በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች 65% መጨመር ተፈቀደላቸው

Date:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ሚገኙ 1,227 የግል ትምህርት ቤቶች በ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን፣ እስከ 65 በመቶ ድረስ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸው ሲሆን፣ የጭማሪውን ጣሪያ 65 በመቶ መጨመር እንዲችል የተፈቀደለት ግን አንድ ትምህርት ቤት ብቻ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ባፀደቀው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግል ትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሠራር ሥርዓት ረቂቅ ደንብ ቁጥር 194/2017 መሠረት፣ በ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 1,585 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1,227 ያህሉ እስከ 65 በመቶ ብቻ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ ይችላሉ፡፡

በ2018 ዓ.ም. ጭማሪ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ 1,227 ትምህርት ቤቶች አስቀድሞ የክፍያ ጭማሪ መነሻ ሐሳባችሁን አቅርቡ ሲባሉ የዋጋ ግሽበት (Inflation) ጨምሯል በሚል ያቀረቡት ጭማሪ አስደንጋጭ ነበር ብለዋል፡፡

ከትምህርት ቤቶቹ ውስጥ አሥር በመቶ የሚሆኑት ብቻ እስከ 50 በመቶ የጭማሪ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ቀሪ 90 በመቶ ያህሉ ከ75 እስከ 263 በመቶ ጭማሪ ማቅረባቸውን አቶ ኢዘዲን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች፣ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቢሮ፣ የንግድ ቢሮ፣ የፕላንና ልማት ቢሮ፣ የፍትሕ ቢሮና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በተሳተፉበት ጥናት፣ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችልና በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚኖር የዋጋ ጭማሪ ጣሪያ ይፋ መደረጉን አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የክፍያ ጭማሪ ጣሪያውን ሲያስቀምጥ አንዱ መሠረት ያደረገበት ነጥብ የትምህርት ቤቶች ጥራት ነው ያሉት አቶ ኢዘዲን፣ በዚህም ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ተብለው በመሥፈርት መለየታቸውን አክለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ጥራቱ የተሻለ የሚባለው ደረጃ አራት ትምህርት ቤት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

<<ደረጃ አራት የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት ቤት ነው፣ ጭማሪ ሲደረግም ከደረጃ ሁለት ጋር እኩል መሆን የለበትም ስለዚህ ጭማሪውን በፐርሰንት (በመቶኛ) አለያይተነዋል›› ብለዋል።

በዚህም ቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉት እስከ 45 በመቶ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

<<45 በመቶ ጨምሩ ማለት ሳይሆን ከዜሮ ጀምሮ 10፣ 30፣ 45 በመቶ ብቻ መጨመር ይችላሉ ነገር ግን ከዚህ በላይ ማለፍ አይችሉም፤›› ብለዋል።

አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 40 በመቶ፣ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 45 በመቶ፣ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 55 በመቶ ዋጋ መጨመር ይችላሉ ተብሏል።

በጣሪያው መሠረት 144 ትምህርት ቤቶች እስከ 40 በመቶ፣ 591 ትምህርት ቤቶች እስከ 45 በመቶ፣ 378 ትምህርት ቤቶች እስከ 50 በመቶ፣ 47 ትምህርት ቤቶች እስከ 55 በመቶ፣ 66 ትምህርቶች እስከ 60 በመቶ ሊጨምሩ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድ ትምህርት ቤት ብቻ የመጨረሻውን ጣሪያ ማለትም እስከ 65 በመቶ ክፍያ መጨመር እንደሚችል አቶ ኢዘዲን አመላክተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 1,585 ትምህርት ቤቶች መካከል 358 ያህሉ በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የጨመሩ ስለሆኑ በቀጣዩ ዓመት እንደማይጨምሩ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ትምህርት ቤቶች ክፍያ መጨመር የሚችሉት በ2019 ዓ.ም እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ አሠራር ሥርዓት ደንብ 194/2017፣ የትምህርት ዘመን ሲያበቃ በኅብረተሰቡና በትምህር ቤቶች መካከል ከትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ በተመለከተ ለረጅም ጊዜ የሚስተዋሉ ንትርኮችን፣ በተለምዶ ሲከናወን የነበረውን አሠራር በሕግ አግባብ እንዲመራ እንደሚያደርግ አቶ ኢዘዲን ተናግረዋል።

ደንቡ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፣ የመምህራን ክፍያ፣ ትምህርት ቤቶቹ ማግኘት ያለባቸው ገቢ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ማኅበረሰቡም ሲጠይቅ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኢዘዲን አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶችም አሠራሩን በቀናነት እንደተቀበሉት ተናግረዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል።

ሪፖርተር

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...