በትግራይ ክልል በጦርነትና በክረምቱ ከባድ ዝናብ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በርካታ ቅርሶች የማደስና የመገንባት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
የመልሶ ማቋቋም ጥረቱ የአክሱም ሃውልት እና ታሪካዊውን የአል ነጃሺ መስጊድን ጨምሮ፤ ቁልፍ ባህላዊ ምልክቶችን በመጠበቅ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃይላይ በየነ እንደገለጹት ከፌዴራል ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ የማገገሚያ ሥራው በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ነው።
“እነዚህን በዋጋ ሊተመን የማይችል ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ኢትዮጵያም ትልቅ ታሪካዊና ባህላዊ ጠቀሜታ ስላላቸው ወደ ቀድሞ ክብራቸው ለመመለስ እየሰራን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ምልክቶች አንዱ የሆነው የአክሱም ሃውልት ጥናትና ግምገማ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፤ በቅርቡም የተሃድሶ ሥራ ለመጀመር እቅድ ተይዟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፍተኛ ሐይማኖታዊ እና ታሪካዊ ፋይዳ ያለው የአል ነጃሺ መስጂድ እድሳት 90 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአፍሪካ አንጋፋ የሆነው መስጊድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ፤ ላለፉት ሰባት ወራት በእድሳት ላይ ይገኛል።
የክልሉን ባህላዊ ቅርስ ችግሮች ለመፍታት ቢሮው ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ሀይላይ አፅንኦት ሰጥተዋል። “እነዚህ የማገገሚያ ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን መልሶ ለመገንባት ብቻ ሳይሆን ማንነታችንን እና ታሪካችንን ለመጪው ትውልድ የማስጠበቅ ነው” ሲሉም አክለዋል።
በግጭቱ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ከፍተኛ ውድቀቶችን ያጋጠመውን የትግራይን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት እየተካሄደ ያለው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሰፊ እንቅስቃሴ አካል መሆኑንም አመላክተዋል።
ባለሥልጣናቱ የተመለሱት ቅርሶች በቅርቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን በመሳብ፤ ለቀጠናው ኢኮኖሚ ማገገም አስተዋፅዖ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አላቸው።
@አሐዱ
