ለዓለም የንግድ ሰንሰለት እጅግ ስትራቴጂካዊ በሆነው የሆርሙዝ ባህረ ወሽመጥ ላይ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ወታደራዊ ግጭት ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገር ጠንካራ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገለጸ።
የአሜሪካ ባለስልጣናት እና የኢራን ወታደራዊ አመራሮች እርስ በእርስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማን በመጣስ አንዳቸው ሌላኛቸውን በመወንጀል ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል፤ ይህም የዓለምን የነዳጅ ገበያ እና የንግድ እንቅስቃሴ የከፋ ስጋት ላይ ጥሎታል።
አልጀዚራ እና ሮይተርስ እንደዘገቡት ከሆነ ደግሞ በደቂቃዎች ልዩነት የነዳጅ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። የፕሮጀክት ፍሪደም መጀመር እና መቋረጥ ለዚሁ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባህር ወሽመጡ መዘጋት ምክንያት ታግተው የሰነበቱ መርከቦችን ለማስወጣት ፕሮጀክት ፍሪደም የተሰኘ ወታደራዊ ዘመቻ አውጀው የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ግን ዘመቻው ለጊዜው እንዲቆም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ይህ ውሳኔ የተላለፈው ከኢራን ተወካዮች ጋር “የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ትልቅ እድገት ታይቷል” በሚል ምክንያት እንንደነበር መሆኑ ተገልጿል ። ይሁንና አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የባህር ኃይል እገዳ አሁንም እንደቀጠለች ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት የአየር መከላከያ ሥርዓታቸውን የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመከላከል፣ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል በድጋሚ ማንኛውም መርከብ ያለ እሱ ፈቃድ በባህር ወሽመጡ ለማለፍ የሚሞክር ከሆነ “ቆራጥ ምላሽ” እንደሚሰጥ በማስጠንቀቅ ዝቷል።
ኢራን፣ አሜሪካን “ሲቪል አካባቢዎችን ኢላማ አድርጋለች” በማለት የከሰሰች ሲሆን፣ በቴሄራን እና በአካባቢው የጸረ-አውሮፕላን መከላከያ ሥርዓቶች በንቃት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ግጭት ከፍቶ፣ እየተመታሁ ነው ማለት ምንድነው የሚል አንድምታ ያለው መግለጫ ሰጥቷል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሁለቱ ሀገራት የተቀናጀ ድርድር በማድረግ የባህር ወሽመጡን ለንግድ መርከቦች ክፍት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ምንም እንኳን እስካሁን ሁለቱም ወገኖች “ለሰላም ዝግጁ ነን” ቢሉም በመሬት ላይ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ግን ቀጣናው ወደ ሰፊ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ደግኗል።
አዲስ ማለዳ
