Home ተጋባዥ ፀሐፊ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ

ደራሲ- አርኖ ሚሼል ዳባዲ

                                                                   ተርጓሚ- ገነት አየለ አንበሴ

                                                                   ቅኝት- አበራ ለማ

አርኖ ሚሼል (ሚካኤል) ዳባዲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1837 – 1848 በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ ያሰተዋለውን የዘመነ መሳፍንት ገጽታ በመጽሐፍቱ አሳይቷል፡፡ ሚሼልና ወንድሙ አንቷን ዳባዲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት፣ በጂኦግራፊ፣ በአርኪዮሎጂና በታሪክ ረገድ ከፍተኛ ጥናት አካሂደዋል፡፡ በዚህ የሚካኤል ቆይታ ዓመታትም አራት ተከታታይ መጻሕፍትን ሰለ ዘመነ መሳፍንት በፈረንሳይኛ  ቋንቋ ጽፎልናል፡፡ እስካሁን ሁለቱን ገነት አየለ ወዳማርኛ መልሳ አሰነብባናለች፡፡

መጽሐፎቹ የዘመነ መሳፍንትን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ባሕል፣ አስተዳደር፣ የጦር ኃይል አሰላለፍ፣ የዘመኑን ሰው አስተሳሰብና ሌሎችንም ጉዳዮች ያካተቱ ናቸው፡፡ ይህንን የዘመነ መሳፍንት ጉዳይ አንስተው የጻፉ ሌሎች ደራሲዎችም አሉ፡፡ ላብነት ያህል ሁለት ተጨማሪ ጸሐፍትን እዚህ ላይ እጠቅሳለሁ፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ

1.  እንገሊዛዊው ናትናኤል ፒርሰ ከ1810-1819 ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረና ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› የሚል መጽሃፍ የጻፈና ብርሃኑ በላቸው ወዳማርኛ የመለሰው፣

2. አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ (1864-1917) ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› የሚል መጽሃፍ የጻፉ ናቸው፡፡

ሦስቱም ጸሃፊዎች የዘመነ መሳፍንትን ሁለንተናዊ ገጽታ በዝርዝር ጽፈዋል፡፡ ሚካኤል ግን በጥልቀት በማጥናትና በመተንተን ሌሎቹን ይበልጣቸዋል፡፡ የሦስቱም ደራሲዎች አቢይ ትኩረት ግን በዘመኑ የጦርነት ወከባና የእርስ በርስ ሽኩቻ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይኸውም፡-

**ራስ አሊ  ከደጃች ጎሹ፣ ከደጃች ውቤ፣ ከደጃች ብሩ፣ ከደጃች ካሣ ኃይሉና ከሌሎችም ጋር ያካሄዱት ጦርነት፣.

**ደጃች ጎሹ ከራስ አሊ፣ ከደጃች ውቤ፣ ከደጃች ሥዩም፣ ከራሳቸው ልጅ ከደጃች ብሩ፣ ከኦሮሞ ባላባቶችና ከሌሎች ጋር ያካሄዱት ጦርነት፣

**ደጃች ብሩ ከራስ አሊ፣ ከደጃች ሥዩም፣ ከደጃች መርሶ፣ ከራሱ አባት ከደጃች ጎሹና ከሌሎችም ጋር፣

**በትግራይ ራስ ወልደ ሥላሴ ከሰባጋዲስ፣ ከኦሮሞ ባላባቶች፣ ከራስ ጉግሳ፣ ከራስ ኃይሉ፣ ከራስ ገብሬና ከሌሎችም ጋር፣

**በትግራይ የነ ወልደ ሩፋኤልና የነ አውረሰው ግጭት፣ የሰባጋዲስና የወልደ ሩፋኤል ጦርነት፣ የወልደ ኪዳን፣  የግራዝማች ሕዝቅያስና የነገብረ ሚካኤል ጦርነቶች ለምሳሌ ያህል ይጠቀሳሉ፡፡

**ባጠቃላይ ዘመነ መሳፍንት የጦርነት፣ የዘረፋ፣ የግድያና የፉክክር እንደነበር የዘመኑ ጸሐፊዎች እነ ሚካኤል ዳባዲ በሰፊው ጽፈውበታል፡፡

በዘመኑ የመሳፍንቱ የጭካኔ ሥራዎች ** ጥቅሰ መርድ የሚባለውን ስመ ጥር የጦር አበጋዝና ታማኝ ሰው በገዛ አለቃው በደጃች ብሩ ትእዛዝ የቀኝ እጅና እግሩ ተቆርጦ፣ ተሰቃይቶ እንዲሞት ተደርጓል፡፡

** አባ ሳህሉ የተባለውን ጎበዝ የጦር መሪና ታዛዥ ሰው ጌታው ደጃች ሥዩም በተራ ጥርጣሬና ቅናት ተነሳስቶ የቀኝ እጁንና እግሩን አስቆርጦ ለሞት አብቅቶታል፡፡

**ወይዘሮ መነን፤ ዘመዳቸcውን ኃይሉ ታምሩን የመሰለ የጦር መሪና ጀግናን የድካም ዋጋውን ከመንፈግ ባሻገር፣ ሕይወቱንም ለማጥፋት አርዝመው የሄዱበት መንገድ ያሸማቅቃል፡፡

**ራስ አሊ ትልቅ የጀግንነት ሥራ የሠሩላቸውን እነደጃች ብሩ አሊጋዝን፣ እነደጃች መርሶንና አነደጃች ሊበንን አስረው፣ ከሥልጣናቸው ሽረውና አሰቃይተው ነውረኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡

በዘመኑ የነበሩት መሳፍንቶችና ጦረኞችና እጅግ ጨካኞች ነበሩ፡፡ የጠሉትን ሰው እጅና እግሩን ቆርጠው እያሰቃዩ ይገሉ ነበር፡፡ ለማሳያ ያህል የሚከተሉትን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡-

**ደጃች ብሩ ያያቱ የደጃች ዘውዱና የራሱም ምስጉን ሹም የነበሩትን የእድሜ ባለጸጋ አዛውንት፣ አባይን ሊሻገሩ ሲሞክሩ ውሃው ጠልፎ ሲወስዳቸው ቆሞ እያየ፣ ‹‹እንደ ባዶ ብርሌ ብቅ ጥልቅ እያለ…›› በማለት እያፌዘ ይስቀባቸው ነበር፡፡ ደጃች ብሩ እጅግ እብሪተኛ፣ እጅግ ጨካኝ፣ ያልተረጋጋና ተጠራጣሪ ሰው ነበር፡፡

**ደጃች ውቤም ከወዳጃቸው ጋር የማይሰነብቱ አድርባይ፣ ከሃዲ፣ ጨካኝና ክፉ ሰው ነበሩ፡፡

**ወይዘሮ መነን ሸረኛ፣ ተንኮለኛ፣ የሥልጣን ጥመኛ፣ ነገረ ሰሪ፣ ተጠራጣሪና ውለታቢስ ሴት ነበሩ፡፡ እሳቸውን ልክ ያስገባው ቋረኛው ካሣ ኃይሉ አማቻቸው ብቻ ነበር፤ ያውም በጦር ሜዳ ተፋልሟቸው፡፡

**አጤ ቴዎድሮስ አገር ላገር እየዞሩ ወረራ የሚፈጽሙበት ዋና ምክንያታቸው አልገብር ያሏቸውን ጎበዝ ለማንበርከክ ነበር፡፡ ታዲያ ወረራውን ሲፈጽሙ ገደብ የሌለው ዘረፋ በወታደሮቻቸው ከማስፈጸማቸውም በላይ፤ እጅግ ዘግናኝና ተዋዳዳሪ የሌለው የጭካኔ ተግባር ይፈጸሙ ነበር፡፡ የብዙ ድሃ ገበሬ እጅና እግር እያሰቆረጡ አገሩን ያለ አባወራና የቤተሰብ መሪ ያስቀሩ ነበር፡፡ የእሳቸው መዋእለ ዜና ጸሐፊዎች እነ አለቃ ዘነብና አለቃ ወልደ ሚካኤል በዝርዝር ከጻፉት የቴዎድሮስ የጭካኔ ሥራ በተጨማሪ፣ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ በመጽሃፋቸው ላይ በዝረርዝር ጽፏል፡፡ አለቃ ‹‹ ባንድ ቀን ብቻ 1500 ሰው አቃጠሉ፤ ከዚያም ቁጭ ብለው አምላኬ ለምን ጨካኝ አደረከኝ ብለው አለቀሱ›› ይሉናል፡፡ ይህ ያጤ ቴዎድሮስ የጭካኔ ተግባር በቀሳውስቱም ሆን በመጨረሻም በመቅደላ አምባ አስረኞች ላይ እጅ እግር እየተቆረጠ እንደተፈጸመ፣ ዶክተር ሄንሪ ብላንክ ባይን ምስክርነት በጻፉት ‹‹የእስራት ዘመን ባበሻ አገር›› በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ አመልክተዋል፡፡ ዳኘው ወልደ ሥላሴ ወዳማርኛ የመለሰውን ልብ ይሏል፡፡

ይህ የመሪዎች የጭካኔ ተግባር ከዚያም በኋላ ባጼ ዮሃንስ፣ ባጼ ምንሊክ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በወያኔ ዘመን ቅርጹን በቀያየረ መልክ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የመሳፍንቱ ዘመን መጥረቢያንና የመሳሰሉትን የእጅ መሣሪዎችን ለመቅጫ ሲጠቀም፣ ሰልጠን ባለው በወዲኛው ዘመናት ግን በዋነኝነት በጥይት ደብድቦ መግደልንና መስቀልን ገዢዎች መርጠው ለመቅጫ ተጠቅመውበታል፡፡

የጭካኔ ነገር ከተነሳ ወዲህ በኛው ዘመን በደርግ ዘመን በ60 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሹማምንት ላይ ደርግ የፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ለማሳያነት መጥቀስ ይበቃል፡፡ ጀብሃም ተሰነይ አሊ ጊደር ላይ በሐምሌ ወር 1970 ዓ.ም. የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጅል የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ባይን ምስክርነት የሚያስታውሰው ነው፡፡ ጀብሃ በቁጥጥሩ ስር የነበሩ 300 የኢትዮጵያ ወታደሮችን በምርኮኝነት ሲያሰቃይ ቆይቶ፤ ጀግናው የ501 ግብረ ኃይል ምርኮኞቹን ከጀብሃ ሊያስለቅቅ 12 ሰዓታት ሲቀሩት፣ ጀብሃ በመትረየስ ረፍርፏቸውና ቤንዚን አርከፍክፎ አቃጥሏቸው ከስለው ተገኝተዋል፡፡

የሴት ልጆች እጣ ፈንታ በዘመነ መሳፍንት

የመሳፍንቱ ቤተሰብ ሴቶች ልጆች የወላጆቻቸውን በጎ ፈቃድ ፈጻሚዎች አሻንጉሊቶቻቸው ነበሩ፡፡ ሴት ልጅ ውለታ መክፈያ፣ ሥልጣን ማቆያ፣ ግዛት ማስፋፊያ፣ ወገን ማብዣ፣ ወንበር መግዣና ወዳንዱ መጠጊያ ሁና እንድታገለግላቸው ብቻ ይጠቀሙባት ነበር፡፡
ያለእድሜያቸው ጥቅም ፍለጋ ላንዱ ለፈለጉት ሰው ይድሯቸዋል፣ ወዲያው ደሞ አፋተው ላንድ ለሌላ ለፈለጉት ሰው ይድራሉ፡፡ ትንሽ ቆይተው ደሞ ሴትን ልጅ ያፋቱና ለሌላ ለፈለጉት ሰው ይድሯታል፡፡ ሴት ልጅ

እራሱ የራስ አሊ አማች የሆነ ሰው ነው፡፡ የራስ አሊን እህት ወይዘሮ የውብዳርን አግብቶ የሚኖር ክፉ ሰው ነበር፡፡

ብዙ መሳፍንት በትርፍ ሚስትና ቅምጦች የቶጀሩ ናቸው፡፡ ናትናኤል ፒርስ እንደጻፈው፣ አጼ ተክለ ጊርጊስ 12 ሚሰቶች ነበሯቸው፡፡ እኚህ ንጉሥ ሲሞቱ ልጃቸው ኃይሉ ያባቱን ሚስት ወይዘሮ ሰረቁሽን አግብቶ ኖሯል፡፡

ሌላው የመሳፍንቱ ነውር የበጅሮንድ ዮሃንስ ልጅ ኃይሉ አባቱ በሕይወት እያሉ እንጀራ እናቱን አግብቶ ሁለት ልጆችን ወልዷል፡፡ የ70 ዓመቱ አዛውንት የትግራዩ ራስ ወልደ ስላሴ ደግሞ የ13 ዓመት ሕጻን አግብተው ይኖሩ ነበር፡፡ አጼ ቴዎድሮስ፣ ደጃች ጎሹ፣ ደጃች ውቤ፣ ደጃች ብሩና ሌሎችም ብዙ ቅምጦችና የጭን ገረዶች ነበሯቸው፡፡ ወደዚህ ዘመን ተሻግረን የንጉሳውያኑንና የመሳፍንቱን ጓዳ ስንፈትሽ፣ ይህ ሴት ልጅን ያለእድሜ መዳር፣ ማፋታትና ለፈለጉት መዳር፣ አሁንም እያፋቱ መዳር በጣም ተዘውትሮ እናያለን፡፡በቤተሰቦቹ ሙዚየም የሚገኘው ሚሼል ጋሻ

እንዲሁ ሕይወቷ ሳይረጋጋ ካንዱ ጭን ወዳንዱ ጭን ስትተላለፍ እድሜዋን ባዘንና በትካዜ ትጨርሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ— ደጃች ውቤ ልጃቸውን ወይዘሮ ሂሩትን ከራስ አሊ አፋተው፣ ለደጃች ብሩ ድረዋታል፡፡ ደጃች ብሩ

ለምሳሌ፡-

እቴጌ ጣይቱ ሁለት አግብተው ፈተው ሲኖሩ፣ በምንሊክ ትእዝ ያንኮበሩን አንድ ቀኛዝማች እንዲያገቡ ይደረጋሉ፡፡ ትንሽ ቆይተው ደሞ ምንሊክ እራሳቸው ከቀኛዝማቹ አፋተው አራተኛ ባላቸው ሁነው ይጠቀልሏቸዋል፡ እራሳቸው ጣይቴም በተራቸው የእህት የወንድም ልጆቻቸውን ከጎንደር እያስመጡ ላንዱ የዘመኑ መኳንንት እየዳሩ እያፋቱ ደሞ ለሌው እየዳሩ ብዙ ወገን ለማፍራት የሄዱበት መንገድ አለ፡፡

የእንጀራ ልጃቸውን ወይዘሮ ዘውዲቱ ምንሊክን ለወንድማቸው ለራስ ጉግሣ ወሌ፣ ሌላይቱን የወንድማቸውን ልጅ ከፈይ ወሌን ከትግሬው መስፍን ከራስ መንገሻ ዮሃንስ፣ የወንድማቸውን ልጅ ወይዘሮ ምንትዋብን ለራስ መኮንን፣ የእህታቸውን የልጅ ልጆች ታላቋን አልማዝ መንገሻን የንጉሥ ሳህለ ስላሴ ቤተሰብ ለሆኑት ለደጃዝማች ታዬ ጉልላቴ ሲድሩ፣ ታናሽቱን አስቴር መንገሻን ደግሞ ልጅ ኢያሱ እንዲያጩዋት አድርገዋል፡፡

እቴጌ መነን አስፋው ላይም የተፈጸመው ተመሳሳይ ከሞራል ውጭ የሆነ ድርጊት ነው፡፡ ወላጆቻቸው ገና በልጅነታቸው ለሁለት የወሎ ጃንጥራሮች በተለያየ ጊዜ ድረው ካፋቷቸው በኋላ ለሶስተኛ ባል ይድሯቸዋል፡፡ ሦስተኛው ባል ፊታውራሪ ልዑልሰገድ ሲሆኑ፣ የመጀመሪያ የጋራ ልጅ ወልደውላቸው አራስ ቤት ተኝተው እያሉ፣ አጎታቸው ልጅ እያሱ መነን አስፋውን ከፊታውራሪ ልዑልሰገድ አፋተው ለራስ ተፈሪ መኮንን ድረዋቸዋል፡፡

ባጠቃላይ ዘመነ መሳፍንትም ሆነ ዘመነ ነገሥታት ለሴት ልጆች የማይመች ብዙ ጭቡ የተሰራበት እንደነበር እንገነዘባለን፡፡

ጨዋና ስመ ጥር ሰዎች

**ሊቅ አጽቁ ቁም ነገረኛና አርቆ አሰተዋይ ሰው እንደነበሩ ሚካኤል በብዙው ይነግረናል፣ ሚካኤልና እሳቸው ሲሰነባበቱ፣ የሀበሻን ሰው ጸባይ አጥብቆ እንዲያውቅ የመከሩት ምክር አስገራሚ ነው፡፡ ‹‹…ያገሬን ሰው ጠርጥር፣  ያገሬ ሰው መሰሪ፣ ጭቦኛ፣ ወረተኛ፣ መጥፎም ጥሩም ነው›› ያሉት አባባል ሚካኤልን አሰገርሞት መጽሃፉ ላይ ጠቅሶታል፡፡

**የደጃች ጎሹ ባለቤት ወይዘሮ ሣህሏ የስመ ጥሩ ሴት ወይዘሮና የጨዋ ሴት ተምሳሌት ሁነው እናገኛቸዋለን፡፡

**ኃይሉ ታምሩ፣ መሃመድ ገልሞ፣ ጥቅሰ መርእድ፣ አባ ስሁልና የመሳሰሉት ትጉሃን ለወዳጆቻቸው፣ ለጌቶቻቸውና ለጓደኖቻቸው እጅግ ታማኝና ሃቀኞች መሆናቸውን እናያለን፡፡

የአርኖ ሚሼል ዳባዲ ሰብእናና ጽሑፎቹ

ሚሼልን በነዚህ ሁለት ሥራዎቹ ወስጥ ዘልቀን ስንፈትሸው፣ ከፈረንሳዊነቱ ይልቅ ሀበሻ ሀበሻ የሚሸት ሰብእና እያየለበት መምጣቱን እናያለን፡፡ ይህንኑ የሚያጠናክርልልን መንፈሱን ገጽ 91 ላይ፣ ‹‹ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን በላይ ሰለአገራቸው ያወቅሁ ይመስለኛል›› ሲል አስምሮበታል፡፡ በተጨማሪም ገጽ 70/71 ላይ እንደምንመለከተው፤ እጁን በየመሳፍንቱ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ሁሉ እንደሚያገባና ባማካሪነትም እንደሚያገለግል እንረዳለን፡፡ ያማክራል ፣ ምስጢራዊ ደብዳቤዎች ይለዋወጣል ወዘተ…

ሚሼል ጥሩ ታሪክ ጸሀፊና ተራኪ ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ ገጸ ባህሪ ቀራጭ፣ ገላጭና አሰተዋዋቂ ካሜራ የሆነ ብእር ያለው ሰው ነው፡፡ እያንዳንዱን ድርጊት በዝርዝር የመጻፍ ብርታት ያለው ነው፡፡ ሁሉንም ነገር እንዳጉሊ መነጽር አጉልቶ በብእሩ ያሳየናል፡፡ ባጻጻፉ ከመናገር ይልቅ ማሳየትን የሚመርጥ ብርቱ ጸሐፊ ነው፡፡

በገነት ግሩም አማርኛ እንዲህ የጣፈጠን፣ በፈረንሳይኛ ቋንቋው እንዴት ሊጥም እንደሚችል ለማጣጣም በጣም ያጓጓል፡፡

ከሚሼል ረቂቅ ጽሑፎች

አርኖ ሚሼል ዳባዲ ከሁሉ መሳፍነት ጋር ተስምቶና ተግባብቶ መኖር የቻለ ብልህ ሰው ነበር፡፡ ለወዳጆቹ እጅግ ታማኝና ለችግራቸው ፈጥኖ ደራሽ ሰው ነበር፡፡

ለምሳሌ ያህል—- ገጽ 81/82 ላይ ጓደኛሞቹን ኃይሉ ታምሩንና መሃመድ ገልሞን የገለጸበት ሥእላዊ አተራረክ አጀብ ያሰኛል፡፡ ገጽ 125 ላይ ደግሞ ደጃች ብሩ እጅግ የሚወደው ፈረሱ ዳምጠው ሲሞትበት፣ የሃዘን ስሜቱን እንዴት እንደገለጸ ሚሼል የሚተርከው ክፍል፣ ለሁኔታው እጅግ ቅርብና ባይን ምስክርነት የምናውቀው ዓይነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ

ነው፡፡

ባጠቃላይ ሚሼልን የመሰለ ተመራማሪና የታሪክ ጸሀፊ በዚያን ዘመን ባይታደለን ኖሮ፣ ያ ሁሉ ሁካታ፣ ሽብር፣ ጦርነት፣ ሽኩቻና መከራ የበዛበትን ጨለማውን የመሳፍንት ዘመን ታሪካችንን፣ አንዲህ በጥልቀት የሚነግረን ሳናገኝ እንቀር ነበር፡፡

የገነት አየለ አንበሴ የተርጓሚነት ሚና

ገነት አየለ የሚሼልን ተከታታይ ሁለት ሥራዎችና የጋል ፋይን ‹‹ትንሷ አገር››ን ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ወዳማርኛ መልሳ አስነብባናለች፡፡ ቀደም ሲልም የደርጉን ሊቀመንበር፣ የኢሠፓን ሊቀመንበር፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና ሌላም ሌላም  የሆኑትን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን አይደፈሬውን ደፍራ ትዝታዎቻቸውን በሁለት ቅጾች አቅርባልናለች፡፡ እነዚህ ሁለት መጽሐፎቿ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ለተመራማሪዎች ማቀበል የቻሉ ናቸው፡፡ በግፍ የተገደለውን ምርጥ ያገሪቱን ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማን እነማን ገዳይና አስገዳይ ሆነው እንዳጠፉት ጭምር፣ የመጀመሪያውን ጠንካራ መረጃ የሰጡን እነዚህ የገነት ሁለት ወጥ ሥራዎች  ናቸው፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባታል፡፡

የገነት ትርጉም ሥራዎች ከትርጉምነታቸው ይልቅ የወጥ ሥራነት ዓይነት ጣእማቸው ጎልቶ ይታያል፡፡ ያማርኛ ቋንቋን እንደልቧ ማዘዝና ለሥነ ጽሑፍ ቋንቋነት የመጠቀም ብቃትዋ በግልጽ ይታያል፡፡ ቋንቋዋ ቀለል ያለና አተራረኳ አንደቀና የቦይ ውሃ እየተንኳለለ ያለ ችግር የሚፈስ ነው፡፡ አልፎ አልፎም የምትጠቀምባቸው ምርጥ ቃላት በዘመናችን እምብዛም የማንጠቀምባቸው ዓይነቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ መዋገድ፣ አረጋገድ፣ አምባላይ ፈረስ ወዘተ… የመሳሰሉት ቃላት ይጠቀሳሉ፡፡

ባጠቃላይ ጀጎልና ለገሃሬ ተወልዳ ያደገች አማርኛ ተናጋሪ ሳትሆን፣ ዋሸራ እነማሆይ ገላነሽ ጉያ ስር ተኮትኩታ ያደገች ያስመስላታል፡፡ በዚህ በነካ እጇም ቀጣዮቹን የሚሼል ዳባዲን ሥራዎች በርትታ ተርጉማ እንደምታቀርብልን ተስፋ አለን፡፡

(ጸሐፊውን ለማግኘት Aberalemma2018@gmail.com ይጠቀሙ)