ትረምፕ እያንኳኩ ነው – በሩን ከመክፈታችን በፊት መላ እንምታ! በክቡር ገና

Date:

ትረምፕ ቃለ መሀላ አድረገው ስልጣን ከያዙ አንድ አመት ሞላ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የአለም ህግና ስርአት ከትረምፕ በኋላ ጓዙን ጠቅልሎ የሄደ ይመስላል፡፡ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ‹‹ቅድሚያ ለአሜሪካ›› ሲሉ አሜሪካ አንድን ነገር ከፈለገች ትወስዳለች ማለታቸው ነው፡፡ አሜሪካ ያልፈለገችው ህግና ስርአት ደግሞ ተቀዶ ይጣላል ማለት ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ትረምፕ ለግብጹ ፕሬዚዳንት አብድልፈታ አልሲሲ በጻፉት ደብዳቤ በህዳሴው ግድብ የተፈጠረውን አለመግባት ልሸምግል ብለው እጃቸውን ሰደዋል፡፡ የደብዳቤው መንፈስ የወዳጅነት ቢመስልም መልእክቱ ግን ለመዋጥም ለመትፋትም የማይመች ነው፡፡

ካለፉት 12 ወራት የስልጠን ዘመናቸው እንደምንረዳው ትረምፕ ድርድር ሲሉ በሁለት እኩዮች መካከል የሚደረግ ውይይት አይደለም፡፡ እሳቸው ድርድር ሲሉ በአለም አቀፍ ህግ ወይም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርህ መሰረት የሚደረግ ሳይሆን የምለውን ትቀበላለህ አልያም የምወስድብህን እርመጃ ትቀበላለህ ማለት ነው፡፡

ይህን አቋማቸውንም አይደብቁም፤ እንዲያውም ይኮሩበታል፡፡ አለም አቀፍ ህግ የሚባል ነገር እንደሌለና አሜሪካ በተናጥል ያላትን ሀይል ያለገደብ ለመጠቀም የሚያግዳት ነገር አንደሌለም በግልጽ ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ ልሸምግል ሲሉም በዚሁ ማዕቀፍ መሰረት መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በአሜሪካም ሆነ በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር የተገነባ አይደለም፡፡ ሀሳቡም የመነጨው ከየትኛውም የውጭ አካል አይደለም፡፡ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ጉልበትና መዋጮ የተገነባ ሀገራዊ ሀብት ነው፡፡ ግድቡ የሀይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመንን የሚያጎናጽፍ ብሄራዊ ኩራት ነው፡፡

ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ የአለማችን ሀያሏ ሀገር ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ በአንጡራ ሀብቷ የገነባችውን ግድብ እንዴት መጠቀም እንዳለባት በሽምግልና ስም የውሳኔ ሀሳብ ሊጥሉብን በር እያንኳኩ ነው፡፡ እዚህ ላይ በሩን ከመክፈታችን በፊት መላ መምታት አለብን፡፡

ከዚህ ቀደም የአለም አቀፍ ህግ በከፊልም ቢሆን በሚሰራበት ጊዜ አንዳንድ ሀገራት ለአለም አቀፍ ህግ አንገዛም ብለው ቡራ ከረዩ ቢሉም በስተመጨረሻ ግን ለአለም አቀፍ ስርአት ሲገዙ እናስተውል ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ዘመን ያበቃ ይመስላል፡፡ ይህን በቅርቡ በቬንዚዌላ፣ በግሪን ላንድ፣ በዩክሬን፣ በታይዋንና በደቡብ ቻይና ባህር የሆነውን አይተናል፡፡

ከሩቅ ስንሰማውና ስናየው የነበረው በአባይ በኩል ከደጃፋችን ደርሷል፡፡ ሀይል ሥርአትን ሲተካ ዲፕሎማሲ ቴያትር ይሆናል፡፡ ውልና ስምምቶችም የመድረክ ጌጦች ይሆናሉ፡፡ የድሀና ትንንሽ ሀገሮች እጣ ፈንታም በሀያላኖቹ ይወሰናል፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት?

በትህትና ፈገግ ማለት አለባት ? ወይስ ክቡርነትዎ ለውስጥ ጉዳያችን ትኩረት ስለሰጡ እናመሰግናለን እንበል? በፍጹም! ድምጻችንን ማሰማትና በአንድ ላይ መቆም ነው ያለብን፡፡ ይህን ስናደርግ ግን በግብዝነትና በግብታዊነት ሳይሆን በሰከነ መንፈስና ግልጽነትን በመፍጠር ነው፡፡

  • ግድቡ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት የተገነባ በመሆኑ ማንም የውጭ ሀይል ግድቡን አንዴት መጠቀም እንዳለብን መመሪያ ሊሰጠን እንደማይችል ግልጽ ማድረግ
  • ፍትሀዊ የውሀ ሀብት አጠቃቀም መብት አንጂ በማንም መልካም ፈቃድ የሚገኝ እንዳልሆነ ግልጽ ማድረግ
  • ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች አማራጮች ሳይሆኑ መሰረታዊ መሆናቸውን ግለጽ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ውድ አንባቢያን ይህ ጉዳይ የኢትጵያ ጉዳይ ብቻ አይደልም፡፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ጉዳዩ ይመለከተዋል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በውሀ ሀብት ርእሰ ጉዳይ የተጀመረው ጣልቃ ገብነት ነገ በማእድን፣ በንግድ፣ በግዛት ሎአላዊነትና በመንግስት ስርአት ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ የማይመጣበት ሁኔታ የለም፡፡

አሁን የምንኖርበት አለም የአለም የንግድ ድርጅት መርሆዎች በአሜሪካ የማይሰሩበት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርሆዎች ተግባራዊ የማይደረጉበትና መፈንቅለ መንግስት መፈጸም በአንድ ሀገር የሚኮነንበትና በሌላው የሚያሸልምበት ሆኗል፡፡ ምንም ማስመሰል በሌለበት ሁኔታ ሀያላኖች በአለም የዳኝነት መድረክ ለሚፈልጉት የሚወግኑበት ዘመን ሆኗል፡፡

ስዚህም አፍሪካውያን የግድ ተባብረው መቆም አለባቸው፡፡ ትብብሩ በመፈክርና በጉባኤዎች ሳሆን የራሳቸውን እጣ ፋንታ ለመወሰን በሚያስችላቸው መልኩ መሆን ይኖርበታል፡፡

  • አባይ የሚፈሰው በአሜሪካ ፈቃድ አይደለም፡፡
  • ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገነባው በአሜሪካ ይሁንታ አይደለም፡፡
  • ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን በማልማቷ ለማንም መስገድ የለባትም፡፡

ስናጠቃልለው ጉዳዩ የግድብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የክብር ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የሎአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ የኢትጵያ ህዝብ ህልምና ያለመውን ተግባራዊ የማድረግ የሀገር ስኬት ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ሀያልነት የትክክለኝነት ማረጋገጭ እየሆነ በመጣበት ዘመን ለራሳችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ማቅረብ አለብን

  • ፍትህንና ርትዕን ማን ነው የሚወስነው?
  • ሀላፊነትን መውሰድ ምን ማለት እንደሆነ የሚበይነው ማነው?
  • ዳኛው ራሱ ተጫዋች ሲሆን ምን ይደረጋል?

ምላሹ ለኢትዮጵያ ግድ ይላል፡፡ ለአፍሪካ ደግሞ የበለጠ ግድ ይላል፡፡ ለሁላችንም አንዲሁ፡፡ ጥያቄዎቹን አንደዘበት ችላ ካልናቸው ግን በራሳችን ላይ ፈርደናል ማለት ነው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...

ምንገድ ላይ

(በእውቀቱ ስዩም) በቀደም ከሆነ ቦታ ተነስቼ ወደ አልሆነ ቦታ ስራመድ...

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በጡረታ ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ...

አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ አዲስ መግለጫ አወጣች

ታዋቂዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ለስፖርት ወዳጆችና ለደጋፊዎቿ ወቅታዊ መረጃ...