት ቴሌቪዥናቸው ፊት ቁጭ ብለዋል፡፡ ‹‹በቤኒሻንጉል ክልል ሕገ ወጥ መሣሪያ በታጠቁ ግለሰቦች፣ ዜጎች እየተገደሉና ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡›› ይላል የከፈቱት የመጀመሪያው ጣቢያ ዜና፤ የቴሌቪዥናቸውን ‹ሪሞት› በጣታቸው ተጭነው ቀየሩት፤ ‹‹በቅርቡ በጣለው ኃይለኛ ጎርፍ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች… ›› አሁንም ጣቢያውን ቀየሩት፤ ‹‹የድምፃዊ አጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ… ›› ሲል፣ ደንግጠው ጣቢያውን ያሳለፉት መስሏቸው ቴሌቪዥኑን ሙሉ ለሙሉ አጠፉት፡፡ (ከድርጊቱ በኋላ ለአፍታ ተክዘው ለራሳቸው እንዲህ አሉ፤ ‹‹ወይ ጉድ! ምን አስደነገጠኝ!? የድምፃዊ አጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ምን ያልሆንነው ነገር አለ!?››)
ቴሌቪዥኑን ከእንደገና አበሩትና ወደ ቀጣዩ ጣቢያ ተሸጋገሩ፤ ‹‹የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ ለመጀመር… ›› ይላል ይኼኛው ደግሞ፤ አሁንም በብስጭት ተጫኑት፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል እየታየ ያለው ህገ ወጥ የመሬት ወረራን መንግሥት… ›› ኦኦይ! ሪሞቱን አጥብቀው ተጫኑት፡፡
‹‹በመሬት መናድ ከቤት ንብረታቸው የተፈላቀሉ ሰዎች የመንግሥትን ድጋፍ ቢፈልጉም…›› ኤጭ! ቀየሩት፡፡ ‹‹በኮሮና የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ ማሻቀቡን ተከትሎ… ›› አሁንም ሪሞታቸውን ተጫኑት፡፡ ‹‹በመላው አገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው የአንበጣን መንጋ ለመከላከል ኅብረተሰቡ… ›› ወይ ጉድ! በፍጥነት አሳለፉት፡፡
‹‹ሰሞነኛ ጉዳይ፡- ከአርባ ዓመታት በላይ የደመራ በዓል ሲያከብሩበት ከነበሩበት ቦታ እንዳያከብሩ የተከለከሉት ምዕመናን በክልሉ መንግሥት ላይ ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡›› በኀዘኔታ ራሳቸውን ነቅንቀው ወደ ቀጣዩ ጣቢያ ተላለፉ፡፡
‹‹መጪው ምርጫ ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል? በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተደረገ ውይይት›› በመሰላቸት ሪሞቱን ተጫኑት፡፡
‹‹ማነህ ትንሹ! ኧረ ትንሹ!›› ትንሹ ልጃቸውን እየተጣሩ ነው፤ ‹‹ትንሹ!››
‹‹አቤት!›› አለ ልጅ፣ እሳቸው ወዳሉበት ሳሎን እየመጣ፡፡
‹‹እስኪ ቀይረው ይኼን ቴሌቪዥን!?›› ሪሞቱን እየሰጡት፡፡
‹‹ምን ጣቢያ ላድርግልህ?››
‹‹የጠቅላይ ሚንስትሩ ሽርሽር ላይ ወይም ይኼ እየተሠራ ያለውን አረንጓዴ ፓርክ የሚያሳይ ጣቢያ ካለ፣ እርሱ ላይ ብቻ አድርግልኝ!››
‹‹የቱ ላይ?›› ልጅ ግራ በመጋባት ጠየቀ፡፡
‹‹ይኼ ብልጭ ድርግም የሚል መብራት፤ ፏፏቴ ምናምን ያለበት መዝናኛ የሚታይበት ጣቢያ ነዋ!››
‹‹አሁን እኮ ላይኖር ይችላል፡፡››
‹‹ዝም ብለህ ፈልግማ፡፡ እሱን ሳይ ነው አገር ሰላም የሆነ የሚመስለኝ!››
ልጅ የአባቱን ትእዛዝ ተቀብሎ የተባለውን ጣቢያ ፈለገ፡፡ ነገር ግን አላገኘም፡፡ በአጋጣሚ አሁንም ዞሮ ዞሮ ስለምርጫ ውይይት የሚያቀርበው ጣቢያ ላይ መጣ፡፡ አባት ተበሳጩ፡፡
‹‹አገር ሳይረጋ ምርጫ እንዴት ብሎ!? …ቀይረው!›› በጩኸት ቤቱን አናወጡት፡፡
* * *
ድራማው ተፈፀመ፡፡
መቼት፡- በዚህ ሳምንት ውስጥ፤ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ጓደኛ ቤት፤
ድራማውን የተጫወቱላችሁ፡- የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ጓደኛ እና የጓደኛው አባት፡፡
፪. ድኅረ ታሪክ
በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ቢሮ ውስጥ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉ አዳዲስ አባላት ምልመላ እየተካሄደ ነው፡፡ አንዱ ጭቁን ወደ አንዱ ፓርቲ ቢሮ ሄደ፡፡
‹‹የፓርቲያችን አዲስ የቅስቀሳ አባል ለመሆን ነው የመጣኸው?›› ጠየቀ መልማይ፡፡
‹‹አዎ!›› መለሰ ጭቁኑ፡፡
‹‹መልካም፤ እንኳን ደህና መጣህ፡፡ ወደ ምርጫ ቅስቀሳው ከመሄድህ በፊት ስለ ፓርቲያችን ብዙ ማወቅ የሚገቡህ ነገሮች አሉ፡፡ ፓርቲያችን የሕግ የበላይነት ለማስፈን የሚታገል እና ከሞላ ጎደል እንዲሰፍን ያደረገ፤ ፓርቲያችን በብሔር ብሔረሰቦች መካከል እርስ በርስ መተሳሰብና መቀራረብ እንዲኖር፣ በአገራችን ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የታገለና ታግሎም ለውጥ ያመጣ፤ ፓርቲያችን ሙስናንና ዝርክርክ ቢሮክራሲያዊ አሠራርን ለማቆም የሚሠራ፤ ፓርቲያችን የዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን በርትቶ የሚታገል፤ ፓርቲያችን የሃይማኖቶች እኩልነት … ››
‹‹ይቅርታ ጌታዬ አልገባኝም!›› ሲል ጭቁኑ ካድሬውን አቋረጠው፡፡
‹‹ምኑ ነው ያልገባህ?›› ካድሬው ኮስተር ብሎ ጠየቀ፡፡
‹‹ተሳስቼ ለሌላ አገር ፓርቲ ስቀሰቅስ እንዳልውል!››
‹‹እንዴት?››
‹‹ይሄን አሁን ያሉትን ነገር ሁሉ የሚሠራው ፓርቲ የምር አገር ውስጥ በሕይወት አለ ወይ!? ነው ወይስ ሌላ ዓለም ላይ ያለ ነው!?››
* * *
ሰሞኑን፣ ምርጫ ምርጫ የሚለው የሚዲያ ወሬ በትዝታ እያዳፋ ወደ አይረሴው የዘጠና ሰባቱ ምርጫ እየወሰደን ነው፡፡ (ከላይ በድኅረ ታሪኩ ክፍል ያነበባችሁትም በምርጫ ሰሞን ዕቅደ – ብዙ የሆኑትን ገዢም ተገዢም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመተቸት የተፈተለ ነው፡፡)
ከአምና ሲንከባለል የመጣውን ስድስተኛውን አገራዊ የፖለቲካ ምርጫ ለማካሄድ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዱብዱብ እያለ ነው፡፡ ምርጫው ላይ እንደሚሳተፉ ቀደም ብለው ያሳወቁት ፓርቲዎችም ያን ያህል የጎላ መነቃቃት ባይታይባቸውም የተወሰኑት ተፍተፍ ማለት ጀምረዋል፡፡
የእኔ ብጤው ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በቅጡ ውሉ ባለመታወቁና (ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ቢልም) የክልሎች ሰላም ያልተረጋጋ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥጉን ይዞ እንዲህ በማለት ያንጎራጉራል፤ ‹‹መጀመሪያውኑ ለምን ምርጫው ተራዘመ? አሁንስ ምን ተገኝቶ ይካሄዳል?››
‹‹እና ምርጫው ሳይካሄድ ይቅር?›› ባይ አጥብቆ ሞጋች ቢመጣ፣ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ስላለፉት “አምስት ምርጫዎች” ፈገግ ብሎ የሚያስታውሰው መልካም ትዝታ የለውምና፣ ‹‹እንጃላችሁ! ምርጫ በመጣ ቁጥር ስጋት እና ውጥረት እንጂ ምን አተረፍን!?›› የሚል ትሁት መልስ ይመልሳል። (ትሁትነት ያደግንበት ስለሆነ)
መዝጊያ መጠይቅ
ለሚከተለው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ምረጥ፡፡
በቀጣይ ሊካሄድ የታሰበው ስድስተኛው አገራዊ የፖለቲካ ምርጫ ምን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል?
ሀ. ግፍ ለ. ሰደፍ
ሐ. ሰነፍ መ. ደግፍ
ሠ. ተነፍ ረ. መልሱ አልተሰጠም፡፡
ሰ. ሁሉም መልስ ነው፡፡
የምኅፃረ ቃሉ መግለጫ፡-
– ግፍ፡- ግልፅ እና ፍትሐዊ – ደግፍ፡- ደሞክራሲያዊ፣ ግልፅ እና ፍትሐዊ
– ሰነፍ፡- ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ – ሰደፍ፡- ሰላማዊ፣ ደሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ
– ተነፍ፡- ተዓማኒ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ
