አቶ ሙሉጌታ መኮንን
ከብሔራዊ ባንክና ከአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዕውቅናና ፈቃድ አግኝቶ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ የተመሰረተው ‹‹ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማኅበር››፣ በገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ዘርፍ የፋይናንስና ተዛማጅ የኾኑ አገልግሎቶችን እየሰጠ ሁለተኛ ዓመቱን ለመድፈን እየገሠገሰ ነው፡፡ ለመኾኑ ማኅበሩ በእነዚህ የሥራና የአገልግሎት ጊዜያት ምን አሳለፈ? ውጤታማነቱስ እንዴት ይለካል? ስንል ከሕብረት ሥራ ማኅበሩ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ መኮንን ጋር የሚከተለውን አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡
ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎትን ቢያስተዋውቁ?
ሙሉጌታ፡- ሙሉጌታ መኮንን እባላለሁ፡፡ በአስመጪና ላኪ ሥራ ላይ ተሰማርቼ በንግድ የምተዳደር ሰው ነኝ፡፡ የጳጉሜን የገንዘብ ቀጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ማኅበር ደግሞ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ነኝ፡፡ ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድርን ለማቋቋም ከሐሳቡ ጀምሮ ተካፋይ የነበርኩ ሰው ነኝ፡፡ ጳጉሜን በመተጋገዝ እና የምንችለውን ሁሉ በማድረግ እየደገፍን እዚህ አድርሰናታል፡፡ ወደፊትም ትልቅ ተቋም ትኾናለች፡፡ ጳጉሜን ታዳጊ እና ጀማሪ የገንዘብ ቁጠባና ብድር መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማኅበር ነች፡፡ ማኅበረሰባችን የቁጠባ ባሕልን እንዲያዳብር እና የቆጠበውንም ገንዘብ መልሶ በአራት እጥፍ እና በአነስተኛ ወለድ ብድር ወስዶ ቤተሰቡን እንዲረዳና እራሱን እንዲጠቅም የምታግዝ ድርጅት ነች፡፡
ግዮን፡- ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር አሁን ላይ ለሕብረተሰቡ እየሰጠች ያለው አገልግሎት እንዴት ይገለጻል?
ሙሉጌታ፡- ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ለሕብረተሰቡ የተቻላትን እያደረገች ነው፡፡ ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ለመርዳት ከፍተኛ ሥራ እያከናወንን እንገኛለን፡፡ በዚህም በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ተቋሙን ለመርዳት፣ ከፍ ሲልም ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ለማገዝ በጋራ እየተገናኝን በመወያየት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ብዙ ሠርተናል፡፡ ወደፊትም የተሻለ እንሠራለን፡፡
ግዮን፡- ጳጉሜን ራዕይዋ ምንድነው? ወደፊት ወደ ባንክነት የማደግ እቅድስ አላት?
ሙሉጌታ፡- የጳጉሜን ራዕይ በ2025 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኩራት የሆነ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ማኅበር ሆኖ መገኘት እንጂ ወደ ባንክ ማደግ አይደለም፡፡ ጳጉሜን ብዙ ተጠቃሚ ማኅበረሰብ ያላት ኾና ዝቅተኛው ማኅበረሰብ የመቆጠብ ባሕሉ እንዲያድግ ማድረግ ነው፡፡ የጳጉሜን አባል ኾኖ በትንሽ ብር አባልነት ከፍተኛ ገንዘብ በመበደር እራሱን የሚያሻሽል ሰው እንዲበዛ እንመኛለን ፤ እንሠራለንም፡፡ አንዳንዴ እውቀት ያለው ሰው ብር የለውም፡፡ እውቀቱ ላይ ገንዘብ ቢጨመርበት የተሻለ ሥራ ይሠራል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለማበደር የተዘጋጀን ነን፡፡ ጳጉሜን ‹‹ሰውን መበዝበዝ ሳይኾን ሰውን ማገዝ›› የሚለውን ሐሳብ ራዕይ አድርጋ የምትጓዝ ተቋም ናት፡፡
ግዮን፡- እስካሁን ከጳጉሜን ብድር የወሰዱ ሰዎች ውጤታማነታቸው ምን ያህል ነው?
ሙሉጌታ፡- ከጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ብድር የወሰዱ ሰዎች በተለያየ መንገድ ስኬታማ መኾናቸውን ይገልፃሉ፡፡ እኔ ግን ከዚህም በላይ መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ አሁን ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ኾነ እንጅ፣ እቅዳችን የነበረው ተበዳሪዎችን አሁን ካገኙት በሦስት እና አራት እጥፍ አድገው እነርሱም በተራቸው ተቋሙን የሚረዱበት ደረጃ ላይ ማድረስ ነበር፡፡ ያም ኾኖ ግን አሁንም ቢኾን የጳጉሜን አባላት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሁሉም በየዘርፉ እየጣሩ ነው፡፡
ግዮን፡- የጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር አባል ለመሆን ምን ያስፈልጋል?
ሙሉጌታ፡- አባል ለመሆን የሚያበቁ መስፈርቶች ኢትዮጵያዊ የሆነ እና ዕድሜው ከ18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ፣ በሕብረት ሥራ ማኅበሩ ደንብና መመሪያ ተገዥ ለመሆን ፈቃደኛ የሆነ/ነች መመዝገቢያ 1000.00 ብር የሚከፍል፣ ዕጣ/ሼር በመግዛት የአንድ ዕጣ ዋጋ 1,000.00 ብር ሲሆን አንድ አባል መግዛት ያለበት መነሻው የእጣ መጠን 3 የመድረሻ ዕጣው 10,000፣ የማህበሩን ዝቅተኛ የመደበኛ ቁጠባ መጠን 500.00 ብር ሳያቋርጥ በየወሩ የሚቆጥብ እና የፍላጎት ቁጠባ መቆጠብ የሚችል፡፡
ግዮን፡- የጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምን ምን ናቸው?
ሙሉጌታ፡- የምንሰጣቸው አገልግሎቶች በዋናነት ሸር (ዕጣ) ሽያጭ፣ ቁጠባና ብድር ሲሆን፣ የቁጠባ ዐይነቶቻችንም የመደበኛ ቁጠባ፣ የፍላጎት ቁጠባ፣ የልጆች ቁጠባ፣ የጊዜ ገደብ ቁጠባ፣ የንግድ ቁጠባ፣ የቤት ቁጠባ፣ የመኪና ቁጠባ፣ ወለድ አልባ ቁጠባ፣ የቡድን ቁጠባ፣ የቤት ቁጠባ እንዲሁም አነስተኛ የብድር መድህን አገልግሎት በተጨማሪም የማማከር አገልግሎቶች ናቸው፡፡
ግዮን፡- ተበዳሪዎች ወደ እናንተ ሲመጡ የምታስተናግዷቸው በምን መልኩ ነው?
ሙሉጌታ፡- ለተበዳሪዎች መጀመሪያ የቁጠባ ባሕላቸውን እንዴት ማዳበር እንዳለባቸው እና ምን መሥራት እንደሚፈልጉ እንጠይቃቸዋለን፡፡ የሥራውን አዋጭነት በተመለከተ ካለን ልምድ በመነሳት እናማክራቸዋን፡፡ አልፎም እነርሱ ይዘውት የመጡት ሐሳብ አትራፊ ካልኾነም አማራጭ ዘርፎችን በመጠቆም ውጤታማ እንዲኾኑ እናማክራቸዋለን፡፡ በተጨማሪም ቁጠባን ባሕላቸው እንዲያደርጉ የቁጠባን ጠቃሚነት በተገቢው መንገድ እናስረዳቸዋለን፡፡ ተበድሮ መክፈል ብቻ ሳይኾን ተበድሮ አትርፎ ማበደርም እንደሚገባ በሥነልቦና እንገነባቸዋለን፡፡ ከዛ በብድር መመሪያችን መሰረት እንሳተናግዳቸዋለን፡፡ በዚህ መልኩ ብዙዎቹ ተበዳሪዎቻችን አትራፊዎች መኾናቸውን ተገንዝበናል፡፡
ግዮን፡- ተበዳሪዎቻችሁ የወሰዱትን ብድር ለምን ዓላማ እንዳዋሉት እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ?
ሙሉጌታ፡- ለተበዳሪዎቻችን ብድር ስንሰጥ የሰጠነውን ብድር በተመለከተ ምን ዓላማ ላይ ዋለ የሚለውን የሚያጣራ ራሱን የቻለ ክፍል አለን፡፡ ለምሳሌ ቤት ሊገዛ የተበደረ ግለሰብ መኪና ሊገዛ አይችልም፡፡ ምክንያቱም መኪናም መግዛት ከፈለገ ልናበድረው እንችላለንና፡፡ ነገር ግን ተበዳሪው ይዞት የመጣውን ጥያቄ በደንብ በማጤንና በማጥናት ብድሩን እንሰጠዋለን፡፡ ይህ ሲኾን ደግሞ በድርጅቱ ደንብ መሠረት አንድ ተበዳሪ ቢበዛ 6 ወር ቢያንስ 3 ወር መቆጠብ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የጳጉሜን ዋና ዓላማ ቁጠባን ባሕል ማድረግና በመቆጠብ የተሻለ ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል ማሳየት በመኾኑ ነው፡፡ ተበዳሪዎችም ሐሳብና ምክራችንን ይቀበላሉ፡፡ ወደፊት እንደምናግዛቸውም ቃል እየገባን አልፎም የራሳችንን የሕይወት ልምድ በማጋራት እንሸኛቸዋለን፡፡ ደስተኛ ኾነውም ወደ ሥራቸው ይሄዳሉ፡፡
ግዮን፡- ሰዎች የጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር አባል እንዲኾኑ ምን ዓይነት የአባልነት መመልመያ መንገዶችን ትጠቀማላችሁ?
ሙሉጌታ፡- ሰዎች የጳጉሜን የገንዘብ ቁተባና ብድር አባል እንዲኾኑ የድርጅቱን ዓላማ በማሳየት ማለትም ለትርፍ ሳይኾን ለመርዳት የተቋቋመ መኾኑን በመጥቀስ የሚገኘውን ወለድ ትርፍም ለጋራ የምንካፈል መኾኑን በማሳወቅ እንዲቀላቀሉን እናደርጋለን፡፡ ካለን ማካፈል ማለት ምን ማለት እንደኾነ ለማሳየት እንጥራለን፡፡ ለምሳሌ የእኛ ተቋም አባል የመኾን ፍላጎት ያላቸው ትላልቅ ተቋማት አሉ፡፡ እነርሱ አባል ከኾኑ ካላቸው በማካፈል ብዙዎችን መደገፍ እንደምንችል እናስረዳቸዋለን፡፡ በዚህ መንገድ ሁሉም ሰው ደስተኛ ነው፡፡ አዳዲስ አባላትን ለማካተት በዓመታዊ በዓላችን ላይ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ ማንነታችን እንዲታወቅ በተለያየ መንገድም መረጃዎችን እንበትናለን፡፡ ሁሉም አባላት የሚቀርቧቸውን ሰዎች ስለጳጉሜን ምንነትና ዓላማ እንዲያስረዱ ይደረጋል፡፡ በዚህ መንገድ አዳዲስ አባላትን እናስገባለን፡፡ በቀጣይም አዲስ እቅድ አለን፡፡ በተለይ የባንክ አክሰስ የሌላቸው ተቀጣሪ ሠራተኞችን ከአረብ ሀገር ተመላሽ እህቶቻችንን፣ ጥሩ የማሽከርከር ሥነ-ምግባር ያላቸውን ሹፌሮችንና ሌሎች ማኅበራትን የማቀፍ ዕቅድ አለን፡፡ ሹፌር ለብዙ ዓመት መኪና እየነዳ ገንዘብ ስለሌለው ብቻ የሥራ ሕይወቱ በዚያው ያበቃል፡፡ እኛ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ለመለወጥ ሌላ አዲስ ጥናት አለን፡፡ የከተማችንን አሽከርካሪዎች በማደራጀት ባለመኪና (ባለ ንብረት) ለማድረግ እየተነጋገርንበትና እየሠራንበትም እንገኛለን፡፡
ግዮን፡- አባሎቻችሁ ወይም ማኅበረሰቡ የቁጠባ ባሕሉን እንዲያዳብር እንደ ጳጉሜን ምን ትመክራላችሁ?
ሙሉጌታ፡- የቁጠባ ባሕላቸው እንዲዳብር የተቋሙን ዓላማ በግልጽ እናስረዳለን፡፡ ለሚቆጥቡ አባሎቻቸን ደግሞ የቆጠቡተን ብር ወለድ እናስባለን በተጨማሪም አራት እጥፍ በማበደር እያበረታታን እና ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ መድረስ በጥሩ መሠረት ላይ እንደተገባ ስኬት መኾኑን ለማስገንዘብ እንጥራለን፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለውም ከእኛ ተቋም ጋር የሚሠሩ አካላት ሁሉ ተቋማችን በየጊዜው እያገዛቸው መለወጥ እንደሚቻል እናስረዳቸዋለን፡፡ የእኛን የአነሳስ ሂደትም በአስረጂነት እናነሳላቸዋለን፡፡ የእራሳችን የትናንትና ተሞክሮ ለእነርሱም ትምህርት ይኾን ዘንድ በግልጽ እንነግራቸዋለን፡፡
ግዮን፡- ዓመታዊ በዓላችሁን አስመልክቶ ምን ማስተላለፍ ትፈልጋለህ?
ሙሉጌታ፡- በዓመታዊ በዓላችን ላይ ለታደሙ ልዩ እንግዶቻችን ያለንን እናካፍላለን፡፡ ጳጉሜን ስፖንሰር በማድረግ የተቋማችን ዓላማ ምን እንደኾነ ለማኅበረሰቡ እናሳያለን፡፡ እንደአቅማችን ዘይትና ዱቄት አዘጋጅተን ለልዩ እንግዶቻችን በማቅረብ ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋም ምን ያህል የተሻለ ሐሳብ እንዳላት ለማሰረፅ እንጥራለን፡፡ ጳጉሜን ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች እንደኾነም እናሳያለን፡፡ በዓመታዊ በዓላችን ላይ ይህን መጽሔት ያነበበ ሁሉ ተገኝቶ የተቋማችንን ዓላማ ተረድቶ አባል ቢኾንና ቢደግፈን ደስ ይለናል፡፡ የተሻለ ሐሳብ ያላቸው ሰዎችም እኛን ብቻ ሳይኾን ሀገር እንደደገፉ በመረዳት መጥተው ቢጎበኙን ደስተኞች ነን፡፡ መጪው ዘመን ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመትና እና ጥሩ የሥራ ዘመን እንዲኾን እመኛለሁ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክልን፡፡
ስለ ጳጉሜን ብድርና ቁጠባ የተሰጡ ምሥክርነቶች
‹‹መቆጠብን እንደ ትልቅ ዓላማ እንውሰድ››
አማረ መንግስቱ እባለሁ፡፡ የሥራ ዘርፌ ትራንዚስት ነው፡፡ በግል ደግሞ ለባለቤቴ ዳቦ ቤት ከፍቼ እየሠራሁ ነው፡፡ የጳጉሜ አባል የኾንኩት ተቋሙ ሲመሠረት ጀምሮ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ኾኖኛል፡፡ አባል ለመኾን ያነሳሳኝ ጳጉሜ ብድርና ቁጠባ ተቋም ባንክ የማይደርሳቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች የመድረስ ዓላማ ስላለውና ዓላማውን መጋራቴ ነው፡፡ በዚህም ለ6 ወር 250ሺህ ብር በመቆጠብ አንድ ሚሊዮን ብር ብድር ወስጄ ዳቦ ቤት ከፍቻለሁ፡፡ ክፍያውንም በየጊዜው እየከፈልኩ ነው፡፡ የወሰድኩትን ብድርም ውጤታማ ለኾነ ሥራ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ዳቦ ቤቱ አሁን ላይ ጥሩ እየሠራ ነው፡፡ በሥሬም የተሰወኑ ሠራተኞች አሉኝ፡፡ ወደፊት ደግሞ እቅሜ እየጨመረ ስለመጣ ሰራተኛ የመቅጠር እቅድ አለኝ፡፡ ሰዎች የጳጉሜ አባል ቢኾኑ ከባንክ በተሻለ በቀላል ማስያዣ ብድር ማግኘት ይችላሉ፡፡ ትንሽ ተቆጥቦ የተሻለ ነገር ማግኘት ይቻላል፡፡ ወለዱም ከባንኮች አንፃር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ትልቁ ወለድ 15,000 ሺህ ብር ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የተበደርኩት አንድ ሚሊዮን ብር ሲኾን ወለዱ 15% ነው፡፡ ስለዚህ ከወለዱም ከጊዜም አንፃር ከጳጉሜ ጋር መሥራት ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ስለጳጉሜ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አባላቱ በሙሉ መቆጠብን እንደትልቅ ዓላማ በመውሰድ ቆጥበው ይበደሩና የሚፈልጉትን ሥራ ይሥሩ የሚል ነው፡፡
***
‹‹ዛሬ ይህን ማድረግ ከተቻለ ነገ ደግሞ ወደ ትልቅ ደረጃ መሸጋገር ይቻላል››
ፋሲካ መንገሻ እባላለሁ፡፡ የሥራ ዘርፌ በግል ባንክ ላይ ከተበዳሪዎች ጋር የተያያዘ ሲኾን ክሬዲት አግሪ ነኝ፡፡ ይህ ማለት የተበዳሪዎችን መረጃ የሚይዝ ማለት ነው፡፡ የጳጉሜ ብድርና ቁጠባ አባል ብቻ ሳልኾን መሥራችም ነኝ፡፡ ሼሩ በሚሸጥበት ሰዓት በሥራ ባልደረባዬ አማካኝነት ሼሩን ገዛሁ፡፡ ይህም ከመሥራቾቹ አንዷ እንድኾን አድርጎኛል፡፡ የተቋሙ አባል እንድኾን ያነሳሳኝ ከሥራዬ የተያያዘ ስለኾነና የእነርሱን ከትንሽ ተነሳስቶ ትልቅ መድረስና መለወጥ ማየቴ ይመስለኛል፡፡ በተለይ አቅማችን ከባንክ ጋር ለመሥራት የማንችል ሰዎች ይህን ዓይነት አማራጭ አነስተኛ ቁጠባ ተቋም ሲያጋጥም ልናልፈው አይገባም፡፡ እኔ ለምሳሌ ባልደረባዬ ተመዝገቢ ሲለኝ በደስታ ነው የተቀበልኩት፡፡ ምክንያቱም ስፈልገው የነበረ ነገር በመኾኑ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች ቁጠባዎች ላይ ሞክሬ አልተሳካልኝም ነበር፡፡ ጳጉሜ ግን አቀራረቡ በራሱ ሳቢ ነበር፡፡
የዚህ ተቋም አባል በመኾኔ ያገኘሁት ጥቅም ከሁለት ወር በፊት አስቸኳይ ብድር ፈልጌ ሼሩ ዋስትና ኾኖኝ ብድሩን ማግኘት ችያለሁ፡፡ በተበደርኩት ገንዘብ ከባለቤቴ ጋር ሁለት ነገር ተግብረንበታል፡፡ የመጀመሪያው የከፍተኛ ተቋም ተማሪ በመኾኔ ለመማር ገንዘብ ያስፈልገኝ ስለነበር እሱን ከፍዬበታለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባለቤቴ የራይድ ሹፌር በመኾኑ ለመኪናው የሞተር እድሳት እንዲያደርግ ተጠቅመንበታል፡፡ አሁን ላይ ባለቤቴም የዚሁ ተቋም አባል በመኾን እየቆጠበ ይገኛል፡፡ ወደ ፊት ሐሳባችን ቁጠባችንን በማሳደግ የመኪና ብድር መውሰድ ነው፡፡
ሌሎች ሰዎችም ወደ ጳጉሜ መጥተው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የምመክረው፣ ከምኞት ይልቅ በትንሽ ነገር ጀምሮ ትልቅ መኾንን ይሹ ዘንድ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ አሁን የወሰድኩት ብድር 200ሺህ ብር ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሁለት መቶ ሺህ ብር ምንም አይሠራም፡፡ እኔ ግን ሸክሜን አቅልየበታለሁ፡፡ ተምሬ ከወጣሁ በኋላ ሥራ ቦታዬ ላይ የሚኖረኝ ደረጃ ከአሁኑ ደረጃዬ በጣም የተሻለ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባለቤቴ የመኪናውን ሞተር ሲያድስ 70 እና 80 ሺህ ብር አውጥቶ ነው፡፡ ይህ ከራሱ ቢኾን ያወጣው በጣም ከባድ ነበር የሚኾነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መልከ በብድር ወጪውን ሸፍኖ እየሰሩ መቆጠብና ብድሩን መክፈል የላቀ መንገድ ነው፡፡ ዛሬ ይህን ማድረግ ከተቻለ ነገ ደግሞ ወደ ትልቅ መሸጋገር ይቻላል፡፡ መጀመሪያ ሼሩን ስገዛ 3ሺ ብር ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ አሁን ደግሞ ወደ 9 ሺ አሳድጌዋለሁ፡፡ በቀጣይ ጊዜ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ይኖረኛል፡፡ ጳጉሜ እንደኔ በዝቅተኛው የኅብረሰብ ክፍል ላሉ ሰዎች የሚጠቅም ተቋም በመኾኑ በተቻለ መጠን አባል እንዲኾኑ እመክራለሁ፡፡ ጳጉሜ ብድርና ቁጠባ ተቋምም አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ብሎ ቅርንጫፎቹን አስፍቶ ለበርካታ የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ቢኾን ብዬ እመኛለሁ፡፡
ግዮን ቅጽ 6 ቁጥር 215 መስከረም 2017 ዓ.ም
