በትግራይ ክልል በነፃነት እንዳልንቀሳቀስ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ጫና እየተደረገብኝ ነው ሲል የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ለአሐዱ አስታውቋል።
የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ጣዓመ አረዓዶም ከአሐዱ መድረክ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ህወሓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሕጋዊ ፓርቲነት (ሰውነቱ) ከመሰረዙ በፊትም ሆነ አሁንም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ላይ ጫና ያደርግ ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፓርቲያችን ላይ ጫና እያደረገ ነው” በማለት ገልጸዋል።
አቶ ጣዓመ አክለውም፤ “ህወሓት ለውጥ ባለመፈለጉና ሥልጣኑን ለሕዝቡ ባለማስረከቡ ሕዝቡ አሁንም ወደ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እንዲገባ እያደረገው ይገኛል” ብለዋል።
”በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አንድ አንድ ግለሰቦችም ‘የስምረት ፓርቲ ደጋፊዎች ናችሁ’ እየተባሉ እገታና ድብደባ እየተፈጸመባቸው ነው” ያሉም ሲሆን፤ “ፓርቲው አሁን ላይ በክልሉ በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻለም” በማለት ገልጸዋል።
”በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲዎች ሕዝቡ ያለበትን ችግር ተገንዝበው ቅድሜያ ለሕዝቡ ሰላም ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል” ሲሉም አሳስበዋል።
በቀድሞው የክልሉ የጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ስምረት ፓርቲ ከወራት በፊት በመቀሌ ከተማ የከፈተውን የዋና መስሪያ ቤት ጽህፈት ቤት በታጣቂዎች የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ፤ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት ማድረጉን አቶ ጣዓመ መናገራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
(አሐዱ ሬዲዮ)
