በትግራይ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ጉባኤ እንዲካሄድ ጥሪ ቀረበ

Date:


ዓለም አቀፍ የትግራይ ምሁራንና ባለሞያዎች ሕብረት (GSTS)፣ በትግራይ ክልል የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አካታች ብሔራዊ ኮንፈረንስ እንዲካሄደ ጥሪ አቅርቧል። ሕብረቱ በኤርትራ መንግስትና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው  ህወሓት መካከል “ተፈጥሯል” የተባለው ንቅናቄ በአስቸኳይ መቆም  እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ሕብረቱ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን መነሻ በማድረግ፣ ቅዳሜ ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስረዳው፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካይነት “ተፈጽሟል” ያለውን በሃይል የታገዘ የደቡባዊ ዞን አስተዳደር አመራሮች ቅየራ በጥብቅ ኮንኗል።

አክሎም፣ “የሕዝብን ፍላጎት በጠመንጃ ሃይል የማፈንና በሃሳብ የተለየ ትግራዋይን ከመኖሪያ ቀዬው የማሳደድ ተግባራት ከየካቲት ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች በስፋት እየተከወነ ነው” በማለት አትቷል።

እንቅስቃሴው የአስተዳደሩን ስልጣን የማጠናከር ስትራቴጂን በውስጡ ያዘለ መሆኑን ያነሳው ሕብረቱ፣ ይህ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።

“ኮር እና ከኮር በላይ” በማለት ራሳቸውን የሚጠሩና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለሚመራው ህወሓት ድጋፋቸውን የቸሩ የትግራይ ወታደራዊ ሃይል አዛዦች፣ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ያወጡትን የአቋም መግለጫ ተከትሎ፣

በወቅቱ በአቶ ጌታቸው ረዳ ፕሬዚዳንትነት ይመራ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ከአዛዦቹ አቋም በተቃራኒ አቅጣጫ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ በመቆየቱ ሳቢያ፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩ እንዲፈርስ፤ ኬላዎችን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በማቋቋም የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ፤ ሕዝብም እንዲሸበርና ሕዝብ ባልመረጠው አስተዳደር እንዲመራ በማድረግ ረገድ ይኸው ወገን ተጠያቂ መሆኑን ሕብረቱ በመግለጫው አመልክቷል።

GSTS መግለጫውን ሲቀጥል፣ “በፈረሰው የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ምትክ ስልጣኑን የተቆናጠጠውና በሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራው አስተዳደር ካለፉት ስሕተቶች በመማር ትግራይን ወደ ተሻለ የሰላም መንገድ፣ መልሶ መቋቋምና የክልሉ ነዋሪዎችን ተስፋ ማለምለም ‘ይወስዳቸዋል’ ተብሎ ሲጠበቅ፤ በተቃራኒው አቅጣጫ በማምራት የአንድ የፖለቲካ ቡድን የስልጣን ጥምና ጥቅም ለማርካት፣ ብሎም ከተጠያቂነት ለማዳን የትግራይ ሕዝብን በመያዣነት አግቶ ይዟል። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ በከባድ ጭንቀትና ሽብር ውስጥ ይገኛል” በማለት አስረድቷል።

በመሆኑም፣ ሕብረቱ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ ለምሁራንና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ባቀረበው ጥሪ መሰረት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በደቡባዊ ዞንም ሆነ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች በጠመንጃ አፈሙዝ የታገዘ “ሕዝብን የማንበርከክ ዕንቅስቃሴው” ወደ ተጨማሪ ግጭትና ግርግር ከማምራቱ በፊት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል።

በተጨማሪም ሕብረቱ፤ “ጽምዶ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው፣ “ሕጋዊ መሰረት የሌለው”፤ የትግራይ ሕዝብን ወደ ፍጹም ውድመት የሚወስደውና ትግራይ “የውክልና ጦርነት ዓውድማ” ሊያደርግ የሚችለው የጥምረት ንቅናቄ በአፋጣኝ እንዲገታ አሳስቧል።

በመጨረሻም፣ የጸጥታ ሃይሎችን፤ የሲቪል ማሕበራትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ አካታች ብሔራዊ ኮንፈረንስ ገለልተኛ በሆነ ተቋም አማካይነት እንዲጠራና ለትግራይ “መፍትሔ የሚያስገኙ ሃሳቦች” የሚንሸራሸርበት ውይይት እንዲደረግ GSTS ጥሪ አቅርቧል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...

ኢራን ድርድር ውስጥ ከገባች “እጇ ከቃታው ላይ” አይነሳም

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር የምታደርግ ከሆነ ንግግር ውስጥ የምትገባው...

ለቅርስ ጥበቃና ምርምር የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም

የቅርስ ጥበቃና የምርምር ዘርፍ ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አስፈላጊ...