የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ሰላም ለመፍጠር ከ10 እስከ 12 ቀናት ብቻ እንደሚሰጧት አስጠንቅቀዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ትራምፕ የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን የሰላም ስምምነት እንዲያርጉ የ50 ቀናት ቀነ ገደብ ሰጥተዋቸው ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አሁን ‹‹ለመጠበቅ ምንም ምክንያት አይታየኝም››ብለዋል።
ትራምፕ ‹‹እኔ ጉዳዩ እንዲፈታ ብሞክርም እስካሁን ምንም የሰላም ንግግር ሂደቶች እየተመለከትን አይደለም›› ሲሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እና ሁለተኛ ደረጃ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።
ፑቲን ጦርነቱን ስለማቆም እያወሩ በዩክሬን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ቦምብ ማዝነባቸውን በመቀጠላቸው የሰነዘሩትን ትችት ደግመውታል።
በፕሬዝዳንት ፑቲን ቅር ተሰኝቻለሁ፤ ከእንግዲህ ለማውራት ብዙም ፍላጎት የለኝም ብለዋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በኤክስ ገጻቸዉ ላይ የትራምፕን ‹‹ግልጽ አቋም እና ቁርጠኝነት›› በደስታ ተቀብለነዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የዩክሬን አየር ኃይል ፤ሰኞ ሌሊት ከ3መቶ በላይ ድሮኖች እና ሰባት ሚሳዔል በዩክሬን ላይ እንደተጣለ አስታዉቋል።
ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም
