
አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ
አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ በሀገራችን የኪነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ሥመጥር ከኾኑ ሙያተኞች አንዱ ነው፡፡ በድንቅ የአተዋወን ብቃቱ በሚሊዮን የጥበብ አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ አለው፡፡ ከ25 በላይ በሚኾኑ ቲያትሮች እና በርካታ የቴሌቭዥንና ሬዲዮ ድራማዎች ላይ የተወነው ካሌብ የዛሬው የኢትዮጵያዊነት ዓምዳችን እንግዳ በመኾን፣ ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት አኳያ ለሰነዘርንለት ዐሥር ጥያቄዎች የሚከተሉትን ምላሾችን ሰጥቶናል፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት በአንተ እይታ እንዴት ይገለፃል?
ካሌብ፡- ኢትዮጵያዊነት ማለት የሀገር ባለቤትነት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት የሉዓላዊነት መገለጫ፤ የኩሩ ማንነት ባለቤት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሰው የመኾን መገለጫ ነው፡፡ ይህ ማለት ሀገር አልባ የኾነ ሰው ክብር አልባ ይኾንና ስደተኛ ወይም ከዚያ ከፍ ካለ ዳያስፖራ ቢባል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ለእኔ የማንነቴ መገለጫና ሰው የመኾኔን ዋጋ የምገልፅባት ነች፡፡ ከዚህ ባለፈም እንደእኔ ምልከታ ኢትዮጵያ የእመብርሃን የአሥራት ሀገር፤ የዓለም ብርሃን ናት፡፡ እምነት ማለት እውቀት ማለት አይደለም፡፡
እውቀት ዓለማዊ ሕይወትን ሲያሳልጥ እምነት ደግሞ ከሰማያዊውና ከመንፈሳዊው ዓለም የሚያቀናጅ ነው፡፡ በእምነት ከተጓዝን ስለኢትዮጵያ ብዙ ልንረዳ እንችላለን፡፡ በተለይ አሁን ላይ የውጭው ዓለም በጠላትነት ኢትዮጵያ ላይ መነሳቱ ኢትዮጵያ ከዓለም እንደምትለይ ማሳያ ነው፡፡ በእኔ እምነት ዓለም በክፋትና በእርኩስ መንፈስ ተይዟል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን ነገር የእርኩስ መንፈስና የቅዱስ መንፈስ ግጥሚያ ወይም ጦርነት አድርጌ ነው የምታዘበው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይም ይኹን በየትኛው መልኩ የቆመችበትን የእውነትና የሀቀኝነት መሠረት መረዳት ያሻል፡፡ በጥቅሉ ኢትዮጵያ የወደፊቷ የዓለም ገዥ እንደምትኾን ጥርጥር የለውም፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ምን ምን ናቸው?
ካሌብ፡- ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን በርካታ ናቸው፡፡ በእኔ እምነት እንደውም ከዓለም ኹሉ ይለያል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌም እንግዳ ተቀባይነት፣ ትሑትነት፣ ኩሩነት፣ ሀቀኝነት፣ አልደፈርባይነት፣ ለሀገር ክብር እና ለሀገር ልዕልና ሟችነት፣ ወዘተ ያሉትን እሴቶቻችንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምናልባት እነዚህ እሴቶቻችን ዛሬ ላይ ቀማኛ ስለበዛ ብቻ ውሸት ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዛሬም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት፣ ኩሩነት፣ ትሑትነት ወዘተ አለ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን የተማረከና እጁን ወደላይ አንስቶ ሰላም የጠየቀን ሰው ስለበደለን ብቻ አንቀጣም፡፡ ይሄ ደግሞ የሰውነት መገለጫ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች ሰብዓዊ ክብር እንደምንጨነቅ አመልካች ነው፡፡ ዛሬ ግን ይህን ላናይ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በውሸት የታጀለ ማንነትን ደርበናልና ነው፡፡ መንግሥቱ፤ ሚዲያው ውሸት ብቻ ኾኗል፡፡
ግዮን፡- ይህ ትውልድና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል?
ካሌብ፡- አዎ፣ ይህ ትውልድና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትና ትውልዱ መራራቅ የጀመሩት ደግሞ ገና በንጉሡ ዘመን ለትምህርት ወደ አውሮፓ በሚያቀኑበት ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ያኔ የነበረው ትውልድ ነው የዝቅጠቱን መንገድ የጀመረው፡፡ ምክንያቱም ወጣቶቹ አውሮፓ ሄደው ተምረው የመጡት ሥልጣኔያቸውን ሳይኾን በራዥ የኾነ አዳፋ ማንነታቸውን ነው፡፡ ሊማሩ ሄደው ንፁሑን ማንነታችንን እንዲያበላሹ ተብለው ተላኩ፡፡ ተማርን ብለው የመጡት ወጣቶች ይዘው በመጡት ጥራዝ ነጠቅ እውቀት መንግሥት ገልብጠው መንገሥ ነበር ያማራቸው፡፡ ስለዚህ የትውልዱና የኢትዮጵያዊነት መራራቅ ሥረ መሠረቱ የትምህርት ፖሊሲያችን ነው፡፡ የእኛ ባልኾነ ቋንቋ የኛ ያልኾነ ባሕልና ፍልስፍና ነው የምንማረው፡፡ እዚህ ጋር አንድ አጋጣሚዬን ላንሳልህ፡፡ አንድ ወቅት ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለሀገራችን እየተጨዋወትን አንድ ከእንግሊዝ ሀገር የመጣ ሌላ ሰው በጨዋታችን ጣልቃ ገባ፡፡ ይህ ሰው እንግሊዞች ስለ ኢትዮጵያ ገና በ1820ዎቹ ገደማ ምን ያስቡ እንደነበር ከቤተ መጽሐፍታቸው አገኘሁ ያለውን መረጃ አጋራን፡፡
ይህ ሰው በፎቶ ያቀረበልን መረጃ እንግሊዞች ኢትዮጵያን እንዴት አድርገው በዘርና በሃይማኖት ከፋፍለው በተለይም አማራና የተዋሕዶ እምነትን አጥፍተው መግዛት እንደሚችሉ በፓርላማቸው ያደረጉን ሙግት ነው፡፡ ተመልከት እንግዲህ ዛሬ እንግሊዞች የዚህ ሃሳባቸውን ፍሬ ነው እያበሉ ያሉት ፤ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ያኔ እነሱ ሲያልሙት የነበረውን ዓይነት የበታችነት የሚሠማው ወጣት ተፈጥሮና የሐሰት ትርክት ተደርቶለት እርስ በእርሳችን እየተባላን ነው፡፡ ይሄ ማለት ትውልዱና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ማንነቱን ተሰልቧል፡፡ የጠላቶቻችን አጀንዳ ተቀባይ ኾኗል፡፡ ኩሩ ማንነቱን ጥሎ ስደትና ፍልሰትን ምርጫው አድርጓል፡፡
ግዮን፡- በዚህ ትውልድ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው?
ካሌብ፡- የኢትዮጵያዊነት ተግዳሮት በሚዲያ ልፈፋ አይፈታም፡፡ ወረድ ብሎ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ እንደ ተግዳሮት የሚታዩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይም ከሕግ አንፃር መሻሻል ያለባቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ተግዳሮቶች የፈጣሪ እርዳታ ካልታከለባቸው በቀላሉ ለመፍታት ከባድ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
ግዮን፡- ይህ ትውልድ ከብሔርተኝነት መንፈስ ተላቅቆ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ይችላል?
ካሌብ፡- ወደማንነታችን ለመምጣት የቀደመ ታሪካችንን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እውነተኛ የሃይማኖት አባቶች በመካከላችን ካሉ ችግሮቹ ተፈተው ከብሔርተኝነት መላቀቅ እንችላለን፡፡ አሁን የምናየው ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ ፈጣሪ ሰው አድርጎ ፈጥሮን እኛ በብሔር ተከፋፍለን ስንጠፋፋ ማየት ፍፁም አሳፋሪ ነው፡፡ የቆምንበትን ቦታ ማየትና ማጤን አለብን፡፡ በምትሰምጥ መርከብ ላይ እያበድን መኾኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ይህን ስንረዳ ነው ከዘረኝነት አባዜ መላቀቅ የምንችለው፡፡ ዓይነ ልቦናችንን ፈጣሪ ከፍቶልን ይህን የምንፀየፍ ያድርገን፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው ግብር?
ካሌብ፡- ኢትዮጵያዊነት በተግባር የሚገለፅ ግብር ነው፡፡ በተግባር የማይገለፅ ነገር ስሜት ብቻ ኾኖ አየር ላይ ይቀራል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግን ከስሜት የተሻገረ ግብርን ይሻል፡፡ ስሜት አይጨበጥም፤ አይዳሰስም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የቱንም ያህል ለመግለጽ ረቂቅ ቢኾንም የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ ካርታ ያለው፣ ማንነት ያለው፣ እሴት ያለው፣ ምሉዕ የኾነ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ኾኖ ማለፍን የሚሻ ማንነት ነው፡፡
ግዮን፡- ማኅበራዊ ድረገፆች ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ሚና ምንድነው?
ካሌብ፡- ማኅበራዊ ድረገፆች በአግባቡ ለተጠቀመባቸው ጥሩ መልዕክት ማስተላለፍ ያስችላሉ፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ በበጎነትና በቀናነት ላይ ለመሥራት የተከፈቱ ገፆች ከፍተኛ አዎንታዊ አገልግሎት አላቸው፡፡ ዜጋን ለመቅረፅና ለመገንባት ያስችላሉ፡፡ ቴሌግራም፣ ዋትሳፕ ወዘተ የመማሪያና መወያያ መንገዶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ አጠቃቀማችን ነው፡፡
ግዮን፡- ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት ይዞ እንዲቀጥል ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ?
ካሌብ፡- እግዚአብሔር ዓይነ ልቦናውን ያብራለትና ማንነቱን እንዲያውቅ ያድርገው፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶችን በዓለም ለማስተዋወቅና ቅርሶችን ከነክብራቸው ለመጠበቅ ምን ይደረግ ትላለህ? ኃላፊነቱንስ የማን ነው?
ካሌብ፡- በእኔ እምነት አባቶቻችን ያቆዩልን ቅርሶቻችን ማንነታችንን አውቀን እንድንኖር ካላደረጉን ለእኔ ቅርሶቻችን ማለት ይከብደኛል፡፡ የኛ ቅርሶች ያሉት አውሮፓ ሙዚየም ውስጥ ነው፡፡ እነሱ ዛሬ ላይ ሠለጠንን ብለው የሚሠሯቸው ነገሮች መነሻቸው የኛ ነው፡፡ ሆሊውድ ውስጥ የሚሠሩ ፊልሞች መነሻ ሐሳባቸው የእኛ ነው፡፡
ቅርሶቻችንን መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ አይደለም በድፍን ሀገራችን ያሉት ቅርሶች ይቅርና አንዷ የኾነችው ላሊበላ ብቻ ዓለምን ታስተምራለች፡፡ ትውልዱ በእጁ ያለውን ነገር መጠበቅ አለበት፡፡ ምኒልክ ዓድዋ ላይ ታሪክ ሠርቶ ዓለምን ቢያስደምም ዛሬ የምኒልክን ሐውልት ካላፈረስን የሚል ወጣት ተፈጥሯል፡፡ ለእኔ ቅርስን መጠበቅ የዚህን ወጣት አስተሳሰብ ከመቀየር ይጀምራል፡፡ “ጡት ተቆረጠ” ብለው ሐውልት ሲያቆሙለት “ይሄ ታሪኬ አይደለም” የሚል ትውልድ ከመፍጠር ይጀምራል፡፡
ግዮን፡- አባቶቻችን ለዚህ አገር በክብር መቆየት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለተከታዩ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ትውልድስ ለቀጣዩ ለማስተላለፍ ምን ይጠበቅበታል? ምንስ ያድርግ? ካሌብ፡- በእኔ እምነት ይህ ትውልድ የራሱን የሐሰት ትርክትና አዳፋ ምግባር በመልካም ተግባር ለውጦ ማለፍ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ላይ ይህ ትውልድ ይህን ላስተላልፍ ብሎ ለቀጣይ ትውልድ የሚያስቀምጠው ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ እንኳ የቀደምት አባቶቻችንን ቅርሶች እንደተረከበ ጠብቆና እርሱ ደልዞ የወየበውን የኢትዮጵያዊነት ማንነት አስተካክሎ ይለፍ፡፡ ከዚህ ውጭ ትውልዱ እሴት ለመጨመር የሚያስችል ቁመና ላይ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም በሐሰት ትርክት ወንድሙን በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገድል፤ ዘር ቆጥሮ በመጓዝ የኢትዮጵያን ክብር ያዋረደ ትውልድ ነው፡፡ ይኼን ታሪክ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያወርስ አልመክርም፡፡