የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ከተለያዩ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ገዳማት እና መስጅዶች የሰበሰባቸውን ከ8 ሺህ በላይ ጥንታዊ የብራና ፅሑፎች እና ሰነዶችን ወደ ዲጂታል እንዲቀየር ማድረጉን አስታውቋል።
በተቋሙ የመረጃ ሀብቶች ጥበቃና እንክብካቤ ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ፈጠነ አወቀ ዲጂታይዝ ከተደረጉት፤ ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሑፎች በተጨማሪ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች፣ የታሪክ መጽሐፍቶች ታሪካዊ ሰነዶች እና ፊልሞች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ከሚሰራቸው በርካታ ተግባራት ውስጥ አንዱ የመረጃ ሃብቶችን መጠበቅ እና እንክብካቤ ማድረግ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ፈጠነ ከ500 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ወደ ዲጂታል መቀየራቸውን አብራርተዋል።
ይህ ተግባር ታሪካዊ ሰነዶቹ በዲጂታል መልክ ተጠብቀው የሚመጣው ትውልድ በቀላሉ እንዲያነባቸው እና እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ምርምር እና ጥናት ማድረግ ለሚፈልጉ ተቋማት እና ግለሰቦች ወደ ዲጂታል አሰራር የተለወጡትን ጥንታዊ ሰነዶች እንዲገለገሉባቸው እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት 12 የሚሆኑ ጥንታዊ ጽሑፎች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ማድረጉን የመረጃ ሀብቶች ጥበቃና እንክብካቤ ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ፈጠነ አወቀ ገልጸዋል።
