
በትግራይ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ባጋጠሙ 741 የትራፊክ አደጋ የ187 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ 373 ከባድና 182 ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰ በትግራይ ክልል የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥርና አደጋዎች ማጣራት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር ተስፋይ ገብረመድህን ተናግረዋል።
በዚህ ምክንያትም እነዚህን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተበራከተ ያሉ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቀነስ ሲባል በሀገር ደረጃ የወጣውን የትራፊክ ቁጥጥር ደንብ 557/2016 ወደ ትግበራ ለማስገባት አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ገልፀዋል። ነገር ግን የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ጠንካራ መንግስታዊ ቁመና የሌለው መሆኑ ህግና ስርዓት ለማስከበር አዳጋች እንዳደረገው ተገልፆል።
በአዲሱ ደምብ መሰረት ቅጣቶቹ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ተብለው የተለዩ ናቸው ያሉት ኮማንደር ተስፋይ በአንደኛ ደረጃ ላይ ያሉ ጥፋቶች የ500 ብር ቅጣት፣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ጥፋቶች የ1000 ብር ቅጣት፣ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ጥፋቶች ደግሞ በ1500 ብር የሚያስቀጡ መሆናቸው ገልፀዋል።
ዳይሬክተሩ አክለው ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ንብረቶችን በመንገድ ላይ በማራገፍ መንገድ የዘጉ ከ2 እስከ 20 ሺ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተናግረዋል። ደንቡ በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ሲሆን በትግራይ ክልልም አስፈላጊ ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኃላ በያዝነው ሳምንት ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ሲሉ የትግራይ ክልል የትራፊክ ድህንነት ቁጥጥርና የአደጋዎች ማጣራት ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር ተስፋይ ገብረመድህን ተናግረዋል።