በብሔር ጉያ የመሸጎጥ ኪሣራ አዘል ፖለቲካ! አዳነ ጥላሁን ዳኜ(ወልድያ)

Date:

አባቶቻችን ሰኔ ግም ሲል ለእርሻ ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ከሰቀሉበት አውርደው የሚጠግኑበት ከሕፃን እስከ አዛውንት ለእርሻና ለቁፋሮ ራሱን የሚያዘጋጁበት ወር ስለሆነ በዓመት አንድ ጊዜ በመጣ በሄደ ቁጥር ንፍሮ ቀቅለው በፍቅር የመቀበልም የመሸኘትም ሥርዓት የሚፈፀምበት ወር እንደነበር ይታወቃል፡፡

ተኪው የሐምሌ ወር በበኩሉ ገበሬና በሬ አንዱ ጠማጅ ሌላው ተጠማጅ ሆነው በኅብረት ጓል ፈንቅለውና ማሳውን አርሰው አዝመራ የሚያዘምሩበት የያንዳንዱ አራሽ ገበሬም ሆነ ሞፈርሳቢ በሬ ጥንካሬ ብሎም ታታሪነት የሚፈተሽበት የሥራ ወር ነበር፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን ሰኔም ሆነ ሐምሌ የቀድሞ ለዛና ወዘናቸው የተሟጠጠ ወራት ሆነዋል፡፡ በተለይ ሰኔ ነገረኛ ወር መሆኑ አይሎ ታይቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም ሰኔ ወር ነበር ዶ/ር ዐቢይን ለመግደል በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ፈንጂ የፈነዳው፡፡ እነጀኔራል ሰአረ መኮንን፣ አሳምነው ጽጌና እነዶ/ር አምባቸውም የተገደሉት በሰኔ ወር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የትግራይ ሽፍታ ቡድን መቃብር ቆፍሮ ከተቀበረበት ወጥቶና አንሰራፍቶ 2ኛውን ዙር ጦርነት በአፋርና በአማራ ላይ የከፈተው ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንት ነበር፡፡

የ2014 ዓ.ም ወርሀ ሰኔና ሐምሌም ቢሆኑ መልካም ዜና አብሳሪ ወራት አልሆኑልንም፡፡ እነዚህ ወራት የደስታ ብስራት የሰማንባቸው ወራት አይደሉም (የ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ የድል ብስራት ሳይዘነጋ)፡፡

በወለጋ በተለያዩ ወረዳዎች ዘመዶቻችን ላይ የተፈፀመው ዘር የማፅዳት የግፍ ጭፍጨፋ ቅስማችንን እንደሰበረው ነው ወደ ሐምሌ ወር የተሸጋገርነው፡፡ የሐምሌም ወር ቢሆን በአራቱም ማዕዘን የሰላም አየር ነፋስ አልነፈሰበትም፡፡ የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ደረት የሚያስነፋ አልሆነም፡፡

በዘንድሮው ሰኔና ሐምሌ ሌላው ቀርቶ የመሪዎቻችን  ባሕሪ ጭምር ተቀይሮብናል፡፡ ሆደባሻም ሆነውብናል፡፡ ከልባቸው በፈለቀ ልባዊ እውነትም ይሁን በማስመሰል ከአንደበታቸው ይወጣ የነበረው ትሁትና ለስላሳ አነጋገር ሻክሮብናል፡፡ “ያላረፈ ይቀፈደዳል” የሚል ፉከራ አዘል ቃል የሰማነው በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደአምባገነንነቱ እያዘገሙ ነው እንዴ? የሚል ጥያቄ ያነሳነውም ከዚያ ዛቻ የተሞላ ቃል በኋላ ነው፡፡

ተስፋ ተጥሎበት በፍቅር የተጨበጨበለት ያገር መሪ መጨረሻው አላምር ብሎ ዐይንህን ላፈር ተብሎ የሚረገመው በሻከረ ቋንቋውም ሆነ ጉልበቱን ተማምኖ ከሕዝብ ፍላጎት እየራቀ ሲሄድ በመሆኑ ትናንት ከራሳችን አብልጠን የወደድናቸው መሪዎቻችንን የዴሞክራሲ ሾተላይ አጋጠሟቸው ይሆን? ስንልም ጠይቀናል፡፡ እኛም ሲጀማምረን እንዲህ እያደረገ ነበር ያለችው እብድ ለካ ወዳ አልነበረም፡፡

መሪዎቻችን በአንገብጋቢ ሀገራዊ አጀንዳ ዙሪያ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ተብለው የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ወደጎን ሲገፉት እንጂ ቀና መልስ ሲሰጡባቸው  አልታዩም፡፡ ይኸ ደስተኛ ባለመሆን ሀሳባቸውን በነፃ የሚያንሸራሽሩ ጥያቄና ተከራካሪዎችን መድረክ መንፈግ  በፓርላማ ስብሰባ ላይ ጭምር ታይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ም/ቤት ባደረገው ስብሰባ በኮንዴሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ በተፈፀመ ረቂቅ ሌብነት ዙሪያ ጣት የተቀሰረበት ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ በተጠረጠረበት ወንጀል ሐሳቡን በነፃ በማቅረብ ፈንታ በአፈጉባዔዋ በኩል እንዳይናገር ንግግሩ በተደጋጋሚ ሲቋረጥ በትዝብት አይተናል፡፡

ዶ/ሩ ድርጊቱን ፈፅሞት ከሆነ መማር እንደእርሱ ከሆነ ይቅር ምን ያደርጋል? የሚል ትዝብት ያስነሳል፡፡ በኔ በኩል የዋህ ነህ አትበሉኝና “ዶ/ር” የሚለውን እጅግ ተከባሪ ማዕረግ ተሸክሞ መጠርጠሩ በራሱ አስደንግጦኛል፡፡ በረሃብ ከሚንገላቱና ከሞት ጋር ግብግብ ከገጠሙ ምንዱባን ጉረሮ በመንጠቅ የዕርዳታ እህል ዘረፉ የተባሉት ትልቁ የዕርዳታ ድርጅት መሪ በእርሳቸው ብቻ አላበቃ ብሎ ልጃቸውን ጭምር ሌብነት ስለማስተማራቸው የሰማነው የዘረፋ ተውኔት መረጃ ገና ሳይደበዝዝ የዶ/ር ሙሉቀን መጨመር ይበልጥ በሀፍረት እንዲንሸማቀቅ እንዳደረገን ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም፡፡ እንደው በሞቴ ነገርን ነገር ካነሳው አይቀር የታላቁ ዕርዳታ ድርጅት መሪ አባትና ልጅን በስርቆት መጠርጠር ስትሰሙ አሁን በስደት ተፈናቅሎ ጎዳና ላይ ከወደቀ ከርሀብ ጋር ግብግብ ከገጠመ መጠጊያ አጥቶ በዝናብና በብርድ ከሚሰቃይ ሕዝብ የሚሰርቅ ሰው ነው ወይስ አረመኔ የሚል ጥያቄ አላጫረባችሁምን?  ኧረ የማርያም ልጅ ድረስልን!

ወደተነሳሁበት አጀንዳ ስመለስ የዶ/ር ሙሉቀን በሌብነት መጠርጠር በራሱ አናዶኛል፡፡ አይቻልም እንጂ ቢቻል ኖሮ በአባባሌ አትሳቁብኝና አንድ ወቅት የወያኔ ባለስልጣናት ሕዝብን በአግባቡ አላስተናገደም በሚል በሰብሰባ በማስወሰን “የዶ/ርነቱን ማዕረግ ገፈነዋል” የሚል ውሳኔ እንዳስተላለፉበት የላልይበላ ጤና ጣቢያ ዶ/ር፣ እኔም የዶ/ር ሙሉቀን ዱክትርና ማዕረግ ይገፈፍ የሚል ሀሳብ አቀርብ ነበር፡፡ ክፋቱ ግለሰቡ ይኸን ክቡር ማዕረግ ያገኘው በሹመት ሳይሆን በትምህርት ሆነብኝ እንጂ፡፡

ይኸም ሆኖ በአፈጉባዔዋ በኩል ዶ/ር ሙሉቀን ሲናገር በተደጋጋሚ የተደረገበት የማቋረጥ ጫና ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ እንጂ የሚያፋፋ ባለመሆኑ ሊወገዝ እንጂ ሊበረታታ የሚገባ አስመስጋኝ ተግባር አይደለም፡፡

ይኸው የአፈና ተግባር በኦሮሚያ ክልል ም/ቤት ስብሰባም ላይ ስለመፈፀሙ እንዳልናገር ታፈንኩ ባሉት አቶ ታየ ደንደአ አንደበት ስንሰማ ደግሞ እንዴ! ይኸ ነገር ወደየት እያመራ ነው የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አስገደደን፡፡ ጉዳዩ በአቶ ታየ ላይ ብቻ ሳያበቃ ወደአማራ ክልል ተዛምቶ በአማራ ክልል ም/ቤት ስብሰባም ላይ በአቶ ፀጋ አራጌ ላይ ስለመፈፀሙ ከራሳቸው አንደበት በተንቆረቆረ ጽሑፍ ስናነብ የኛ መሪዎች ትልቁ ችግር ስህተታቸውን የሚነግራቸውን ሰው አለመውደዳቸው እንጂ የችግር መፍትሔ የሚገኘው ቅሬታ አለን የሚሉ ሰዎችን እንዳይናገሩ በማፈን ሳይሆን የሚሰማቸውን እንዲተነፍሱ በማድረግ መሆኑ መዘንጋት አልነበረበትም፡፡

የተቃራኒን ሐሳብ በመድረክ ላይ በግልፅ አውጥቶ ማንሸራሸር አንድም የቅሬታ አቅራቢውን የቅሬታ ሥረ ምንጭ ለማወቅ ይረዳል፡፡ በሌላ በኩልም የቅሬታ አቅራቢውን ዴሞክራሲያዊ መብት ሳይሸራረፍ ያረጋግጣል፡፡ በሦስተኛ ደረጃም የዴሞክራሲ ባህል በእግሩ ቆሞ እንዲራመድ ያግዛል፡፡ “ተ..ን…ፍ..ስ..” አለ ሐኪም የሚባለውኮ መተንፈስ በራሱ ለታማሚው በሽተኛ ፍቱን መድኃኒት ለማስገኘት እንዲያግዝ ነው፡፡

አቶ ፀጋ አራጌ በክልሉ ም/ቤት ስብሰባ ላይ ደረሰብኝ የሚሉት እንዳይናገሩ መከልከል ብቻ ሳይሆን ከአዳራሹ በፖሊስ ለማባረር የሚያስችል ሙከራ እንደተደረገባቸው ጭምር ነው በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው የገለፁት፡፡

ከላይ የተገለፁትንና የአቶ ፀጋን ቅሬታ ጨምረን አጠቃላይ የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንገምግም ካልን ባገሪቱ ዙሪያ የዴሞክራሲ ሾተላይ አጋጠመ መሰል የሚል የጥርጣሬ መደምደሚያ ላይ ያደርሰናል፡፡ ይኸ  ጉዳዩ በአፋጣኝ ካልታረመ እየጎለበተ ሄዶ ሙሉ በሙሉ አምባገነንነትን ያሰፍናልና ሁላችንም ከወዲሁ ልናወግዘው እንደሚገባም መናገር ያስፈልጋል፡፡

ወደአቶ ፀጋ ዝርዝር አስተያየት ስናመራም “የታፈንኩት እኔ ብቻ ነኝ ብየ አላምንም፤ የታፈነው የአማራ ሕዝብ ነው” ሲሉ እርሳቸው ማለት የአማራ ህዝብ በሙሉ፤ መላው የአማራ ሕዝብም እርሳቸው እንደሆኑ አድርገው ያስተላለፏት መልዕክት ግን ምቾት የማትሰጥ አደገኛ መደምደሚያ ናትና ዘርዘር አድርጌ የዚህ ጽሑፍ ቁልፍ ማጠንጠኛ አድርጌ እናያታለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ለሌሎቹ ነጥቦች ቅድሚያ ሰጥቼ ትንሽ ልበል፡-

አቶ ፀጋ ትግሉን ባልተመቸ ሁኔታ ሳደርግ ሥራ አጥቼ ጦም አድሬ ታስሬ እስከሞት መስዋዕትነት እንደሚሆን ነው፡፡ መኪናና አጀባ ይጎድልብናል ብለው የአማራን ሕዝብ በግዞት አስይዘው እንደሚቀልዱት  ግን አልወስንም ብለው የገዛ የትግል አጋሮቻቸውን በውስጠ ወይራ አነጋገር ጎሸም አድርገዋቸዋል፡፡

የሚገርመው ከአቶ ፀጋ በፊት ባልሳሳት የዛሬ 2 ወራት አካባቢ ሌላው የአማራ ብልፅግና ባለስልጣን የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ለአማራ ሕዝብ በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ ከአቶ ፀጋ አራጌ አነጋገር ያልተለየ መረር ከረር ያለ ስንኝ የቋጠረ መግለጫ ሰጥተውናል፡፡

አንድ ወቅት “የበረከት ስምዖን ግልገሎች” የሚል የዳቦ ስም ከአማራ ሕዝብ የተቸራቸው እኒህ ግለሰቦች ከነበረከት የጡት ልጅነት ተላቅቀው በወያኔ ኢሕአዴግ ጃንደረባነት ሲያስለቅሱት ለነበረው የአማራ ሕዝብ መብት መከበር መቆማቸው ትናንት ከትናንት በስቲያ በፈፀሙት ግፍ የቆሸሸች ነፍሳቸውን በንስሀ ፀበል ለማንፃት የተደረገ ልባዊ ውሳኔ ሆኖ ሊቆጠርላቸው የሚገባ አስመስጋኝ ተግባር ነውና በርቱ ልንላቸውም ከጎናቸው ልንቆምም ይገባል፡፡ ግን ካለፈው አመጣጣቸው ስናይ እንደት እንመናቸው? የሚል አጠያያቂ ጥያቄም በአእምሯችን ይመላለሳል   ለምንጠረጠርክ ካላችሁኝ ደግሞ ሁለቱም ባለሥልጣናት በወያኔ ኢሕአዴግ ዘመነ አገዛዝ ወቅት በሕዝብ መጨቆኑ ሂደት ላይ መሪጌታ ነበሩ ባይባሉ እንኳ የጭቆናው መሪጌታዎች ካባና በርኖስ አልባሽ የመሆን እድላቸው ሰፊ ስለነበርና ንክኪ ስለነበራቸው ነው፡፡

መቼም ባለፈው በተፈፀመው የሕዝብ አፈናና ጭቆና ዙሪያ የለንበትም በሚል ደፍረው እንደጲላጦስ እጃቸውን ይታጠባሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ያን ካደረጉ ሁለቱም የ2010 ለውጥ(በኔ በኩል ለውጥ ሳይሆን እጅግ ኢምንት የሆነች ነቁጥ ታህል የአስተዳደር መሻሻል ነው የሚል አቋም ነው ያለኝ) ከተከሰተ ወዲህ ተወልደው በትምህርት ተኮትኩተው አድገውና አሁን የደረሱበት የሥልጣን እርከን ላይ መድረስ አለባቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአራት ዓመት ቆይታ የማይቻል ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ በደረሱበት የሥልጣን ማማ ላይ ለመድረስ የግድ በወያኔ ኢሕአዴግ ታማኝ ተላላኪነት አድርጉ የተባሉትን ሁሉ ያለኮሽታና ማንገራገር እያደረጉ ታማኝነታቸው ካልተረጋገጠ በስተቀር  የማይሆን ነው፡፡

በ27ቱ የወያኔ ኢሕአዴግ ዘመነ ሥልጣን እንኳን ከከፍተኛው የሥልጣን ማማ መድረስ አይደለም፡፡ የአካባቢ ዕድር ጡርንባ ነፊ ለመሆን ጭምር የአገዛዙ ታማኝነት ዋና መሥፈርት እንደነበር በተግባር ያየነው ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ከተሆነ ደግሞ ወያኔ በሕዝብ ላይ በሰራው ግፍና በደል ዙሪያ ድርሻ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

አቶ ዮሐንስ ቧያለውን ጠልቄ ስለማላውቃቸው በእርሳቸው ዙሪያ በይሆናል ከመናገር እቆጠባለሁ፡፡  ታማኝ የወያኔ ኢሕአዴግ ከድሬ ሳይሆኑ አሁን ከያዙት የስልጣን እርከን ላይ መድረስ አይችሉም ብሎ ደፍሮ ለመናገር ግን የግድ እርሳቸውን በሚገባ ማወቅን አይጠይቅም፡፡ ደራሲ ማርዮ ፑዞ የጡት አባት በሚል ርዕስ ወደአማርኛ የተተረጎመ የማፊያን ታሪክ የሚተነትን መጽሐፍ አለው፡፡  በዚህ መጽሐፍ ላይ ከያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ አንድ ወንጀል አለ የምትል ድንቅና ዘመን አይሽሬ አባባል አለች፡፡ ይቺን የማርዮ ፑዞ ድንቅ ጥቅስ ተውሰን ከያንዳንዱ የሥልጣን መሸጋገሪያ እርከን ዙሪያ አንድ ወንጀል ነበረ በሚል መልዕክት አስተላላፊ ዓ.ነገር ወደሀገርኛ ቋንቋ ብንከልሳት ለእነአቶ ፀጋ የኋላ ታሪክ መነሻም መደምደሚያም ትሆናለችና ይቺን ጥቅስ እዚህ ላይ ቋጥሬ  ወደሌላው ቁም ነገር ልለፍ፡-

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት አቶ ፀጋ አራጌ በአማራ ክልል ም/ቤት ስብሰባ ላይ እንዳልናገር  ታፈንኩ ያሉትን ዐቢይ ጉዳይ ስናየው ድርጊቱ ሳይከለስ ሳይበረዝ ትናንት ከትናንት በስቲያ እርሳቸው የሰሜን ወሎ ዞን ቁጥር አንድ አለቃ በነበሩበት ወቅት በራሳቸውም በዙሪያቸው በተሰባሰቡ ካድሬዎችም ይፈፅሙት ስለነበር ዛሬ በእርሳቸው ላይ ደርሶ ስናይ ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው ከምንል በስተቀር አዲስ ነገር አላየሁበትም፡፡ እንዳውም እርሳቸው ደረሰብኝ ብለው የተብከነከኑት እንዳይናገሩ መከልከል ብቻ ነው፡፡ እርሳቸውና በዙሪያቸው ተሰባስቦ የነበረው ቡድናቸው በኛ ላይ የፈፀመው ግን አጥንት ሰርስሮ የሚገባ ቅዱስ ዮሐንስ የማይሽረው ምሬት አዘል ግፍ ነው፡፡ ለግፍ ፈፃሚ ግፈኞች ትምህርት ይሆን ዘንድም ይኽን ነጥብ ከይቅርታ ጋር ትንሽ ላብራራው፡-

በ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ወልድያ ላይ ቅንጅትን ወክለው ከተወዳደሩትና በአስተማማኝ የሕዝብ ድምፅ ካሸነፉት አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ የምርጫ ውጤቱ በጉልበት ተዘርፎ አሸናፊዎቹ ወደተሸናፊነት በመውረድ ብቻ አበሳችን አልተደመደመም፡፡ እኛ በተቀዋሚነት ለፓርላማ የተወዳደርነው ብቻ ሳንሆን ገና ለገና የቅንጅት አባል ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የታሰቡ በተለይ ያኔ እነአቶ ፀጋ አራጌም የበላይ ጌቶቻቸው የወያኔ ኢሕአዴግ ቁንጮ ባለሥልጣናትም አደገኛ ቦዘኔ ብለው ይጠሩት የነበረው ወጣት ትውልድ ላይ በጅምላ የእስር የማንገላታት የግድያ ዘመቻ እንደተከፈተበት ይታወቃል፡፡ የብአዴን ካድሬዎች ያኔ ባልና ሚስት አፋትተዋል፡፡ የቆቦ ወረዳ የመኢአድ ተጠሪ የነበረውና ቃሊም ከተባለ ቀበሌ ኗሪ የነበረው ግለሰብ በሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየች የትዳር አጋሩን በሚኖርበት ሰበካ ቤተክርስቲያን እንዳትቀር ክልከላ ተደርጎበታል፡፡ ወዘተ፣… ወዘተ፣…

በኛ በፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪዎች አካባቢ ማሰር ማዋከቡ የጀመረውም በዕጩ ተወዳዳሪነታችን የተሰጠን ያለመከሰስ መብት የጊዜ ገደብ ገና ሳይጠናቀቅ ነበር በዚያ ወቅት እኛ ብቻ ሳንሆን ስለፖለቲካ ምንም ነገር የማያውቁ ቤተሰቦቻችን ጭምር ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተጉላልተዋል፤ ለስደትም ተዳርገዋል፡፡

የእኔ ሦስት ልጆች በፖሊስ ያለርህራሄ የተደበደቡትና ለስንቅ ማመላለስ እንዳይመች ሆን ተብሎ በሦስት የተራራቀ ጣቢያ ተነጣጥለው እንዲታሰሩ የተደረገው ስንቅ አቀባይ ቤተሰብን ለቁርስ ለምሳና ራት ስንቅ ሲያመላልሱ መንገድ እንዲመታቸው ሆን ተብሎ በተሰራ ደባ ሲሆን ልጆቹ  የታሰሩትም ወንጀል ፈፅመው ሳይሆን ከኔ በመወለዳቸውና በኔ ባባታቸው ተቃዋሚ መሆን የተነሳ ነበር፡፡ እኔን ለማሰር ወደኔ ቤት የመጣው የፖሊስ ኃይል እኔን ማግኘት ስላልቻለ ምንም የማያውቁ ልጆቼን በግፍ ከመግረፍ አልፎ በኔ ምትክ መያዣ ነበር ያደረጋቸው፡፡

የኔ ተቃዋሚነት ጦስ ከቤተሰቤ አልፎ ላሳደግሁት ውሻም ተርፏል፡፡ ወደእኔ ቤት የመጡት ፖሊሶች እኔን ሲያጡ ተበሳጭተው ስለነበር የተፈጥሮ ግደታውን እየተወጣ የነበረውን ውሻ በንዴት ከበው በዱላ እንደጉድ ቀጠቀጡት፡፡ የዚህ ውሻ ወንጀሉ መጮሁ ነበር፤ ከተጋደመበት ሳይንቀሳቀስ ውሎ አድሮ በ3ኛው ቀን ነበር ካንገቱ ቀና ያለው፡፡ ባልተቤቴም ቢሆን ከተነጣጠረባት የጠመንጃ አፈሙዝ ሰለባነት ፈጣሪ አምላክ በተአምሩ ነበር ያተረፋት፡፡ ምላጭ ሳቢው ፖሊስ ከትከሻው ክላሹን አውርዶ ጣቱን ከምላጩ ላይ ባሳረፈበት ቅፅበት ጎረቤቶቻችን ለእርዳታ በመድረሳቸው ነበር ከሞት ያተረፏት፡፡ ግርግሩ አልፎ ነገር ከበረደ በኋላ ጠመንጃ የደገነባትም ሆነ “በላት” ብሎ ትዕዛዝ የሰጠው አለቃ በመፀፀት በዚያች ቅፅበት ምላጭ ሊስብ እንደነበር በመግለፅ ይቅርታ ጠይቀዋታል፡፡ በኔ ሰበብ ተደጋጋሚ መንገላታት ስለደረሰባትም ከመንግሥት ሠራተኛነት ወደሥራ አጥ የቤት እመቤትነት የተዛወረችው ሰበባ እየተፈለገ መቆሚያ መቀመጫ ስላሳጧትና በየዕለቱ በሚደርስባት የካድሬዎች ትንኮሳና የመብት ጥሰት ነበር፡፡ እኔና የዞኑ የቅንጅት ሰብሳቢ አቶ በለጠ ገብሬን ደግሞ በዚያ አሰሳ ወቅት ቢያገኙን ኖሮ የከፋ እርምጃ ይወስዱብን እንደነበር ነግረውናል፡፡ ደግነቱ መረጃው ቀድሞ ደርሶን ስለነበር ሁለታችንም አንድ ላይ ሌላ ቦታ ሰንብተን እጅ የሰጠነው የፖሊስ ኃይሉ ደምፍላት ከበረደና ከተረጋጉ በኋላ ስለነበር በኛ ላይ የደረሰ ድብደባም ሆነ ሌላ ማንገላታት የለም፡፡

ከእሥር ከተፈታን ጀምሮ እስከ 2010 መጋቢት ወር የነበሩት ዓመታትም በተቃዋሚነት ስማችን በጥቁር መዝገብ የተመዘገብን በሙሉ ይደርስብን የነበረው የተለያየ ማዋከብና የ24 ሰዓት ክትትል በሙሉ ቢፃፍ ራሱን የቻለ መፅሐፍ ይወጣዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከአካባቢያችን ማኅበራዊ እድር እንዳንሳተፍ በእድር አመራሮቹ ላይ ይደርስባቸው የነበረውን ጫና አመራሮቹና ፈጣሪ ብቻ ነበር የሚያውቁት፡፡ በተቃዋሚነት አቋሙ በዞናችን ደማቅ ታሪክ የነበረውና ዛሬ በሕይወት የሌለውን ጋሸ በለጠ ገብሬ (ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያሳርፋት) ከወልዲያ መድኃኒዓለም የሰበካ ጉባዔ ም/ሰብሳቢነት በእንዴት ያለ ውስብስብ ሴራ እንዳወረዱት የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ወዘተ፣… ወዘተ፣…

በእነዚህና በተፈፀሙብን ሌሎች ደባዎችና በርካታ የመብት ረገጣዎች ዙሪያ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት አቶ ፀጋና እርሳቸው ሲመሩት የነበረው የካድሬዎች ስብስብ ነው፡፡ ይኸ ስብስብ አይሰሩ ሥራ ነበር የሠራን፡፡ አንድ ወቅት በሰሜን ወሎ ዞን በተካሄደ አጠቃላይ የመንግስት ሠራተኞች ስብሰባ ላይ በተነሳ የፖሊሲ ውይይት እኔ ከብአዴን ሰዎች የተለየ ሀሳብ በመሰንዘር በመናገር ላይ እንዳለሁ የድምፅ ማጉሊያውን  በመንጠቅ  እንዳልናገር የተከለከልኩት በአቶ ፀጋና በካቢኔ ሰዎቻቸው ነበር፡፡ ዛሬ የለውጡ ፋናወጊ ነኝ እያለ ጎፈሬውን የሚያበጥር አንድ እበላባይ ካድሬ (ለክብሩ ስል ስሙን ከማንሳት ተቆጥቤአለሁ) ድምፅ ማጉሊያውን ሲቀሙኝ ደግ አደረጉት የታባቱንስ ብሎ ከኔ አልፎ አባቴን የሰደበበት ኃይለቃል አሁንም በጆሮየ ይሰማኛል፡፡ በሌላ ስብሰባ ወቅትም እየተናገርኩ እያለ መብራት በማጥፋት ንግግሬን አቋርጠውኛል፡፡ ከስብሰባ አዳራሽም በፖሊስ ተገድጄ እንድወጣ ተደርጌ አውቃለሁ፡፡

ይኸ ሁሉ የተፈፀመው አቶ ፀጋ አራጌ የሰሜን ወሎ ዞን ቁጥር አንድ አድራጊ ፈጣሪ ባለሥልጣን በነበሩበት ወቅት ሲሆን አንዳንዶቹን ድርጊቶችም ራሳቸው በመሯቸው ቀሪዎቹ ደግሞ በጓዶቻቸው ሰብሳቢነት በተካሄደ ስብሰባ ወቅት የተፈፀሙ ናቸው፡፡ ትናንት በኛ ላይ ሲፈፅሟቸው የነበሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ዛሬ ሳይበረዙና ሳይከለሱ በእርሳቸው ላይ መፈፀማቸወን በገዛ ብዕራቸው ሲያስነብቡን የፈጣሪን ረቂቅ ሥራ በማድነቅና ብድር በምድር የሚለውን የአበው ተረት ብቻ ሳይሆን “አንተም ጨካኝ ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ ፤ እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብህ” ተብሎ ለአቤቶ ሰይፉ የተገጠመውን የሕዝብ ግጥም ነው ያስታወሰኝ፡፡ እንደው ነገሩ ከተነሳ ብየ ወደዝርዝር ጉዳይ ገባሁ እንጂ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የኢሕአዴግ ሰዎች በሀገር ደረጃ በሕዝብ ላይ የፈፀሙት ደባ ሲታይ በኛ ላይ የተፈፀመው እዚህ ግባ የማይባል ኢምንት መሆኑን አጥቼው አይደለም፡፡

ከላይ የተዘረዘረውን ሐተታ ያቀረብኩት ከቂም ተነሳስቼ አይደለም፡፡ የመብት ረገጣው በአቶ ፀጋ ላይ በመድረሱም “ደግ አደረጓቸው” ብዬ አይደለም፡፡ አቶ ፀጋ በደረሰባቸው የመብት አፈና የተንገበገቡትን ያህል እርሳቸውም ትናንት ከትናንት ወዲያ በእኛ ላይ ሲፈፅሙትም ሆነ ሲያስፈፅሙት የነበረው እኩይ ድርጊት ምን ያህል ቆሻሻ ድርጊት እንደነበር ተገንዝበው ለወደፊቱ የማይረሳ ትምህርት እንዲቀስሙበት ፈልጌ ነው፤ የተዳፈነ እሳት ገለጥለጥ ማድረግ የፈለግሁት፡፡ በተረፈ የዴሞክራሲ ሲሶም ሆነ ኩርማን የለውምና እርሳቸው ላይ የደረሰውን የመብት አፈና በማውገዙም በመቃወሙም በኩል ግን ከጎናቸው እቆማለሁ፡፡

ያም ሆኖ የአቶ ፀጋም ሆነ የአቶ ዮሐንስን ምሬት በጥሞና ለመረመረ ታዛቢ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት አካባቢ ያለው መተሳሰብ ፍቅርና አንድነት የላላና ውስጡም በጥርጣሬና ባለመተማመን የተሞላ ሳይሆን አይቀርም የሚል ወደዕውነቱ የተጠጋ ጥርጣሬ ቢያሳድር አይፈረድበትም፡፡ በበጋ ወቅት አቶ ፀጋ ብቅ አድርገውት መቋጫው ምን እንደደረሰ ያልተነገረን የ60 ሚሊዮኑ ብር ንቅዘት ደግሞ ከላይ የተባለውን ጥርጣሬ አጠናካሪ ነው፡፡ ገና ምኑ ታይቶ ተብለን ሌላም የንቅዘት ጉድ ለመስማት ጆሯችንን ኮርኩረን አፅድተን እየጠበቅንም ነበርኮ፡፡

ውድ አንባቢያን እዚህና እዚያ እየረገጥኩ እንዳሰለቸኋችሁ ይገባኛል፡፡ ኾኖም ወደጽሑፌ ዋና ማጠነጠኛ ፍሬ ነጥብ እየገባሁ ነውና በአቶ ፀጋ አራጌ ሐሳብ ዙሪያ የማልስማማበትን ትንሽ ማለት እችል ዘንድ ታገሱኝ፡፡

አቶ ፀጋ “የታፈንኩት እኔ ብቻ ነኝ ብየ አላምንም፤ የታፈነው የአማራ ሕዝብ ነው” ብለው እርሳቸው ማለት ጠቅላላው አማራ መላው አማራም እርሳቸው እንደሆኑ ራሳቸውን አሳምነው  ያሰራጩትን ሀሳብ ግን የማልስማማበትም መኮነን የሚገባውም እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ሲጀመር አባባሉ በጽንሠሀሳብ ደረጃ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ግለሰብ ተናጠል እንጂ ብዙኃን አይሆንም፡፡ ብዙኃንም አንድ ግለሰብ ብቻ የመሆን ዕድል የለውም፡፡ ከዚያ ውጭ በግለሰብ ላይ የሚደርስ መልካምም ሆነ መጥፎ ነገር መታየትም መመዘንም ያለበት በተናጠል እንጂ በብሔር መነፀር በጅምላ አይደለም፡፡ ግለሰብ ላይ የሚደርሱ ነገሮችን በጅምላ በብሔር ላይ የደረሱ ናቸው ብለን የምንደመድም ከሆነ ድምዳሜያችን የተሳከረ ነው የሚሆነው፡፡

መሪዎቻችን በተቆነጠጡ ቁጥር ብሔር ውስጥ ለመሸጎጥ የሚያደርጉት ሩጫ የከሰረ ፖለቲካና ጮሌነት መሆኑን አቶ ፀጋ ይዘነጉታል ብየም አላስብም፡፡ እርሳቸው ይኸን ያደረጉትም  ለክብራቸው ጋሻ መከታ ይሆን ዘንድ የዐማራን ሕዝብ ለማነሳሳት መሆኑንም በሚገባ ያውቁታል፡፡ የሚያነጋግረው በአማኑ ቀን በደስታ በፈንጠዝያ ወቅት ትዝ የማይላቸውን አማራ እንቅፋት አጋጥሞኛል ብለው ባሰቡበት ወቅት “ተነስ ታጠቅ፣ ከጎኔ ተሰለፍ” ዓይነት አንድምታ ያለው መልዕክት አስተላልፈው የግርግር ክብሪት በመለኮስ በጫጫታ አውሎ ነፋስ አቧራ ለማስነሳት መሞከራቸው ነው፡፡ በዚህ መልክ ሕዝብ እየቀሰቀሱ አቧራ ማስነሳት በበኩሉ ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ መላዕክት ሊረግጡት የሚፈሩትን ጅል ዘሎ ይገባበታል የሚባለው ያለምክንያት አይደለም፡፡

ደግሞምኮ አቶ ፀጋ ያነሱት የስብሰባ ደንብና ሥርዓት ጥሰት እዚያው ለፕሮቶኮል የሚጨነቁ ተሰብሳቢዎችን ይመለከት ካልሆነ በስተቀር ለአማራ ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ አይደለም፡፡  በአሁኑ ወቅት የአማራ ሕዝብ የማርያም ልጅ ጣልቃ ገብቶ ካላቃለለለት በስተቀር በሰው አቅም ስለመፈታቱ የሚያጠራጥር ፖለቲከኞች ያወሳሰቡት ውስብስብ አጀንዳ ከፊቱ ተቆልሏል፡፡

ከምንም በላይ የሕልውናው ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ በየቦታው ተንኳሹ ብቻ ሳይሆን ጨፍጫፊው በዝቷል፡፡ አማራን ያልገደለ የማርያም ጠላት ነው የተባለ ይመስል ለመኖር ዋስትና ሰጪ መንግስት አላገኘም፡፡ በዚህ ላይ ወደሰማየ ሰማያት እየተተኮሰ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ትከሻውን አጉብጦታል ፤ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል ፤ ረሀብ አጥቅቶታል ፤ እንደመዥገር ተጣብቀው ገንዘቡን ብቻ ሳይሆን ደሙን የሚመጡትም ሙሉ በሙሉ አልጠፉም፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብልሹነት እንደአንበጣ ሀገር ምድሩን የወረረው ስርቆት የአስተዳደር ኢ-ፍትሐዊነት ወዘተ፣… ወዘተ፣… ከጫንቃው ላይ ተቆልሏል፡፡ ስለዚህ ይኸ ሕዝብ አሁን የሚፈልገው ከላይ የተዘረዘሩትንና ያልተዘረዘሩ ከተራራ የገዘፉ እንከኖች ከላዩ ላይ ገፎ የእፎይታን አቅጣጫ የሚያመላክት ብልህ መሪ እንጂ በውስጠ ፓርቲ ትግል በሚፈታ ኢምንት አጀንዳ ሰበብ በሚፈጠር ውዝግብ ክብሬ ተነካ ብሎ በእርሱ ላይ የሚደርስን አላስፈላጊ ነገር ወደብሔር መበደል ለማጠጋጋት የሚፈልግ አካል አይደለም፡፡ በጥቅሉ መሪዎቻችን በትንሽ በትልቁ በተቆነጠጣችሁ ቁጥር በብሔር ጉያ ለመሸጎጥ የምታደርጉት ሩጫ አጉል ጮሌነትን የተላበሰ ውጤቱም የማይጠፋ የነገር እሳት ለኳሽ የፖለቲካ ኪሳራ ነውና እባካችሁ ከዚህ ዓይነት ጮሌነት የተላበሰ እኩይ ተግባራችሁ ታቀቡ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...