Home ዜና በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ላይ የተጣለው እግድ እንዲነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ላይ የተጣለው እግድ እንዲነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ላይ የተጣለው እግድ እንዲነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ

ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ በግንቦት 13/2015 ‹‹ሰበር ዜና›› በሚል ባሰራጨው መግለጫ ምክንያት የጣቢያው ፈቃድ በጊዜያዊነት እንዲታገድ መወሰኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ማስታወቁ አስታውቋል። ጣቢያው ‹‹ከሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሚና ውጪ በሆነ አግባብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሄደውን ስብሰባ የሚያውክና ሕዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት ማሰራጨቱ ተረጋግጧል።›› ያለው ባለስልጣኑ፤ ይህም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን የሚተላለፍና በአገር ሁለንተናዊ ሰላም ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ገልጿል። በዚህም ምክንያት ከጉዳዩ አጣዳፊነትና ሊያስከትለው ከሚችለው ጉዳት አንፃር በቀጣይ በባለሥልጣኑ ቦርድ ታይቶ ዘላቂ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ የጣቢያው ፈቃድ በጊዜያዊነት የታገደ መሆኑን ገልጿል። በተለይም የማኅበሩ ቴሌቪዥን ግንቦት 13/2015 ዓ.ም ጠዋት ከዐሥር በላይ ማኅበራትን ማለትም ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት፣ ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የምዕመናን ኅብረት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ጴጥሮሳውያን ኀብረት፣ የጎልማሶች እና ወጣቶች ማኅበር፣ ከወልዳ ዳንዲ አቦቲ፣ ከደጆችሽ አይዘጉ ማኅበር፣ ከሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተለያዩ መምሪያዎች የተወጣጣ የማኅበራት ኅብረት ያወጡትን የአቋም መግለጫ ማስተላለፉ ለእገዳው እንደ ዋና ምክንያትነት እንደሚጠቀስ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ ስለሆነም የማኅበሩ ቴሌቪዥን ሙሉ በሙሉ ሥርጭት ማቋረጡ እንዲሁም ከሳተላይት መውረዱ ታውቋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ለባለስልጣኑ በጻፈው የቅሬታ ደብዳቤ፤ ጣቢያው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለማስተማርና ወቅታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን ለማሳወቅ የተቋቋመ መንፈሳዊ ጣቢያ በመሆኑ የታገደበት የፕሮግራም ይዘት ከመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ጋር የማይጋጭ መሆኑን ዝርዝር ምክንያቶችን በማጣቀስ ገልጿል።

ማኅበሩ ባለሥልጣኑ ተጥሷል ያለው አንቀጽ 70 ‹‹ማንኛውንም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም በሃይማኖት ተከታዮች መካከል እርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት፣ የሌሎችን ሃይማኖት ወይም እምነት ማንኳሰስ፣ ወይም በሃይማኖቶች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስ የለበትም የሚል ነው። ይሁን እንጂ፣ የተላለፈው ይዘት ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር የሚገናኝ ነገር ያለው ባለመሆኑ ማንኳሰስም የሌለበት እና መቻቻል እንዳይፈጠር የሚያደርግ ዘገባ አልተሠራም›› ሲል ስለጉዳዩ አብራርቷል። ‹‹ይዘቱ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ይከበር፣ በአባቶች መካከል የሚስተዋለው መከፋፈል ይቅር የሚል በመሆኑ በማንኛውም መንገድ በቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን መካከል እርስ በእርስ ግጭት የሚፈጥር ነው ብለን አናምንም›› ያለው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ‹‹ዘገባው በተሠራ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ማን ምን ዐይነት ቅሬታ እንዳቀረበ ለጣቢያችን አልተገለጸም። በአዋጁ መሠረት ለባለሥልጣኑ የቀረበ ቅሬታ ካለም ጣቢያችን ዘገባውን የሠራበትን ምክንያት ሳይጠየቅና ሳያስረዳ በባለሥልጣኑ የተወሰደ ርምጃ ነው። ይህም በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ አንቀጽ 7 የተቀመጠውን የባለሥልጣኑን ገለልተኝነት እና ነጻነት የሚጋፋ ሆኖ አግኝተነዋል›› ነው ያለው ማኅበረ ቅዱሳን በቅሬታ ደብዳቤው።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ውሣኔን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ተቋማት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በእርግጥም ሕግን ከማስከበር መነሻነት ይልቅ በማን አለብኝነት ድርጅታዊ ፍላጎት ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጹን ያስታወሰው የኢትዮጲያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ላይ የተወሰደው ‹‹ግብታዊ እርምጃ›› ሌላ ማሳያ እንደሆነ ተረድቻለሁ ብሏል። ኢዜማ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣኑ ገለልተኝነት ላይም ጥያቄ በማንሳት በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን ወሰን ተላልፎ የወሰደውን ይህንን ሕገ ወጥ ውሳኔ እንዲሽር፤ ብሎም ይህን ውሳኔ ያሳለፉት አካላት ተጠያቂ በማድረግ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ ጠይቋል። ‹‹መንግሥት የሕግ የበላይነትን ያክብር!›› በሚል መግለጫ የሰጠው እናት ፓርቲ በበኩሉ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣኑ የወሰደው እርምጃ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፲፩ ንዑስ አንቀጽ ፫ ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ፤ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም›› የሚለውን የሕገ መንግሥቱ ግልጽ ድንጋጌ የጣሰ ነው ብሏል።

በሃይማኖት ጉዳይ ሽፋንም የብዙኃን መገናኛ ተቋምን እስከማገድ የደረሰ እርምጃ መዉሰዱን ተመልክተናል ያለው እናት ፓርቲ በዚህ ረገድ እንደ ፓርቲያችን ዕምነት ለኅብረተሰቡ መረጃ የሚተላለፍበትን የብዙኃን መገናኛ ተቋም አሳማኝ ባልሆነ አመክንዮ ማገድ ተገቢ አይደለም፡፡ በተግባር የሆነዉንና እየተፈፀመ ያለዉን እውነታ መቼም ቢሆን አይደብቀውም ያልተፈጸመም አያደርገውም በማለት ገልጿል። ስለሆነም በሕግ ሽፋን በጊዜያዊነት እንዲዘጋ ዉሳኔ የተላለፈበት የማኅበረ ቅዱሳን መገናኛ ብዙኃን ተቋም የሠራዉ ጥፋት ካለ በግልጽ ቀንና ሰዓቱ ተጠቅሶ ሕዝቡ እንዲያዉቀዉ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ባልሆነበት ሀኔታ መገናኛ ብዙሃን ድርጅቱን በተለመደው ዓይነት ጥቅል ፍረጃና ካለ ተጨባጭ አሳማኝ ማስረጃ ማገድ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕዝባችንም መረጃዎችን በነጻነት የማግኘት መብቱን ሊነጠቅ አይገባም ሲል አስታውቋል። በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው እያሳሰብን፤ የማኅበረ ቅዱሳን መገናኛ ብዙሃን ተቋም ኅብረተሰቡን የማገልገል መብቱ ተጠብቆለት የእግድ ትዕዛዙ በአስቸኳይ እንዲነሳለት እንጠይቃለን ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።