በኦሮሚያ ቱርዝም ቢሮ ምክትል ኮሚሽነር እና የኢኮ ቱሪዝም ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳውድ ሙሜ ዛሬ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ህይወታቸው አልፏል።
የሥራ ባልደረቦቸው አቶ ሀብታሙ አቶምሳ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደተናገሩት አቶ ዳውድ ዛሬ ሀምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአንድ ጀንበር ሰባት መቶ ሚሊዮን ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ ኮሚሽኑን ወክለው የተወሰኑ ሰራተኞችን፣ አባገዳዎችን እንዲሁም ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ነበር ችግኝ ለመትከል በማለዳ ወደ አዳማ የሄዱት።
ችግኝ ተከላውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ አዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ ልዩ ቦታው ” ጎጌቻ ” ወንዝ ድልድይ ላይ አቶ ዳውድ፤ ልጆቻቸው እና አንድ የመስሪያ ቤታቸው ባልደረባ ሰው የነበሩበት መኪና ተገልብጦ የአቶ ዳውድ ሙሜ ህይወት አልፏል።
በመኪናው ውስጥ የነበሩ ሁለቱ የአቶ ዳውድ ልጆች ፤ሾፌራቸው እና አንድ የስራ ባለደረባቸው ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መሄዳቸውን አቶ ሀብታሙ አክለው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
አቶ ዳውድ ሙሜ ከምዕራብ ሀራርጌ ጭሮ ከተማ ከንቲባ እስከ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ፤ በኦሮምያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ውስጥ በዳሬክተርነት ፤ የኦሮምያ ክልል የኮሚኒኬሽን ኃላፊ እና ህይወታቸው እስካለፈበት ድረስ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮምሽን ምክትል እና የኢኮ ቱርዝ ሀላፊ ሆነው ስያገለግሉ ነበር።
” ለቱሪዝም ባላቸው ልዩ ፍቅር በኦሮምያ ክልል ሆነ በፌደራል ደረጃ የፓርኮች ልማት፤ የዱር እንስሳት እንክብካቤ፤ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት እና ማስተዋወቅ ላይ ጥናቶችን ያደረጉ፤ ለቱሪዝም ልማት ያላቸውን የሰጡ እውቅ ባለውለታ ነበሩ ” ሲሉ የሥራ ባልደረባቸው አቶ ሀብታሙ ገልፀዋቸዋል።
በተለይም በኦሮሚያ ክልል አዳዲስ ከተከለሉ 24 ፓርኮች እና 18 እኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች ከጥናት እስከ ማልማት ያደረጉት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ነው የሥራ ባልደረባቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የገለጹት።
@tikvahethiopia
