በጋብቻ ላይ ተጨማሪ ጋብቻን የመፈፀም ድርጊትን ለማስቀረት የተለያዩ ሥራዎች ቢሰራም ችግሩን አሁንም ድረስ መቅረፍ እንዳልተቻለ የጋምቤላ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።
አንድ ወንድ ሦስትና አራት ሴቶችን የሚያገባበት ልማድ መኖሩን ያነሱት በቢሮው የሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኦላንግ ጋች፤ ይህ ድርጊትም ሴቶች የሚቸገሩበት ጉዳይ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በክልሉ ይህንና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ የሆኑ ድርጊቶችን ለማስቀረት የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ አንስተው፤ ለውጥ እየታየባቸው ያሉ አንዳንድ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም ያለ ዕድሜ ጋብቻ በብዛት የሚስተዋል እንደነበረ አስታውሰው፤ ለልጆች በየትምህርት ቤቱ ስልጠና በመስጠትና የሐይማኖት አባቶችንም በማስተባበር ወላጆች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሰራቱ ቀድሞ ከነበረበት እየቀነሰ ስለመምጣቱ አስታውቀዋል።
ነገር ግን አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት በላይ የሚያገባበትን ባህላዊ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት በተሰራው ሥራ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ አለመምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡን ከማስተማር ባለፈ በአመራር ደረጃ ያሉት ሰዎችን ድርጊቱን እንዳይፈፅሙ በመከልከል ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
